2016-05-05 10:54:00

ቅ. አ. ፍራንቸስኮ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት ስረዓት ቅድሴ "ኢየሱስ ብቻ እውነተኛ መንገድ መሆኑን ብዙ ክርስቲያኖች ይዘነጋሉ" ማለታቸው ተገለጸ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ዘወትር ጥዋት ካህናት እና ምዕመናን በተገኙበት በምያሳርጉት ስርዓተ ቅድሴ ላይ ባሰሙት የወንጌል ስብከት ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ብቻ እውነተኛ መንገድ መሆኑን ዘንግተው ክርስትናን ግራ በተጋባ መልኩ እየተከተሉ እንደሚገኙ መግለጻቸው ታወቀ።

“ይህም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማያሳዩትን እና በመንፈስ የደረቁ ክርስቲያኖችን ያጠቃልላል” በማለት ስብከተ ወንጌላቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው “በመቅበዝበዝ ላይ የሚገኙ፣ ግትር ክርስቲያኖች እና እንዲሁም የክርስትና ሕይወታቸውን በግማሽ መንገድ ያቆሙ ክርስቲያኖች እንደሚገኙም” ጨምረው ገልጸዋል። በእለቱ በተነበበው የዩሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14, 6-14 ላይ ተመርኩዘው እና በእለቱ የተዘከሩትን ቅዱሳን ሐዋሪያት ፍሊጶስ እና ያዕቆብን አማክሎ በነበረው ስብከታቸው ኢየሱስ ለቅዱሳን ሐዋሪያቱ “እኔ እውነተኛ መንገድ ነኝ” ማለቱን አስታውሰው “ክርስቲያኖች አድፍጦ መጠበቅ አቁመው እና በእምነት ጉዞዋቸው የሚያጋጥሙዋቸውን መሰናክሎች አስወግደው  ክርስቶስን በቋሚነት መከተል” እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ግራ በተጋባ መልኩ የሚኖሩ ብዙ ዓይነት ክርስቲያኖች እንደ ሚገኙ ከገለጹ ቡኋላ አንድ አንዶቹ የመንፈስ ድርቀት የሚታይባቸው፣ አንድ አንዶቹ ደግሞ የሚቅበዘበዙ ክርስቲያኖች እንደ ሆኑ እና አንድ አንዶቹ ክርስቲያኖች ደግሞ በግማሽ መንገድ የቀሩ ክርስቲያኖች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ቅዱስነታቸው እነዚህን የተለያዩ ዓይነት ክርስቲያኖች ያሉዋቸውን በዝርዝር ሲያስቀምጡ፣ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማያደርጉ ወይም ወደ ፊት የማይራመዱ ያሉዋቸውን ክርስቲያኖች ደረቅ ወይም በድን መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ክርስቲያን ሆነው ወደ ፊት የማይራመዱ በመሆናቸው ክርስቲያን ያልሆኑ ክርስቲያኖች” መሆናቸውን በመግለጽ ስበከታቸውን የቀጠሉ ቅዱስነታቸው “እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች በትክክል ማን መሆናቸውን ማወቅ አይቻልም” ብለው “በትንሹም ጣኦት አምላኪነትን የተላበሱ ክርስቲያኖች እንደ ሚመስሉ እና ደርቀው የቆሙ እና በክርስትና ሕይወታቸው ወደ ፊት የመይነቀሳቀሱ፣ እንዲሁም የክርስቶስን አስተምሮ በሕይወታቸው የማይተገበሩ እና የምሕረት ተግባራትን እና የመሳሰሉትን የማያከናውኑ እንቅስቃሴ አልባ ክርስቲያኖች ናቸው” ብለዋል።

በአጠቃላይ “ደረቅ ሬሳ፣ በመንፈስ የደረቁ ናቸው፣ ይህንንም በማለቴ ይቅርታን እጠያቃለው” ብለው “እንደ መንፈሳዊ አስክሬን የሆኑ እና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማያሳዩ ክርስቲያኖች አሉ ክፉ ተግባራትን አይፈጽሙም እንዲሁም መልካም ተግባራትን አያከናውኑም” በማለት ገልጸዋል።

የግትርነት ምግባር የተላበሱ ያሉዋቸውን ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ሲያብራሩ “እንደ እነዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች ትክክለኛ አቅጣጫ አለመከተላቸውን ብያውቁም ቅሉ፣ ትክክለኝ አቅጣጫ እንደ ያዘ ሰው ሙጭጭ ብለው በሐሳባቸው የጸኑ ክርስቲያኖችን የጌታን ድምጽ እየተከተላችሁ ስላልሆነ ከእዚህ መንገዳችሁ ተመልሳችሁ ተክክለኛውን ጎዳና ያዙ” በማለት አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ወዲህ እና ወዲያ የሚጓዙ እና ወደ የት እየተጓዙ እናዳሉ በትክክል የማያውቁ ተቅበዝባዢ ያሉዋቸውን ክርስቲያኖች በተመለከተ ሲያብራሩ “በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሆነው የሚንከራተቱ ተቅበዝባዢ መሆናቸውን” ገልጸው “በሕይወታቸው ዘመን ወዲህ እና ወዲያ በመመላለስ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ በመግባት የሚገኘውን ደስታ የማያጣጥሙ መሆናቸውን” ገልጸዋል። “በተደጋጋሚ ወዲህ እና ወዲያ ስለሚቅበዘበዙ፣ በእዚህ ምክንያት ትክክለኛውን መንገድ ይስታሉ ወደ ሞት የሚመራቸውን የተሳሳተ ጎዳና ላይ ይመላለሳሉ” በማለት ሐሳባቸውን ያጠናከሩት ቅዱስነታቸው “መንገዳቸውን በማወሳሰባቸው ምክንያት ትክክለኛውን መንገድን ማግኜት ያዳግታቸዋል” ብለዋል።

“ሌላኛው ዓይነት ክርስቲያን ድግሞ” አሉ ቅዱስነታቸው “በክርስትና ሕይወቱ በሚጓዝበት ወቅት ቆንጆ የሆነ ነገር በሚያጋጥመው ጊዜ በእነዚህ ነገሮች ተማርኮ በግማሽ መንገድ የሚቀር ዓይነት ክርስቲያን ነው” ብለው “በሚያዩት ነገር ወይም በሚቀርብላቸው ሐሳብ ተስበው እና ተታለው የክርስትና ጎዳናቸውን የሚያቋርጡ  ክርስቲያኖች መሆናቸውን” ገልጸው “ትክክለኛ ክርቲያን በሐሳቦች እና በነገሮች የሚሳብ ሳይሆን እውነት የሆነውን ክርስቶስን መከተል መሆኑን” በአጽኖት ገለጸዋል።

ቅዱስነታቸው ከላይ የተጠቀሱትን የክርስትና ዓይነቶች ላይ ማብራሪያን ከሰጡ ቡኋላ “እራሳችንን መመርመር እና በትክክለኛው ጎዳላ ላይ መሆን አለመሆናችንን ጥያቄ ለእራሳችን መቅርብ አስፈላጊ መሆኑን” ገልጸው በተጨማሪም “የእኛ አቋም ዓለማዊ እና ከንቱ በሆኑ ነገሮች ላይ ነው? ወይስ እየተጓዝን የምንገኘው መልካም በሚባል ክርስቶስ ባስተማረን መሰረት መልካም እና የምሕረት ተጋባራትን በመፈጸም መሆኑን መመርመር አስፈላጊ መሆኑን” ገልጸው የኢየሱስ መንገድ “በመጽናናት፣ በክብር እና በመስቀል የተሞላ፣ ነገር ግን ሁል ጊዜ ለነብሳችን ሰላምን የሚሰጥ መሆኑን” አብራርተው “መንፍስ ቅዱስ በመንገዳችን እንዲመራን እና እንዲያስተምረን ልንጋብዝ እንደ ሚገባ” ገልጸው በምንደክምበት ጊዜ ሁሉ የሚያበረታንን የእግዚአብሔር ፀጋ መለመን አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ገልጸው ስብከተ ወንጌላቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.