2016-04-30 17:45:00

የ2008 ዓ.ም. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ያስተላለፉት መልእክት


በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ

የ2008 ዓ.ም. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት ያስተላለፉት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

“እንደ ሰው ሆኖም በትህትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት ድረስ፣ ያውም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው የክብር ሥፍራ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው።” (ፊሊ. 2፡8-10)

የተወደዳችሁ ብፁዐን ጳጳሳት፣

ክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያን

ምእመናንና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ወገኖች ሁሉ፡-

 

በቅድሚያ ሁላችሁም እንኳን ለ 2008 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

ሥጋ የለበሰው የእግዚአብሔር ቃል (ዮሐ.1፡14) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የሰው ልጅን ከአምላክ ጋር አስታርቆ ሰላምን ሊያደርግ ነው። “ስለዚህ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ጥበባችን፣ ጽድቃችን፣ ቅድስናችን፣ ቤዛችን እንዲሆን አደረገው”(1ኛ ቆሮ.1፡30) ይላል። ደግሞም “አሁን ግን ልጁ በሥጋ በመሞቱ ምክንያት እግዚአብሔር ከራሱ ጋር አስታረቃችሁ ስለዚህ ቅዱሳንና ንጹሐን፣ ነቀፋም የሌለባችሁ አድርጎ በፊቱ አቀረባችሁ።” (ቆላስ. 1፡ 22) ይለናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ እንድንድን በማያዳግም ሁኔታ ለሁላችን ሞቶ፣ በትንሣኤውም የዘላለምን ሕይወት ተካፋይ እንሆን ዘንድ አድርጎናል። “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! በኢየሱስ ደም አማካይነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት የሚያስችለንን መተማመኛ አግኝተናል። የምንገባውም በመጋረጃው፣ ማለትም በሰውነቱ አማካይነት በከፈተልን በአዲሱና ዘላለማዊ በሆነው መንገድ ነው።” (ዕብ. 10፡19) ይለናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ በፈሰሰው ደሙ እና አፍቃሪ በሆነው ልቡ ደኅንነታችንን አውጆልናል። በዚህም ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድናይና ቅድስናን እንድንካፈል ነው።

የዘንድሮን ዓመት የትንሣኤ በዓል፣ ለየት የሚያደርገው፣ ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቸስኮስ ከባለፈው ህዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት ያህል የሚዘልቅ “የሰማይ አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ፣ እናንተም እንዲሁ መሐሪዎች ሁኑ” (ሉቃ. 6፡36) በሚለው የወንጌል መሪ ቃል መሠረት፣ “የምህረት ዓመትን” ያወጁልን ወቅት በመሆኑ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን እግዚአብሔር በምህረቱ ባለጸጋ ነው (ኤፌ. 2፡4) ይለናል። ኃጢአትን ይቅር የሚል እና በደልን የሚደመስስ አፍቃሪ አባት እንዳለን እናምናለን። በማሰብ ይሁን በመናገር፣ በማድረግም ይሁን ተግባራችንን ባለመፈፀም ያደረግነውን ትንሽ ይሁን ትልቅ ኃጢአት ይቅር ብሎ “አባባ” ብለን እንድንጠራው የፈቀደልን መሐሪ አባት አለን። (ገላ. 4፡6) የመሐሪው የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንም፣ ምህረትን ለሰው ልጆች መስጠትን እናውቃለን። ምክንያቱም አምላካችን የበደለ እና ያልበደለ፤ ኃጢአተኛ እና ፃድቅ፣ ደግ እና ክፉ እያለ አድልዎ ሳያደርግ፣ “እርሱ ለክፉዎችና ለቅኖች ፀሐዩን ያወጣል፤ እንዲሁም ለደጋግ ሰዎችና ለኃጢአተኞች ዝናሙን ያዘንማል” (ማቴ. 5፡ 45) በዚህም ዘወትር በእኩል እኛን ልጆቹን የሚያየን፣ የሚመግበን ቸር አምላክ መሆኑን እናረጋግጣለን።

በደልን እንደበደል ሳንቆጥር፣ ይልቁንም ምህረት መስጠትን የምናውቅ ትውልድ ሆነን እንድንገኝ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ፣ ሞትና ትንሣኤ ምሥጢር ያስተምረናል። የእግዚአብሔርን ምህረት ተቀባዮች እንደመሆናችን መጠን፣ እግዚአብሔር ለእኛ ለሰዎች ስለሰራው በጎነትና ድንቅ ሥራ በእኛ አፍ በብዙ ሊመሰገን ይገባዋል። (መዝ. 107፡8) እኛም ሁልጊዜ ስለቸርነቱና ስለኃይሉ ከሁሉ በፊት ልናመሰግነው ግዴታችን መሆኑን እንረዳለን። የፈጣሪ ስጦታዎች ሁልጊዜ እርሱን ያሳስቡናል፤ በፍቅር ማሰርያም ያስተሳስሩናል።

በጌታ ትንሣኤ ክርስቲያኖች ከእርሱ ጋር አንድ የመሆንን ደስታና ከፍቅሩ ብርሃን ደግሞ የማያልቀውን መጽናናት ያገኛሉ። እኛም በየዕለቱ የህይወታችን እርምጃ፣ ወደ ክርስቶስ እንደሚያደርሰን በማመን፣ ይበልጥኑ ዛሬ ወደ እርሱ እንቅረብ፤ “እነሆ የተመረጠው ሰዓት አሁን ነው፤ የደኅንነትም ቀን አሁን ነው” (2 ቆሮ 6፡ 2)።

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰብ፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መውደዳችንና ማፍቀራችን የሚገለጠው፣ እርሱን በመምሰልና እርሱ የሰራውን ሥራ በመስራት ነው። ለዚህም ችግረኞችንና አቅመ ደካሞችን፣ እንዲሁም ህሙማንን እንድንወዳቸው፣ እንድንደግፋቸውና እንድንራራላቸው ያስፈልጋል። የዕለት ምግብ ያጡ ወገኖችን፣ የምንችለውን ያህል በመርዳትና በመመገብ፣ የክርስቶስን ብርሃን በማሳየት፣ ክብረ በዓሉ የደስታና የፍስሃ እንዲሆንላቸው፣ በእምነታችን ምስክርነትን እንድንሰጥ አደራ ማለትን እወዳለሁ።

መላው የአገራችን ሕዝቦችም አብሮ የመሥራትና ተቻችሎ የመኖር መልካም ባህላቸውን በመጠበቅ፣ የጋራ እሴቶቻቸውን በመንከባከብ፣ ለተሻለች ኢትዮጵያ እንዲሰሩ፣  እንዲሁም ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስለሆነ፣ ይህንንም ሰላም ጠብቀን እንድንኖር፣ የሰላሙ ንጉሥ ሰላሙን እንዲሰጠን ስለ ሰላም እንድንጸልይ በድጋሚ አሳስባለሁ።

ሰላም የልማት መሠረት ነው፡፡ ልማት ደግሞ የእድገት መሰላል ነው፡፡ ስለሆነም ወደ ብልጽግና መሸጋገር የምንችለው በኅብረት ጠንክረን በመሥራትና ለአላማችን ታማኞች ሆነን እድገታችንን ስናፋጥን ነው ፡፡  በግለሰብም ሆነ በህብረተሰብ አንዲሁም በአገር ደረጃ በልማት የገነባነውን በማፍረስ ከድህነት አንወጣም ፤ እንድገትም ብልጽግናም አይኖርም ፡፡ በአንፃሩ ተፈጥሮን መንከባከብ ፤ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ሁሉ ገንዘባችን አድርገን መጠበቅ ፤ አካባቢችንን አረንጓዴ፤ንጹሕና ውብ አድርገን ማስተላለፍ የትውልድ ኃላፊነታችን ነው፡፡

ሰነድ አልባ ስደተኞች ወገኖቻችን በሚንቀሳቀሱባቸው አገሮች ደኀንነታቸው በመንግስታት እንዲጠበቅ ስንጠይቅ ወጣቶቻችን በአገራቸው ድህነትን ለማሰወገድ በሚደረገው ርብርብ እንዲሳተፉ አደራ አንላለን፡፡ በአገርም ውስጥ እየኖሩ ሠረቶ መለወጥ  እንደሚቻል ሳንሰለች ምክርና ትምህርት መስጠት አለብን፡፡

በአሁኑ ጊዜ በተለይ በድርቅና በጎረፍ የተጎዱትን ወገኖቻችንን ለመርዳት፣ ከመንግሥት ጋር የሚደረገውን ርብርቦሽ ሁላችንም በምንችለው መንገድ እንድንረዳ እየተማጸንኩ፣ ምድራችን የሚያስፈልጋትን ዝናበ በረከትን እግዚአብሔር እንዲሰጣት ሁላችሁም እንድትማጸኑና እንድትጸልዩ አሳስባለሁ ፡፡

በቅርቡ በጋምቤላ ብሔራዊ መሰተዳድር መሳሪ በታጠቁ ክፍሎች በንጹሐን ዜጎቻችን ላይ የደረሰው ኢ -ሰባዊ ድርጊት ቤተክርስቲያናችንን በጣም ያሳዘነ ተግባር ነው፡፡  ይህ አይነቱም ተግባር ወደፊት እንዳይደገም መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ በመጠየቅ በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም ለክልሉና ለመላው የአገራችን ሕዝቦች እግዚአብሔር መጽጽናናትን ይስጥልን በማለት ከቦታቸው ሳይወዱ በግድ ተይዘው የተወሰዱት ወገኖቻችን ወደ አገራቸው በሰላም ይመለሱ ዘንድ ቤተክርስቲያናችን ትጠይቃለች፡፡

በመጨረሻም በህመም ላይ ላላችሁ፣ በማረሚያ ቤቶች ለምትገኙ የህግ ታራሚዎች፣ የአገርን ዳር ድንበር በማስከበር ላይ ለምትገኙ፣ በተለያዩ ምክንያት ከቤተሰብ ርቃችሁ ያላችሁ፣ ከአገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖች፣ ሁላችሁም በድጋሚ እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ። በትንሣኤው ባስገኘልን ምህረት ዘወትር ይማራችሁና ይባርካችሁ፤ በቸርነቱም ይጠብቃችሁ እያልኩ፤ በዓሉም የሰላምና የደስታ፣ የምህረትና የበረከት ለሁላችን ያድርግልን በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክና ይጠብቅ!!








All the contents on this site are copyrighted ©.