2016-04-30 11:26:00

አሞሪስ ላኤቲቲአ በቅዱስ አባታች ፍራንቸስኮ ተጽፎ በመጋቢት 30,2008 ለንባብ የበቃው ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን


የፍቅር ሐሴት

አሞሪስ ላኤቲቲአ (Amoris Laetitia)

በቅዱስ አባታች ፍራንቸስኮ ተጽፎ  በመጋቢት 30,2008 ለንባብ የበቃው  ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን

የአሞሪስ ላኤቲቲአ መዋቅር እና ትርጉም በአጭሩ በቫቲካን ሬድዮ እንደ ተዘጋጀ

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ

“የፍቅር ሐሴት” ወይም በላቲን አሞሪስ ላኤቲቲአ የተሰኘው እና ትኩረቱን ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ ስላለው ሚና ላይ በማድረግ የተጻፈው ድሕረ ሲኖዶስ ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን በመጋቢት 19, 2016 በቅዱስ ዮሴፍ የንግሥ በዓል እለት በቅዱስ አባታችን ተፈርሞ ለንባብ እንዲበቃ መታዘዙ በአጋጣሚ የተፈጠር ጉዳይ አልነበረም።

ይህ ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን ከእዚህ በፊት በቅዱስ አባታችን አነሳሽነት፣ በቤተስብ ጉዳይ ላይ ትኩረቱን በማድረግ በ2014 በተዘጋጀው ልዩ የጳጳሳት ሲኖዶስ እና በመቀጠልም በጥቅምት ወር 2015 ከ190 በላይ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ  ጳጳሳት የተሳተፉበት መደበኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ ድምር ውጤት ነው።

አሞሪስ ላኤቲቲአ (የፍቅር ሐሴት) የተሰኘው ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን ቀደም ብለው ከተካሄዱት ሁለት ሲኖዶሶች ባሻገር፣ ከእዚህ በፊት የነበሩትን የቤተ ክርስቲያን ሰነዶች፣ ከቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በፊት የነበሩ ጳጳሳት አስተምህሮዎችን እንዲሁም በቤተሰብ ዙሪያ እርሳቸው እራሳቸው የሰጡትን አስተምህሮ አጠቃሎ የያዘ ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን ነው።

እንደ ተጨማሪ ግብአት በዓለም ዙሪያ፣ ለምሳሌም በኬንያ፣ በአውስትራሊያ፣ በአርጄንቲና . . . ወዘተ ተካሂደው ከነበሩ ጳጳሳዊ ጉባሄዎች የማጠናከሪያ ሐሳቦችን የወሰደ ሲሆን በተጨማሪም የጥቁሮች መብት ተሟጋች የነበረው እና “I have a dream” (ሕልም አለኝ) በሚለው አባባሉ የሚታወቀው አሜርካዊው የሰዎች መብት ተሟጋች የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ እና  የማሕበርሰብ ስነ-ልቦና አጥኝ የነበረው ጀርመናዊው ኤንሪክ ፍሮም ጉልህ ሊባል በሚችል መልኩ የተጠቀሱበት እና “ባቤትስ ፊስት” (Babette’s Feast) የተሰኘው እና በ1987 ለመጀመሪያ ጊዜ በዴንማርክ ለእይታ የቀረበ ድራማ ላይ የተጠቀሰው እና ትኩረቱን በ19ኛ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በዴንማርክ ፓስተር ከነበረው አባታቸው ጋር ጭምት የሆነ ሕይወት ይኖሩ የነበሩ ሁለት እህተማማቾች የሚተርከው ዋና ጽንሰ ሐሳቡም በእዚሁ ሐውሪያዊው ቃለ ምዕዳን ውስጥ ተንጸባርቋል።

 

 

መግቢያ (ከአንቀጽ 1-7)

ከምዕራፍ አንድ እስከ ሰባት በሐዋሪያዊው ቃለ ምዕዳን ውስጥ የተጠቀሰው፣ በመቀጠል በዝርዝር ለሚቀርቡ ሐሳቦች እንደ መንደርደሪያ የሚሆኑ ሐሳቦችን የያዘ ነው። ይህ 325 አንቀጾች ያሉት ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን በዘጠኝ ምዕራፎች የተከፈለ ነው። የመጀመሪያዎቹ ሰባት የመግቢያ አንቀጾች የሐዋሪያዊውን ቃለ ምዕዳን አርዕስት ውስብስብነትን በግልጽ በማስቀመጥ በቀጣይነትም አስቸኳይ እና ጥልቅ የሆነ ጥናት እንዲደርግበት የሚያሳስብ ነው።

በተጨማሪም ቀደም ብለው በተካሄዱት ሁለት ሲኖዶሶች ላይ ቅዱሳን ጳጳሳት መልክ እንዲይዝ ያሳሰቡት የነፍሳት ዕንቁ “multifaceted gem” (አ.ላ. ቁ. 4)  የተሰኘው እና ውድ የሆኑ የሰው ልጆች የማንነት ሕሴቶች ተጠብቀው እንዲቀጥሉ የሚጋብዝ ሐሳቦችም ተጠቅሰውበታል። ነገር ግን ቅዱስነታቸው ጥንቃቄን በተሞላ እና ውዝግብን በማይፈጥር መልኩ   “ቀኖናዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ፣ የስነ- ምግባር ጉድለቶች ወይም ሐዋሪያዊ ተግዳሮቶች፣ ቤተ ክርስቲያን በተሰጣት ስልጣን መሰረት በምታደርገው ኦፊሴልያዊ  አስተምህሮ ወይም (magisterium) ብቻ መፈታት የለባቸውም” የሚል ሐሳብ አንጸባርቀዋል።

በእርግጥም “ለአንድ አንድ ለሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች እያአንድአንዱ ሀገር ወይም ክልል. . . ወዘተ፣ ባህሉን እና ወጉን በጠበቀ መልኩ እና የማሕበረሰቡን ጥቅም  ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ አንገብጋቢ ለሆኑ ችግሮቻቸው መፍትሄ መስጠት ይችላሉ። ‘ባህሎች አንዱ ከአንዱ የተለዩ በመሆናቸው ምክንያት አጠቃላይ ወይም ዓለማቀፋዊ የሆኑ መርዕሆች እንዲከበሩ እና ተግባራዊ እንዲሆኑ ከተፈለገ  እንደ የባህሉ ሁኔታ መወሰድ ይኖርባቸዋል’” (አ.ላ. ቁ. 4)። “እነዚህ ዓለማቀፋዊ የሆኑ መርሕሆችን ‘በባህል ውስጥ ማስረጸ’ የሚለው መርሕ ሐሳብ የሚተገበረው የችግሮችን መንስሄ በማጥናት፣ እንዲሁም መፍትሄን በመንደፍ፣ በተጨማሪም  የቤተ ክርስቲያን ቀኖናን እና ቤተ ክርስቲያን በተሰጣት መንፈሳዊ ስልጣን የምታስተምራቸውን አስተምህሮዎችን ተመርኩዞ ለአንገብጋቢ ችግሮች ተገቢ በሆነ መልኩ መልስ ሊሰጥ ይገባል። ነገር ግን በእዚህ ዓይነቱ ዘዴ የተፈታ ማንኛውም ዓይነት አንገብጋቢ ችግር ይዘቱ ዓለማቀፋዊ ’ ሊሆን አይችልም”።

በ2015 በተካሄደው ሲኖድ ላይ ቅዱስነታቸው በግልጽ እንዳስቀመጡት “ለአንድ ጳጳስ ጤናማ ጉዳይ ሆኖ የሚታየው ነገር፣ በሌላ አህጉር ወይም ሀገር ለሚኖር ጳጳስ ግን እንደ እንግዳ እና አሳፋሪ ነገር ተደርጎ ሊቆጠር ይችል። በአንዱ ጳጳስ ማሕበርሰብ ውስጥ እንደ የሰው ልጆች የመብት ጥሰት ተደርጎ የሚቆጠር ተግባር  በሌላ አህጉር ወይም ሀገር ውስጥ ለሚኖር አቡን ግን እንደ ግልጽ እና የማይጣሱ ትክክለኛ የሰው ልጆች መብትን የሚያስከብር ደንብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።  በአንዱ ማሕበረሰብ ውስጥ እንደ ሕሊና ነፃነት የሚቆጠሩ ተግባሮች በሌላው ማሕበርሰብ ውስጥ ግን እንደ ግራ መጋባት ይቆጠራሉ” ማለታቸው ይታውሳል።

ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው “በመገናኛ ብዙኃን የሚደርጉ ክርክሮች፣ አንድ አንድ አሳታሚዎች አልፎ ተርፎም በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መካከል ጉዳዩን በጥልቀት ሳይመረምሩ እና አንድ አቋም ላይ ሳይደርሱ ተመጣጣኝ ያልሆነ አጠቃላይ ለውጥ እንዲመጣ መፈለጋቸው እና  ሁሉንም ዓይነት ጉዳዮች አጠቃላይ ደንቦችን ተግባራዊ በማድረግ ለመፍታት ዝንባሌ ማሳየታቸው፣ እንዲሁም መለኮታዊ የሆኑ አስተምህሮዎችን ከግምት በማስገባት ወደ አልተፈለገ ድምዳሜ ማምራት” (አ.ላ. ቁ. 2) ቅዱስነታቸው በግልጽ እንዳስቀመጡት የለውጥ ጥያቄዎችን እና ውስብስብ የሆኑ ሕግጋትን አጠቅላይ ተግባራት ጎን ለጎን አስቀምጠን በግልጽ ከመፈርጅ መቆጠብ  እንደ ሚገባ ገልጸኋል።

ምዕራፍ አንድበብርሃነ ቃሉ” (ከአንቀጽ  8-30)

የመንደርደሪያ ሐሳባቸውን ተከትሎ ቅዱስነታቸው ትኩረታቸውን በመጻሐፍ ቅዱስ ላይ መሰረት በማድረግ የመጀመሪያ የቃለ ምዕዳናቸውን ምዕራፍ የጀመሩት በመዝሙር 128 ላይ አስተንትኖ በማድረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በቤተሰብ፣ በልደት፣ በፍቅር ታሪኮች እና የቤተሰብ ቀውስ የተሞላ ነው" (አ.ላ. ቁ. 8)። “ይህ እውነታ እንድናጤን የሚገፋፋን የቤተሰብ ጉዳይ ውስብስብ አለመሆኑን እና ነገር ግን ዕለታዊ፣ ተጨባጭ እና ነባራዊ ተግባር መሆኑን ሲሆን  (አ.ላ. 16) እንዲሁም  በርኅራኄ የሚተገበር (አ.ላ. 28) ነግር ግን ከጥንት ጀምሮ እንደ ሚታየው፣ በፍቅር ላይ የተመሰረት ግንኙነት በሚለወጥበት ጊዜ እና አንዱ ሌላውን በሚጫንበት ወቅት ግጭት የሚጋረጥበት ሕይወት ነው (አ.ላ. ቁ. 19)።

ስለእዚህ የእግዚኣብሔር ቃል ‘በተወሳሰቡ ሐሳቦች የተሞላ ሳይሆን፣ ነገር ግን በችግር ወይም በመከራ  ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን የሚያግዝ  እና የመጽናናት ሁሉ ምንጭ ነው፣ ምክንያቱም ወደ የሕይወታቸው ግብ ስለ ሚመራቸው” (አ.ላ. 22) በማለት በቤተሰብ ውስጥ ስለሚታዩ በጣም ብዙ ሊባሉ ስለሚችሉ መልካም ነገሮች እና ተግዳሮቶች በማውሳት ለችግሮቻቸው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመርኩዘው መፍትሄን እንድያበጁ ያሳሰቡበት ምዕራፍ ነው።

ምዕራፍ ሁለትየቤተሰብ ተመኩሮዎች እና ተግዳሮቶች” (አንቀጽ 31-57)

በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ቅዱስነታቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ላይ በመመርኮዝ አሁን ባለንበት ዘመን ያለውን የቤተሰብ  ሁኔታ ያብራራሉ። ነባራዊ እውነታ ላይ በመመርኮዝ(አ.ላ. 6) የቤተሰብ ተሞክሮን የገመገመ እና በተለይም ከእዚህ በፊት ተካሄደው የነበሩ ሁለት ሲኖዶሶች ጠቅላላ ሪፖርት ላይ መሰረቱን ያደረገ ነው።

ከሰዎች ፍልሰት አንስቶ እስከ በጾታዎች መካከል ስላለው ልዩነት የሚያወሳው ስነ-ጾታዊ ርዮተ ዓለም (አ.ላ 56)፣ እንዲሁም አዲስ ከሆነ ባሕል እስከ ውልጃን የሚከለክል አስተሳሰብ (ማስወረድ፣ abortion) እንዲሁም በእርግዝና ወቅት አሁን እየታየ ያለው የባዮቴክኖሎጂ ተጽዕኖ”፣ ከመኖሪያ ቤት እጥረት እስከ በብልግና ሥራ ላይ እስከ ተሰማሩ ሰዎች የሚያወሳ፣ ለአካለ መጠን ያልደርሱ ልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን አካላዊ እና ሞራላዊ ጥቃቶችን የሚዳስስ፣ የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎች ትኩረት መንፈጋቸውን የሚገልጽ፣ በእድሜ የገፉ ሰዎች ክብር መነፍጋቸውን የሚያብራራ፣ ቤተሰብን ሕጋዊ በሆነ መልኩ ማለያየት የሚያመጣውን መዘዝ እና በሴቶች ላይ በሚደርሰው ጥቃት ምክንያት ቤተሰብ ብዙ ተግዳሮቶች እየደረሰበት መሆኑን ይተነትናል። ቅዱስነታቸው በሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ትኩረታቸውን ያደረጉት ተጨባጭ በሆኑ እውነታዎች ላይ ነው። 

ለተጨባጭ እና ለነባርዊ እውነታ ትርጉሜን በሚሰጠው ንድፈ ሐሳብ እና አጠራጣሪ በሆነው ርዕዮተ ዓለም መካከል ያለውን ልዩነት ጉልህ በሆነ መልኩ መለየት የሚቻለው በሕይወት ውስጥ የሚታዩትን ተጨባጭ እና እውነተኛውን የሕይወት ተመክሮዎችን፣ እንዲሁም  እለት በእለት በሕይወት ውስጥ የሚታዩትን ፈተናዎችን  መገንዘብ ሲቻል ብቻ ነው።

“Familiaris consortio” ከተሰኘው እና በቅዱስ ዩሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ከተጻፈው ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን በመጥቀስ “የመንፈስ ቅዱስ ጥሪ እና ፍላጎት በታሪክ ክስተቶች ውስጥ ስለ ሚያስተጋባ ተጨባጭ የሆኑ እውነታዎች ላይ ማትኮር አለብን’ ይህም ደግሞ ‘ቤተ ክርስቲያንን ይበልጥ ጥልቅ ወደ ሆነ የማይነጥፍ የጋብቻ ምስጢርን እና ስለ ቤተሰብ ግንዛቤ እንዲኖራት ይረዳል’” (አ.ላ. 31) የሚለው ሀርግ በሰፋት ይተነተንበታል። በሌላ በኩል እውነታን መረዳት ካልቻልን አሁን ያለውን ፍላጎት ወይም የመንፍስ ቅዱስን እንቅስቃሴን መረዳት አንችልም ማለት ነው። ቅዱስነታቸው ሲያብራሩም “አንድ ሰው እራሱን ለሌላ አሳልፎ እንዳይሰጥ በአሁኑ ጊዜ እየተሰፋፋ ያለው ግለሰባዊነት (Egoism) ሁኔታዎችን አስቸጋሪ እንደ ሚያደርግም” (አ.ላ. 33) አስገንዝበኋል። “አስገራሚው ነገር” አሉ ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው “ብቸኝነትን መፍራት፣ መረጋጋትን መፈለግ እና ታማኝነትን ለማግኘት ፍላጎትን ማሳየት ጋር አብሮ ጎን ለጎን የሚጓዘው እነዚህ ነግሮች አንድ ሰው የግል ግቦችን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት የሚያሰናክል ወጥመድ ተደርጎ መወሰዱ ነው” (አ.ላ. 34) በማለት የግለሰባዊ አስተሳሰብ የፈጠርውን ውስብስብነት እና በነጻነት የተረጋጋ ሕይወት ለመኖር የሚደረገውን ፍልሚያ በንጽጽር ገልጸዋል።

እውነታን የተከተለ ትህትና እና “ከተጨባጭ እውነታ የራቀ ጋብቻን የተመለከተ በጣም ረቂቅ፣ ሰው ሠራሽ ሥነ-መለኮታዊ ሐሳብ፣  እውነተኛ እና በቤተሰብ ውስጥ ተጋባርዊ ሊሆኑ የማይችሉ ሐሳቦችን” (አ.ላ. 36) እንድናስወግድ ይረዳናል። ሀሳባዊነት በእራሱ ትዳርን በቅጡ እንድንረዳ አያደርገንም። ያም ማለት “የሰው ልጅ ግላዊ እና አካላዊ እድገት ተለዋዋጭ መንገድን የተከተለ” መሆኑን መረዳት ውሳኔዎች በሚደርጉበት ወቅት ሁሉ ይህንን መርሕ ሐሳብ የተከተለ ሊሆን ያስፈልጋል። ይህም  “የእግዚአብሔርን ጸጋ በግልጽ እንዲ ቀበሉ ሳናበረታታ ዶክትሪንን ወይም የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አስተምህሮ፣ የስነ-ሕይወት እና የስነ-ምግባር ጉዳዮችን” (አ.ላ. 37) ቤተሰብን ይደግፋሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል እና ከእውነት እና ከተጨባጭ ሁኔታ የራቀ ሐሳብ ነው።

የጋብቻን እና የቤተሰብ ተመክሮን ያላማከለ ትችት” እና በቂ ያልሆነ አቀራረብ እንዲኖር የሚያደረግ ተግባር ተወግዶ በአንጻሩም ቅዱስነታቸው በቃል ሞዳናቸው እንዳሳሰቡት ምዕመናን ሕሊናቸውን እንዲጠቀሙ እድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስረግጠው አሳስበው የተጠራነው ሕሊናን ለማነጽ እንጂ ሕሊናን ለመቀየር አይደለም (አ.ላ. 37) በማለት ትችትን እና ችኩል የሆነ ውሳኔን ከመውሰድ መታቀብ እንዳለብን አሳስበዋል።  ኢየሱስ የሚጠይቀን ገንቢ የሆኑ ሐሳቦችን እንድንከተል ነው እንጂ “ልክ ስታመነዝር እነደ ተያዘችው ሳምራዊት ሴት ያሉ ግለሰቦችን  መቼም ቢሆን ምሕረቱን እና አለኝታነቱን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ነፍጎ አያውቅም” (አ.ላ. 38) በማለት ፍርደ ገምድል መሆን እንደ ሌለብን እና ሁኔታዎችን አንድ በአንድ መመርመር እንደ ሚገባን አሳስበዋል ።

ምዕራፍ ሦስትየቤተሰብ ጥሪ ኢየሱስን መከተል ነው”  (ከአንቀጽ 58-88)

ሥስተኛው ምዕራፍ ትኩረቱን ያደረገው ጋብቻን እና የቤተሰብ ጉዳይን የተመለከቱ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዎች ላይ ነው። ይህ 30 አንቀጾች ያሉት ምዕራፍ በጣም አስፈላጊ እና ወቅታዊ ሊባል የሚችል ምዕራፍ ነው። ምክንያቱም የቤተሰብ ጥሪ በወንጌል ላይ ተመስርቶ እና ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ሂደት ያረጋገጠችው እና ምን መሆን እንዳለበት የሚናገር እና የሚያሳይ በመሆኑ ነው።

ከሁሉም በላይ ትዳር እስከ ሕይወት ፍጻሜ የሚጸና መሆኑን የተሰመረበት ሲሆን፣ የትዳር ምስጢራዊ የተፈጥሮ ገጽታ እና ሕይወትን ቀጣይ እንዲሆን የማድረግ ተግባሩ፣ እንዲሁም ለሕጻናት ስለሚሰጠው መሰራታዊ ትምህርት አስፈላጊነትን ይገልጻል። “Gaudium et Spes” (ደስታ እና ተስፋ) ከተሰኘው የሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ፣ “Humanae Vitae” (የሰው ሕይወት)  ከተሰኘው የጳውሎስ ስድስተኛ አወዲ መልዕክት እና “Familiaris Consortio”  (ቤተሰብ ባለንበት ዘመን) ከተሰኘው የቅዱስ ዩሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን በሰፊው የተጠቀሱበት ምዕራፍ ነው።

ይህ ምዕራፍ ፍፁም ያልሆኑ ሁኔታዎችን በሰፊው የሚመለከት እና የሚዳስስ ምዕራፍ ጭምር ነው። በሌሎች ባሕሎች ውስጥፍሬማ የሆኑ ዘሮች” (Ad Gentes 11 በአማሪኛ ለሕዝብ) መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ይህም ደግሞ ከጋብቻ እና ከቤተስብ ነባራዊ እውነታ ጋር በማጣመር መገለጹ በእዚህ ምዕራፍ ውስጥ መመልከት ይቻላል።

“ተፈጥሮአዊ እና እውነተኛ ከሆነው ጋብቻ በተጨማሪም አንድ አንድ ጊዜ ድንግዝግዝ ሆኖ ቢታይም አዎንታዊ የሆኑ ግንቢ ነግሮች በሐይማኖታዊ ወግ የተፈጸመ ጋብቻ ውስጥ ይገኛሉ” (አ.ላ. 77)። “በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች በማለት ቅዱስነታቸው በ2015 በተካሄደው ሲኖድስ የማጠቃለያ ሪፖርት ላይ እንደ ገለጹት እና በትዳር ሕይወት ውስጥ በገጠማቸው ችግር እየተሰቃዩ የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታ የሚዘረዝር ሐሳብ በእዚህ ምዕራፍ በሰፊው የተዳሰሰ ሲሆን “’እረኞች ማወቅ ያለባቸው ነገር ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት ስለ እውነት ሲባል በጥንቃቄ  ሁኔታዎችን የመመርመር ግዴታ እንዳለባቸው የሚያስገድዳቸውን አጠቃላይ መርዕ ማስታወስ ምንጊዜም አስፈላጊ ነው” (Familiaris Consortio. 84) በማለት በውሳኔ አሰጣጥ ወቅት ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበኋል። “ኋላፊነትን መሰረት ያደርጉ ውሳኔዎች በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ተመሳሳይነት ባለው መልኩ ሊተገበሩ እንደ ማይገባ እና በአንድ አንድ ሁኔታዎች የሚደረጉ ውሳኔዎችን የመገደብ አጋጣሚ ልያስከስቱ ይችላሉ። ስለእዚህ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በግልጽ መተግበር አስፈላጊ ቢሆንም መጋቢው ወይም እረኛው የነባሪዊ እውነታውን ውስብስብነት ሳያጤን፣ በትኩረት ሳይመለከት፣ ሰዎች ተመኩሮዎቻቸው እና  በችግራቸው ምክንያት እያሳለፉ ያለውን ስቃይ ሳያገናዝብ ውሳኔ ከመውሰን ሊቆጠቡ ይገባል” (አ.ላ.79) በማለት አሳስበኋል።

ምዕራፍ አራትፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” (ከአንቀጽ 89-164)

አራተኛው ምዕራፍ ትኩረቱን ያደረገው ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በጻሐፈው የመጀመሪያ መልዕክቱ በምዕራፍ 13,4-7 ላይ መሰረቱን በማድረግ ፍቅር በትዳር ውስጥ ያለውን ሚና ይገመግማል። የእዚህ ምዕራፍ የመክፈቻ ክፍል በእርግጥም እጅግ አድካሚ ሊባል የሚችል ሥራ ወይም  ተግባራት የታየበት እና በቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት አነሳሽነት የተጻሐፈ እንዲሁም ትኩረቱንም በእዚሁ መልዕክት ላይ ያደረገ ነው።

ይህም በጥንቃቄ የተጻሐፈ እና ተጨባጭ በሆነ መልኩ በሰው ልጆች መኋል ሊኖር ስለ ሚገባ ፍቅር የሚገልጽ፣ ይህንንም የሚያረጋግጥ እና ለይቶ የሚያሳውቅ፣ እንዲሁም ስነ-ልቦናዊ ሐሳቦችን በመመርኮዝ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ ነው። እነዚህ ስነ-ልቦናዊ ማብራሪያዎች በትዳር ዓለም ውስጥ በመግባት የሚታዩትን አዎንታዊ እና አሉታዊ ሁኔታዎች በመዳሰስ፣ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑትን የፍቅር እሴቶችን በሚገባ ይዳስሳል። ይህም በክርስትና ደንብ ጋብቻ ለፈጸሙ ሰዎች ሁሉ ትዳርን በተመለከተ ቱባ እና ጠቃሚ የሆነ አስተዋጾ በማድረግ ረገድ ይህ ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን ቀደም ሲል የነበሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከጻፉኋቸው ሐዋሪያዊ መልዕክቶች ሁሉ ለየት እንዲል ያደርገዋል።

በተጨማሪም ይህ ክፍል ሰፊ እና ውስብስብ የሆነውን የትዳር ሕይወትን አጭር በሆነ መልኩ ዕለት በዕለት የሚከናወኑ ነባራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እና በጋብቻ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ የፍቅር ተመክሮ በመውሰድ በሚታዩት ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ተንተርሶ፣ መስፈርቶችን ተጠቅሞ ፍርድ ከመስጠት ቅዱስነታቸው ተቆጥበው ፍጹም በሆነ በክርስቶስ እና በቤተ ክርስቲያን መካከል ባለው አንድነት ላይ ተመርኩዞ ሁለት ውስን የሆኑ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መጫን አስፈላጊ አይደለም ምክንያቱም ጋብቻ በተፈጥሮው ተለዋዋጭ ሂደትን የሚያስተናግድ በመሆኑ፣ እነዚህ ሰዎች ቀስ በቀስ ከእግዚአብሔር ስጦታ ጋር ይዋሀዱ ዘንድ ማገዝ ያስፈልጋል (አ.ላ. 112) በማለት አጠቃላይ የሆኑ መስፈርቶችን ተጠቅሞ ከመፍረድ በመቆጠብ የሰው ልጆችን ውስንነት ከግምት ያስገባ ጠንቃቃ ውስኔ ማድረግ አንደ ሚገባ አስምረውበታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ቅዱስነታቸው በጣም ጠበቅ ባለ ሁኔታ ሊታወቅ እና ሊከበር የሚገባው ሀቅ በትዳር ሕይወት ውስጥ ያለው ፍቅር በተፈጥሮ የሚያስረዳን ይህ ፍቅር ተጠብቆ ዘላቂ አንድነት እንዲኖር መሆኑ መረሳተ እንደ ሌለበት(አ.ላ. 123)  በአጽኖት ገልጸው በአጭሩም በትዳር ውስጥ “ደስታ እና ትግል፣ ውጥረት እና እረፍት፣ ጭንቀት እና እፎይታ፣ ህመም እና ፈውስ፣ እርካታ እና ምኞት፣ ንዴት እና ተድላ” (አ.ላ. 126) . . . ወዘተ የመሳሰሉትን ተነጻጻሪ ተግባርት እንዲሁም የችግሮች እና የደስታ ቅልቅል ውጤት መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዱናል።

አራተኛው የአሞሪስ ላኤቲቲአ (የፍቅር ሐሴት) ምዕራፍ መደምደምያውን የሚያደርገው “የፍቅር ለውጥ” በሚለው አርዕስት ላይ ተመርኩዞ በጣም አስፈላጊ ሊባል የሚችሉ ሐሳቦችን በመሰንዘር ሲሆን “በአሁኑ ወቅት ረዘም ያለ እድሜ  ማለት፣ የቅርብ እና ለየት ያለ፣ ምን አልባትም የአራት እና የአምስት ወይም የስድስት አስርተ አመታት ግንኙነት ማለት ሊሆን ይችላል፣ በእዚህም ምክንያት የመጀመሪያው ውሳኔ በተደጋጋሚ መታደስ አለበት” (አ.ላ. 163) በማለት ፍቅር ተደጋጋሚ የሆነ እድሳት እንደ ሚያስፈልገው ያትታል። አካላዊ ቁመናችን እንደ ሚያሳስበን እያደግን በመጣን ቁጥር ፍቅራዊ መሳሳብ እየቀንሰ የሚመጣ ነገር ሳይሆን በአንጻሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሩካቤ ሥጋ ፍላጎታችን በማደስ አብሮነታችሁን እንድታጠብቁ እና በጋራ በጉጉት መኖር እንድትችሉ ያደርጋል፣ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ አንድ አይነት የሆነ ስሜት ሊሰማን ይገባል የሚል ምንም ዓይነት ዋስትና የለም። ሆኖም አንድ ባልና ሚስት የሚጋሩት አንድ የጋራ እና ዘላቂ ሕይወት ውጥን ካለቸው እርስ በእርስ ልዋደዱ ይችላሉ እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው ድረስም አንድ ሆነው ይኖራሉ የጠበቀ እንድነታቸውንም ያበለጽጋሉ” (አ.ላ. 163) በማለት ከሁሉም በላይ በትዳር ውስጥ የጋራ የሆነ የሕይወት ውጥን አስፈላጊነት እና የሰው ልጅ ተለዋዋጭ ስሜትን መግታት የሚቻለው የጋራ ዘላቂ እቅድ ሲኖረን ብቻ አስረግጠው የገለጹበት ምዕራፍ ነው።

ምዕራፍ አምስትፍቅር ፍሬያማ ያደርጋል” (ከአንቀጽ 165-198)

የአሞሪስ ላኤቲቲአ አምስተኛ ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ያደረገው ፍቅር የሚያስገኘውን ፍርሬ እና ስነ-ውልደት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው። መንፈስዊ እና ስነ ልቦናዊ በሆነ መልኩ አዲስ እርግዝናን ስለ መቀበል፣ በእርግዝና ወቅት ስለ ሚታየው የውልደት ቀን ጥበቃ፣ እንዲሁም ስለ እናት እና አባት ፍቅር በጥልቀት ይዳስሳል።

በተጨማሪም ፍሬያማ ስለሆነ ጉድፈቻ፣ “የአብሮነትን ባሕል” እና የቤተሰባዊ ኑሮን ሰፋ ባለ መልኩ ማለትም አክስትን፣ አጎትን፣ የአክስት እና የአጎት ልጆችን፣ ዘመዳ ዘመዶችን እንዲሁም ጓደኝነትን  ለሚያበረታቱ እና ለእዚህም አስተዋጾ የሚያደርጉትን  ቤተሰቦችን በተገቢው መልኩ ያወድሳል። አሞሪስ ላኤቲቲአ ወይም የፍቅር ሐሴት ቃለ ምዕዳን ቤተሰብን የሚረዳው በጣምስ ሰፋ ባለ መልኩ በመሆኑ ምክንያት  “በቅርብ የቤተሰብ አባላት ብቻ” ወይም በእንግሊዜኛው (nuclear family) ማለትም (እናት፣ አባት፣ ወንድም፣ እህት፣ አያት የመሳሰሉ የቅርብ ጸመዶች) ላይ ትኩረቱን አላደረገም። “በቤተ ክርስቲያን ምስጢራት የታነጸ ጋብቻ ማሕበራዊ ገጽታ አለው” (አ.ላ.187)። ከእዚህ ማሕበራዊ ገጽታ በመነሳት ቅዱስነታቸው ለየት ባለ ሁኔታ ማጉላት የፈለጉት በወጣቶች እና በአረጋዊያን መኋከል የሚፈጠርው ግንኙነት በማሕበርሰቡ ውስጥ የተለየ ሚን እንደ ሚጫወት እና እንዲሁም በወንድም እና እህት መካከል ያለው ጥብቅ ግንኙነት ደግሞ ከሌሎች ጋር በቀጣይነት ለሚደረጉ ግንኙነቶች እንደ መለማመጃ ሜዳ መሆኑንም በተጨባጭ የገለጹበት ምዕራፍ ነው።

ምዕራፍ ስድስትሐዋሪያዊ አመለካከቶችከአንቀጽ (199-258)

በስድስተኛው ምዕራፍ ቅዱስነታቸው ተጨባጭ በሆነ መልኩ እና በእግዚአብሔር እቅድ ላይ የተመሰረተ ፍሬያማ የሆነ ቤተሰብ ለመመስረት አስተዋጾ የምያደርጉትን በዛ ያሉ ሐዋሪያዊ ተግባራትን የዳሰሱበት ምዕራፍ ነው። ይህ ምዕራፍ በተጨማሪም በቤተሰብ ዙሪያ የመከርውን የመጀመሪያ እና የሁለተኛው ሲኖዶስ አጠቃላይ ሪፖርት የያዘ ሲሆን፣ ቅዱስነታቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ያስተላለፉኋቸውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮችን እንዲሁም ከቅዱስ ዩሐንስ ጳውሎስ አስተምህሮዎችም የተውጣጡ ሐሳቦች ይገኙበታል።

ቤተሰብ ሁል ጊዜ መሰብክ የለበትም ቤተሰብ አንድ አንዴ ሊሰብከን ይገባል ብለኋል በእዚህ ምዕራፍ።  ቅዱስነታቸው ካህናት ብዙን ጊዜ ቤተሰብ እየተጋፈጠ  ያለውን የተወሳሰቡ  ችግሮችን  የመፍታት ችሎታ ለማዳበራቸው” (አ.ላ. 202) ጸጸት በተሞላው መልኩ ገልጸኋል። በሌላም በኩል ደግሞ በዘርሃ ክህነት ለሚገኑ ተማሪዎች የሚሰጠው ስነ-ግንኙነትን የተመለከቱ አስተምህሮ መሻሻል እንደ ሚገባቸው እና በዘርሃ ክህነት በሚሰጠው የሕንጸት ትምሕርት ቤተሰብ ሊሳተፍበት ይገባል (አ.ላ. 203) ብለው በሌላም በኩል “ የምስራቃዊ አብያተ ክርስቲያናት አባላት የሆኑ ያገቡ ካህናት ልምዳቸውን እንድያካፍሉ ሊጋበዙ ይገባል” (አ.ላ. 202) የሚልም ሐሳብ የተንጸባረቀበት ነው።

በመቀጠልም ቅዱስነታቸው የዳሰሱት ለጋብቻ ዝግጅት ስለ ሚሰጠው አስተምህሮ ሲሆን፣ በተለይም ደግሞ ተጋቢዎች በመጀመሪያው ዓመት የጋብቻ ሕይወታቸው ስለ ሚደርገግላቸው መንፈስዊ ድጋፍ በማውሳት ኋላፊነት የሚሰማቸው ወላጆች እንዲሆኑ፣ ውስብስብ በሆኑ ሁኔታዎች እና በመከራ ወቅት ሁሉ “እያንዳንዱ መከራ አስተምሮ የሚያልፈው ትምህርት መኖሩን እና ለልቦናችን የሚያስተላልፍልንን ትምህርት በማዳመጥ” (አ.ላ. 232) እና የችግሮች ሁሉ መነሻ በጥልቀት ከተጠና ቡኋላ የችግሮችን መንስሄ ስይዘገዩ በአጭሩ መቅጨት (አ.ላ. 239) መልመድ ይኖርብናል የሚል ሐሳብ የተንጸባረቀበት ነው።

በተጨማሪም የተረሱ፣ የተለያዩ እና የተፋቱ ቤተሰቦች መንፈስዊ ድጋፍ እነደ ሚያስፈልጋቸው ያሳስባል። ይህ ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን እየተሻሻለ ያለውን እና ሁኔታዎች በሚገባ ከተጠኑ ቡኋላ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ  ምስጢረ  ተክሊልን እንዳልነበረ (anulation) የማድረግ ሥልጣን ያለውን እና በመርቀቅ ላይ የሚገኘውን ሕግ አስፈላጊነትን ያጠናክራል። በተጨማሪም በግጭት ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙ ሕፃናትን ሁኔታ በስፋት በመዳስስ “ፍቺ ክፉ ነገር ነው። ስለእዚም የእኛ ሐዋሪያዊ  ሥራ ዋና ተግባር መሆን ያለበት በቤተሰብ ውስጥ ፍቅር እንዲጠናከር መርዳት ነው” (አ.ላ. 246) በማለት ፍቺ የሚያስከትለውን ማሕበራዊ እና ቤተሰባዊ ቀውስን ይዘረዝራል። በመቀጠልም በአንድ የካቶሊክ አማኝ እና በሌላ የክርስትና እመነት ተከታይ መካከል ስለሚፈጸመው ጋብቻ (mixed marrige) እንዲሁም በአንድ የካቶሊክ እምነት ተከታይ እና የክርስትና መሰረት የሌለው እምነት በሚከተሉ ግለሰቦች መካከል የሚፈጸመው ጋብቻ (የአምልኮ አለመመጣጠን የሚታይበት) ያትታል።

 

ምዕራፍ ሰባትየልጆች የተሻለ የትምህርት አቅጣጫ” (ከንቀጽ 259-290)

የአሞሪስ ላይቲቲአ ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን ሰባተኛው ምዕራፍ ለልጆች የሚሰጠውን መሰረታዊ ትምህርት በሰፊው በመዳሰስ፣ ስነ-ምግባራዊ ሕነጻን፣ ስነ-ስርዓት ይማሩ ዘንድ ቅጣትን ያካተተ ተግሣጽ መስጠትን፣ በትዕግሥት እውነታን ማስተማርን፣ የስነ-ፃታ ትምህርት መስጠትን፣ እምነትን ማስተላለፍ ወይም ማውረስን፣ በአጠቃላይ የቤተሰብ ሕይወትን መሰረት ያደርገ አስተምህሮ  መስጠት እንደ ሚገባ ያሳስባል። በእዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚታየው ጥበባዊ አገላለጽ ትኩረትን ሊስብ የሚችል ሐሳቦች የተጠቀሱበት ሲሆን በተለይም ደግሞ እርጋታን የተሞላ ሂደትን የተከተለና መከተል ያለብንን መንገድ “በሚገባ፣ ተቀባይነት እና ተደናቂነትን” (አ.ላ.271) በተላበሰ መልኩ ለሰዎች በሚያጎናጽፍ መልኩ በዝርዝር ተቀምዋል።

በእዚህ ምዕራፍ ውስጥ በጣም ማራኪ እና ሳይንሳዊ የማስተማር ዘዴን የተከተሉ መሰረታዊ ሐሳቦች የተጠቀሱበት አንቀጾች የሚገኙ ሲሆን በተለይም ደግሞ ቅዱስነታቸው ግልጽ በሆነ መልኩ “ውትወታ ትምሕርት ሊሆን አይችልም፣ ልጆች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን እያንዳንዱን ሁኔታ መቆጣጠር አንችልም. . .ቤተሰብ ልጆቻቸው የሚያከናውኑትን እያንደንዱን ተግባር ለማወቅ በሚያሳዩት ከፍተኛ ጉጉት እያንደንዱን  እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረት ሁኔታዎች ላይ ጫና ይፈጥራል። ነገር ግን ይህ ተግባር ልጆቻቸው ለውደፊት የሚገጥሙዋቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም እንዲችሉ ለማዘጋጀት እና ጠንካራ እንዲሆኑ ለማስተማር የሚበጅ መንገድ አይደለም። በጣም አስፈላጊው ነገር በፍቅር እና በነፃነት እንዲሁም በብስለት እንድያድጉ መርዳት፣ በአጠቃላይ በስነ-ሥረዓት እና እራሳቸውን በመግዛት” (አ.ላ. 260) እንድያድጉ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል አሳብ የተንጸባረቀበት ነው።

ምዕራፍ ስምንትመምራት፣ መወሰን እና ድክመትን ማቀናጀት” (ከአንቀጽ 291-312)

ስምንተኛው ምዕራፍ ወደ ምሕረት የሚጋብዝ እና ከጌታ ሐሳብ ጋር ሙሉ በሙሉ የማይስማሙ ወይም የማይዛመዱ  ሁኔታዎችን በማስተዋል ሐዋሪያዊ ሥራን ማከናወን እንደ ሚገባ የሚያሳስብ ነው። ቅዱስነታቸው  በእዚህ ምዕራፍ መምራት፣ ማስተዋል እና ማቀናጀት ወይ ማዛመድ የሚሉ ሦስት መሰረታዊ የሆኑ ግሦችን በመጠቀም በቀላሉ ለአደጋ ሊጋለጡ የሚችሉ፣ ውስብስብ ጉዳዮችን እና ያልተለመዱ ሁኔታዎችን ለመፍታት መጠቀም አስፈላጊ መሆናቸውን የገለጹበት ምዕራፍ ነው።

በተጨማሪም ሐዋሪያዊ ተግባራት ርህራሄን በተሞላው መልኩ መፈጸም እንደ ሚገባቸው የሚያሳስብ ክፍል የተካተተበት ሲሆን በተለይም ደግሞ ማስተዋል አስፈላጊ እንደ ሆነ፣ ደንቦችን የማቅለያ ሁኔታዎች በሐዋሪያዊ ሥራ ውስጥ በማስተዋል እንዲተገበሩ የሚመክር ሲሆን በመጨረሻም ቅዱስነታቸው በማስተዋል ጥበብ የተሞላ ሐዋርያዊ ምሕረት ማድረግ እንደ ሚገባ የሚተነትን ጭምር ነው።

ምዕራፍ ስምንት በጣም አጉዋጊ ምዕራፍ ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ይህንን ምዕራፍ በሚያነብበት ወቅት የቤተ ክርስትያን ተግባር ልክ እንደ አንድ ሆስፒታል ተግባር (አ.ላ. 219) መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት እንድያነብ የሚጋብዝ በመሆኑ ነው። ቅዱስ አባታችን  ቀደም ሲል በተካሄዱት ሲኖዶሶች ላይ በተነሱ አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮች እና የተወሰኑ ውሳኔዎች ላይ የታገሉበትን ፍሬ ሐሳብ ይተነትናል።  ክርስቲያናዊ ጋብቻን የሚመለከት እና ቤተ ክርስቲያን በማንኛውም ሆኔታ “ስለ ጋብቻ ያላት ግንቢ እና ዋና ዋና አስተምህሮዎችን እየተጋፉ ያሉትን እና ለወደፊቱም የሚከሰቱትን ጋብቻን የተመለከቱ ከአስተምህሮዋ ጋር የማይዛመዱ አስተሳሰቦችን በንቀት ልትመለከት አይገባም” (አ.ላ. 292) የሚል ማሳሰብያ ያዘለ ነው።

ልማዳዊ ያልሆኑ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ልደርግ ስለ ሚገባው ማስተዋል ቅዱስነታቸው ሲጠቅሱ “የሁኔታውን ውስብስብነትን በቅጡ ስያጤኑ እና ሰዎች በችግራቸው ምክንያት እየኖሩት ያለውን የጭንቀት ሕይወት  በትኩረት ሳይመለከቱ ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ” (አ.ላ. 296) የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ያሳስባሉ። በመቀጠልም “እገዛ የሚያስፈለጋቸውን ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ማሕበርሰብ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ እና ‘ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ለማይገባውም እንኳን በነጻ በሚሰጥ ምሕረት ይዳሰሱ ዘንድ ሁሉም የክርስቲያን ማሕበርሰብ አጥጋቢ በሆነ መልኩ የእራሳቸውን አስተዋጾ ማድረግ እንደ ሚጠበቅባቸው’” (አ.ላ. 297) የሚያሳስብ ምዕራፍ ጭምር ነው።

“መጀመሪያ መስርተውት ከነበረው ትዳር በመፋታት አዲስ የሆን ግንኙነት የጀመሩ ሰዎች ለምሳሌም፣ በተለያዩ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እና ጥብቅ ከሆነ  የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና ሐዋሪያዊ ተግባር ጋር አብሮ የማይሄዱ ተግባሮችን የሚፈጽሙ ሰዎችን በተመለከተ ማስተዋልን የተላበሰ ሐዋሪያዊ ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል (አ.ላ. 298) በማለት ያትታል። 

ይህንን በተመለከተ ቀደም ሲል በተደርገው ሲኖዶስ ለተሳተፉ ጳጳሳት ቅዱስነታቸው “ፍቺ የፈጸሙ እና በማዘጋጃ ሌላ አዲስ ትዳር የመሰረቱ ክርስቲያኖች በክርስቲያን ማሕበርሰብ ውስጥ ለሌሎች እንቅፋት በማይሆን መልኩ ሙሉ በሙል ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደ ሚገባ” ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው። “እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች ምንም ዓይነት በቤተ ክርስቲያን እንደ ተወገዙ  እንዲሰማቸው የሚያደርገውን ተግባር በማስወገድ በምትኩም የቤተ የክርስቲያን ቋሚ አባል፣ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እንዲሳተፉ እና እንዲታነጹ እንዲሁም ልጆቻቸውን በቤተ ክርስቲያን ወግ እና ስረዓት እንድያሳድጉ ማገዝ እና በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል” (አ.ላ. 299) በማለት ያትጣል።

ቅዱስነታቸው በስምነተኛው ምዕራፍ ዋና የሆነውን እና ማስጨበጥ የፈለጉትን ግንዛቤ እና የሐዋሪያዊው ቃለ ምዕዳንናቸው ዋና ትጉም በሚገልጸ አረፈተ ነገር “የተለያዩ ተጨባጭ የሆኑትን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት፣  ቀደም ሲል የተደርጉ ሲኖዶሶች ወይም ይህ ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን፣ ቀኖናዊ የሆኑ ሕግጋትን መሰረት በማድረግ እና ለሁሉም ሊተገበር የሚችል  አዲስ የሆነ አጠቃላይ መመሪያ ወይም ሕግ ይወጣል ተብሎ መጠበቁ እሙን ነው። ነገር ግን የሚፈለገው ዋናው ነገር በኋላፊነት ላይ የሚገኙ ሰዎች ተግባራቸውን  በታደሰ መልኩ እንዲወጡ የሚያበረታታ እና ለየት ላሉ የተወሰኑ ጉዳዮች ማስተዋልን በተላበሰ መልኩ እገዛ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሐዋሪያዊ እንክብካቤን ማድረግ፣ የኃላፊነት ደረጃ በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ እኩል አለመሆኑን እና የሚያስከትለውን መዘዝ ወይም ውጤት የግድ ሁል ጊዜ አንድ ዓይነት መሆን እንደ ማይገባው መገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን” (አ.ላ. 300) የሚያሳስብ ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን መሆኑን አውስተዋል። ቅዱስነታቸው በጥልቀት የመረመሩት ጉዳይ በምዕመናን እና በመጋቢያቸው ወይም እረኛቸው መካከል ማስተዋልን በተላበሰ መልኩ ጥልቅ የሆነ ውይይት እንዲደረግ እና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ሐዋሪያዊ እጀባ እንዲደረግላቸው በሚያሳስበው ጉዳዮች ላይ ነው።

በእዚህም ምክንያት የተነሳ ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን ሐሳቡኋን “የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች እና ሁኔታዎችን” ኃላፊነት እና ባለቤትነትን በተላበሰ መልኩ፣ ተጠያቂነትን የተሞላ እርምጃ  ላይ እንድታደርገ እና ከቅዱስ ቶማስ አስተምህሮዎች በመጥቀስ በደንቦች እና በማስተዋል መካከል ያለውን ግንኙነት ላይ የሚያተኩረውን “አጠቃላይ ደንቦች ልያስገኙ የሚችሉት መልካም እና እውነት የሆኑ ነገሮች ችላ ሊባል አይገባም። ነገር ግን እነዚህ ሕጎች ሲቀመሩ ለሁሉም ዓይነት ችግሮችን ሙሉ በሙሉ መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ማሰብ ግን አይቻልም።  በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ሊታወቅ የሚገባው ለየት ያሉ ሁኔታዎች በሚገጥሙ ጊዜ የሚሰጡ መፍትሄዎች ወደ ሕግ ደረጃ ሊለወጡ አይችሉም” (አ.ላ. 304)።

የምዕራፍ ስምንት የመጨረሻው ክፍል “ሐዋሪያዊ ምሕረት የማድረግ የማስተዋል ጥበብን የተመለከተ ነው። ቅዱስነታቸው ማንኛውንም ዓይነት አለመግባባትን ለማስወገድ በማሰብ አጥብቆው እና ደጋግመው እንደ ገለጹት “ልማዳዊ ያልሆኑ ነገሮችን ለመፍታት የሚቀርቡ ልዩ ሐሳቦች ኢየሱስ ለሰው ልጆች የሰጠውን ወይም ብርሃንን የሚያደመዝዝ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በዛሬው ጊዜ  ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ እና የሐዋሪያዊ ሥራ ውድቀት የነበረው ትዳርን ለማጠናከር የሚደረግ እንቅስቃሴ እና ትዳርን ከፍቺ መታዳግ ላይ ያተኮረ ሐዋሪያዊ ተግባራትን ማከናወን” (አ.ላ. 307) ሊሆን ይገባል።

የእዚህ ምዕራፍ አጠቃላይ ስሜት እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮ ምኞት የቤተ ክርስቲያን ሐዋሪያዊ ተግባር መንፈስ መሆን የሚገባው እና ለምዕመናን እና ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጥሪ ያቀረቡት “ በተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ምዕመናን ሁሉ ችግሮቻቸውን በልበ ሙሉነት ለእረኞቻቸው ወይም ሕይወታቸውን ለጌታ ለሰው ምዕመናን እንዲናገሩ አበረታታለው። ይህንንም በምታደርጉበት ወቅት እናንተ  ይዛችሁት የምትሄዱ ሐሳብ እና ምኞታችሁ ሁሉ ያሳካል ማለት ሳይሆን፣ ሁኔታችሁን በማስረዳት መፍትሄ ሊሆን የሚችል ብርሃን ልታገኙ እና እራሳችሁን የምታሳድጉበትን ግንቢ ነገሮች ልታገኙ ትችላላችሁ። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን የማበረታታው ነገር በተመስጦ እና በተረጋጋ መልኩ ችግሮችን እንድታዳምጡ እንዲሁም እየኖሩበት የሚገኘውን መከራ  እና ሐሳባቸውን ለመረዳት ፍላጎት በማሳየት የተሻለ ሕይወት እንዲኖር እንድተረዱ እና ለቤተ ክርስቲያን ልያበረክቱ የሚችለውን አስተዋጾ እውቅና እንድትሰጡ” (አ.ላ. 312) ያስፈልጋል በማለት ገልጸኋል። 

“የሐዋሪያዊ ምሕረትን የማድረግ የማስተዋል ጥበብን” በተመለከተ ቅዱስነታቸው በማጉላት እንደ ገለጹት “አንድአንዴ በሐዋሪያዊ ተግባራችን ወቅት ወሰን ለሌለው የእግዚኣብሔር ምሕረት ቦታን አንሰጥም። ምሕረትን በተመለከተ ብዙ ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ተጨባጭ የሆነው ትርጉዋሜውን  ወይም ክብደት እናሳጣዋለን። ይህም ደግሞ ወንጌልን ተገቢ ባልሆነ መልኩ የማሰራጨት ተግባር ነው” (አ.ላ. 311) ብለው በሐውሪያዊ ተግባራት ውስጥ ለመለኮታዊው የእግዚኣብሔር ምሕረት ቦታ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ገልጸኋል።  

ምዕራፍ ዘጠኝየጋብቻ እና የቤተሰብ መንፈሳዊነት” (ከአንቀጽ 313-325)

ይህ ዘጠነኛው እና  የአሞሪስ ላኤቲቲአ በአማሪኛው የፍቅር ሐሴት ቃለ ምዕዳን የመጨረሻው ምዕራፍ ሲሆን ትኩረቱንም  የጋብቻ እና የቤተሰብ መንፈስዊነት ላይ ያደረገ እና ትዳር “ትንሽ የሚመስል ነገር ግን በሺዎች በሚቆጠሩ ትናንሽ ምልክቶች የተገነባ” (አ.ላ. 315) መሆኑን በስፋት ያትታል። ቅዱስነታቸው በግልጽ እንዳስቀመጡት “ጥልቅ መንፈሳዊ ምኞት ያላቸው ሰዎች፣ የቤተሰብ  ሕይወት የመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገታቸውን እንደ ሚቀንስ ሳይሆን ሊሰማቸው የሚገባው፣ በአንጻሩ በቤተሰብ ሕይወት ጌታ ወደ ታላቅ የምሥጢራዊ ህብረት ጎዳና እንደ ሚመራቸው ማሰብ ይኖርባቸዋል” (አ.ላ. 316) ብለዋል።   “በደስታ ጊዜያት፣ በመዝናናት ወቅት፣ በባዓላት እና እንዲሁም የግብረ ሥጋ ግንኙነት በሚደረግበት ጊዜ ያለው ተመክሮ የትንሣኤ ሙሉ ሕይወት እንደ መጋራት ሊቆጠር ይችላል” (አ.ላ. 317) በማለት በጋብቻ እና በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የሚከናውኑ ተግባራት በፍቅር ከተፈጸሙ መንፈሳዊ ባህሪያት እንደ ሚላበሱ ለመግለጽ የተጠቀሙበት አንቀጽ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

በተጨማሪም “በትንሳኤ ብርሃን የተሞላ ልዩ መንፈስዊ ሕይወት፣ ፈተናዎች ቢጋረጡበትም ጸንቶ የቆመ ንጹሕ ፈቅር፣ እስከ እርጅና ድረስ አብሮ ለመዝለቅ የሚያሳዩት ጉጉት የእግዚአብሔር ታማኝነት ያንጸባርቃል” (አ.ላ 319) እንደ ተጠቀስው። በመጨረሻም እንክብካቤን ማድረግ፣  ማጽናናት እና ማበረታታት የመንፈሳዊነት ግጽታ እንዳላቸው ገልጸው “ሁሉም የቤተሰብ ሕይወት በምሕረት የተሞላ እረኝነት መሆኑን ገልጸው፣ እያንዳንዳችን የምናሳየው ፍቅር እና እንክብካቤ ለሌሎች ጥሩ ተምሳሌት ሊሆን ይችላል” (አ.ላ. 322) በማለት በቤተሰብ ውስጥ ሊከናወን ስለሚገባው እንክብካቤ እና ምሳሌያዊ የሆነ ሕይወት መኖር አስፈላጊ መሆኑን ያብራራል። እነዚህ ጥልቅ "መንፈሳዊ ተመክሮዎች የምንወዳቸውን ሰዎች ስናስብ በአምላክ ዓይን መመልከት እና ክርስቶስን በእነርሱ ውስጥ መመልከት” (አ.ላ. 323) እነደ ሚገባን ቅዱስነታቸው ያሳስቡናል።

በመጨረሻው አንቀጽ ላይ ቅዱስነታቸው የሚያሳስቡን “ፈጹም በሆነ መልኩ ተመስርቶ ከሰማይ ወደ ምድር የተላካ ቤተሰብ የለም፣ የፍቅርን ሕልውና  ለመጠበቅ ቤተሰብ ሁል ጊዜ ቀጣይነት ባለው መልኩ ማደግ እና መብሰል ይኖርበታል. . .ሁላችንም ከእኛ ከሁላችን በላይ እና ከቤተሰባችን ሁሉ  በላይ ወደ ሆነው ነገር መጓዝ እንዳለብን እና ኣያንዳንዱ ቤተሰብ ይህንን የማያቋርጥ የተነሳሽነት ስሜት ማዳበር ይኖርበታል። እስቲ በአንድነት ይህንን የቤተሰብ ጉዞ እናድርግ እብረንም እንጓዝ. . . ባለብን ውስንነት ተስፋ መቁረጥ ወይም በሙላኋት መዋደድ ማቆም እና እግዚአብሔር አስቀድሞ የሰጠንን ሕብረት ማጉደል አይጠበቅብንም” (አ.ላ. 325) በማለት የቤተሰብ እና የትዳር ሕይወት ላይ ትኩረት ያደረገው ቃለ ምዕዳን በማሳሰብ እና ወደ ቅዱስ ቤትሰባ ጸሎት በማቅረብ ተጠናቋኋል።

ማጠቃለያ

የአሞሪስ ላይቲቲአ ሐዋሪያዊ ቃል ምዕዳን ከይዘቱ መረዳት እንደ ሚቻለው “ጥሩ ሊባል የሚችል ቤተሰብን ለማጽናት” መከተል የሚገባንን መንገድ ሙሉ በሙሉ የሚገልጽ ሐዋሪያዊ  ቃለ ምዕዳን መሆኑን ሳይሆን ነገር ግን በአጽኖት የሚዳስሰው እና የሚገልጸው ተጨባጭ በሆነ መልኩ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የሚታዩትን በጣም ቱባ ሊባሉ ይሚችሉ  መልካም ነገሮችን የሚዳስስ እና በተጨማሪም  የቤተሰብ ሕይወት ውስብስብነትን  የሚዳስስ ሐዋሪያዊ ቃል ምዕዳን ተደርጎ ቢወሰድ በይበልጥ ይዘቱን ለመረዳት ያስችለናል።

በሐዋሪያዊው ቃለ ምዕዳን ገጾች ውስጥ የተጠቀሱ ጉዳዮች ውስብስብ ወይም ደግሞ ሐሳባዊነት በተላበሰ  መልኩ የተገለጹበት ሳይሆን ቅሉ በጣም መልካም ሊባሉ የሚችሉ ጉዳዮችን ተጨባጭ  እና ክፍት በሆነ ልብ ላይ ተመስርተው በጥልቀት የተዳሰሱበት እና ተጨባጭ እውነታዎችን ያገናዘበ  ሐዋሪያዊ  ተግባራትን ማከናወን እንደ ሚገባ በግልጽ ያሳዩበት ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን ነው።

በተጨማሪም ይህ ሐዋሪያዊ  ቃል ምዕዳን በመንፈሳዊ ዓይን እና ተጨባጭ እውነታዎችን ባገናዘበ እና ጥበብ በተሞላው መልኩ የቤተሰብን ወይም ቤተሰብ ለመመስረት ያሰበ ግለሰብን  የሕይወት ሁኔታን የሚያስነብበን ቃለ ምዕዳን ነው።

ከሁሉም በላይ ግን ሰዎች ለብዙ ዓመታት በታላቅ ትዕግስ ለኖሩት የትዳር ሕይወት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ እና ተጨባጭ ተመኩሮዎችን ከግምት ያስገባ ነው። በአጠቃላይ አሞሪስ ላይቲቲአ ወይም የፍቅር ሐሴት የተሰኘው ሐዋሪያዊ  ቃል ምዕዳን  በቤተሰብ ውስጥ መታየት ስላለበት ፍቅር ላይ ተንተርሶ እና ተመክሮዎችን ከግምት አስገብቶ ተስፋን በሚሰጥ ቋንቋ ማበረታቻን የሚለግስ እና ቀስ በቀስ በትኩረት ሊነበብ የሚገባው ሐዋሪያዊ ቃለ ምዕዳን ነው።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.