2016-01-07 11:51:00

እግዚአብሔር አባታችን ዓለምን በልጁ በማደስ የዘለዓለም ሕይወትን ሰጥቶናል፡፡


በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“እነሆ ሕፃን ተወልዶልናል፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ እርሱም መሪ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ይባላል፡፡” (ኢሳ 9፡6)

ብፁዐን ጳጳሳት፣

ክቡራን ካህናትና ገዳማውያንና ገዳማዊያት፣

የተወደዳችሁ ምዕመናን ፣

በጎ ፍቃድ ያላችሁ ወገኞች፣

እንደዚሁም መላው የአገራችን ሕዝቦች፣

ከሁሉ አስቀድሜ በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለሁላችሁም የእግዚአብሔር ፀጋና ሰላም እንዲበዛላችሁ በመመኘት እንኳን ለ2008 ዓ. ም. የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ በማለት በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም መልካም ምኞቴን እገልጽላችኋለሁ፡፡

በነብዩ ኢሳያስ የተነገረለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶልናል፡፡ በጽድቅም መንገሥ ፍፁምነትን አምጥቶልናል፡፡ በእርሱም በኩል ሰዎችን ሁሉ ማዳን የሚችል የእግዚአብሔር ፀጋ ፍቅርና ምህረት ተገልጦልናል፤ ስለሆነም በልደቱ ቀን እርሱን በአክብሮት እንቀበለዋለን፡፡ ቋሚ ሰላምንም ይዞ በመምጣት መውደዱንና ቸርነቱን አሳይቶናል፡፡

እግዚአብሔር አባታችን ዓለምን በልጁ በማደስ የዘለዓለም ሕይወትን ሰጥቶናል፡፡ እኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል መንፈሣዊ ጸጋችን በልባችን ሁልጊዜ እየበረታ ሊሄድ  ይገባል፡፡ ለዚህም በእግዚአብሔር ቤት መኖር ታላቅ ደስታ በመሆኑ ወደ ክርስቶስ መቅረብ ይኖርብናል፡፡ ትሑታን የሆንን በእርሱም ሙሉ በሙሉ ያመንን ከሰላሙ ንጉሥ ሰላምን እናገኛለን፡፡

በነብዩ ሶፎኒያስ እንደምናገኘው “የምድር ትሑታን ሁሉ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ትሕትናንም ፈልጉ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፡፡” ይለናል (ሶፎ፤2፡3)

ትሑት ሆኖ በከብቶች በረት ውስጥ የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንም ራሳችንን ዝቅ በማድረግ ትሑታን እንዲያደርገንና ልባችንን በምህረትና በደግነት እንዲሞላ አጥብቀን ልንለምን ያስፈልጋል፡፡ ትሑታን መልካምን ነገርን ሁሉ አግኝተው መልካም ሥራ ይሠራሉና፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስኮስ ከኅዳር 28 ቀን 2008 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር 11 ቀን 2009  ዓ. ም. ለመላው ካቶሊካውያን የእግዚአብሔር ምህረት ልዩ የኢዩቤልዩ ዓመት ሆኖ የምህረት ወንጌል ለሰው ሁሉ እንዲዳረስ፤ በንሰሐ እንድንታደስ፤ የእግዚአብሔርንም የምህረት ስራ የሆነውን ፍቅርን፤ ይቅርታን፤ ቸርነትን እንድንፈፅም አውጀውልናል፡፡ እኛም በየሀገረስብከቶቻችንና በየቁምስናዎቻችን  ካህናት፤ ወንዶችና ሴቶች መነኮሳት ፤ ካቴኪስቶችና ምዕመናን በሙሉ በምህረት የተገለጠው ጌታ የማዳን ዓላማው እንዲታወጅና እንዲስፋፋ ለመሥራት እንነሳሳ፡፡ በቤተሰቦቻችን መካከል፤ በተለይ በባሎችና በሚስቶች እንዲሁም በወላጆችና በልጆች መካከል ሰላምና ፍቅር እንዲጎለብትና የእግዚአብሔር ምሕረት እንዳይርቀን ሁላችንም እንድንጸልይ አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡

“አምላካችን ሆይ እንደምሕረትህ እነጂ እንደኃጢአታችን አይሁንብን፡፡” (ቅዳሴ) በጌታችን የልደት በዓል በአጠገባችንና በአካባቢያችን ለሚገኙት ችግረኞች፤ ድሆች፤ አቅመ ደካሞችና ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናት የተለመደውን በጎ ሥራችንን እንለግሳቸው ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል በጽኑ አደራ ይለናል ፡፡ መረዳዳትና መደጋገፍ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነውና፡፡

መንግስት የሕዝቦችን ጥያቄ ለመመለስ እየሠራ ላለው የመልካም አስተዳደር ግንባታና የአገር ዕድገት ሥራ ሁሉም ትብብሩን እንዲያደርግ እየጠየቅሁ በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ተከስቶ ባለው የተፈጥሮ መዛባት በአገራችን ያስከተለውን ከፍተኛ የድርቅ ችግር ለመቋቋም መንግስት ከለጋሾች ጋር በመሆን ችግሩ ለደረሰባቸው ወገኖች የምግብ ዕርዳታና የነፍስ ማዳን ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሁላችንም በፀሎታችን እንድንበረታ እያስገነዘብኩ፤ ቤተ ክርስቲያናችንም እንደቀድሞው ሁሉ ከመንግሥትና እንዲሁም ከሌሎች በጎአድራጊዎች ገር በመሆን የበኩሏን ኃላፊነት አየተወጣች መሆኗን እገልጻለሁ፡፡

“በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም የሁን ፡፡”   (ሉቃስ 2፡14) እንደዚሁም የሰላምና የአብሮ መኖር እሴቶችን ለማጠናከርና ለማስቀጠል፤ እነዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማሰፈን ይቻል ዘንድ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ሁሉ በሰከነ መንፈስ በውይይትና በመከባበር መፍታትና ዘለቄታዊ መፍትሔ መሻት ከሁላችን የሚጠበቅ መሆኑን ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እግዚአብሔር የታመማችሁትንና የአልጋ ቁራኛ የሆናችሁትን እንዲምራችሁ፤ ታስራችሁ በየማረሚያ ቤቶች የምትገኙትን እግዚአብሔር እንዲፈታችሁ፤ በተለያዩ ሥራዎች በአገር ድንበርና በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ የተሰማራችሁ ወገኖች፤ እነዲሁም በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡ የልደቱ በረከት ፀጋና ምህረት፤ ፍቅሩና ሰላሙ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.