2015-12-29 11:17:00

ሓ. ጳውሎስ " የጨለማን ስራ አውልቀን የብርሃንን የጦር መሳርያ እንልበስ".


የእግዚአብሔር  ወዳጆች  ሁላችሁ የእግዚአብሄር ጸጋ እና ምህረት ይብዛላችሁ

ሓዋሪያው ጳውሎስ እንድህ ይላል "ሌሊቱ ሊያልፍ ነው፣ ቀኑም ቀርቧል፤ ስለዚህ የጨለማን ስራ አውልቀን የብርሃንን የጦር መሳርያ እንልበስ". የሓዋርያው ቃል አሁን ላለንበት ዘመን የሚሆን ትልቅ መልእክት ያለው ነው፤ ዘመኑ ሰው ብርሃንን  ትቶ ጨለማን  የመርጠበት፤ በፈጣሪው መታመን አቁሞ በቁሳዊ  ነገር የሚመካበት፤ የህይወት ቃል ከመስማት ሁከትንና መለያየት ለሚለኩሱ አስተሳሰቦች ጆሮዎቹን በብርሃን ፍጥነት በሚከፍትበት አስቸጋሪ እና ፈታኝ  ዘመን ላይ ላለን  ለኛ ይህ  መልእክት በእውነት የመንቅያ ደወል ሊሆን ይገባል።

ክፉ ነገር በጨለማ ይመሰላል። ጨለማ የብርሃን ያለመኖር ብቻ አይደለም፤ በአምላኩ አምሳል የተፈጠረ ሰው እንዳምላኩ ፈቃድ መኖር ሲያቅተው፤ የመጨረሻ ግቡ  የሆነውን እግዚአብሄርን ማየት ተስኖት የዚህ አለም አላፊ ከንቱነት ላይ አይኑን ሲያማትር፤ ብርሃን እንድሆነ የተፈጠረው ክቡር የሰው ልጅ  በጨለማ ውስጥ ይኳትናል። ለዚህም ነው ህዋሪያው ዮሃንስ የህይወትን ቃል ልነገረን "እግዚአብሄር ብርሃን ነው በርሱ ዘንድ ጨለማ ከቶ የለም" የሚለን። ነገር ግን ሃዋርያው ሲመክረን "ከግዚአብሄር ጋር ህብረት አለን እያልን በጨለማ የሚንኖር ከሆነ እንዋሻለን በሕይወታችን እውነት የለም ማለት ነው" በብርሃን የሚመላለስ ሁሉ ህብረት አለው፤ መለያየት የጨለማው ንጉስ የዲያብሎስ ግዛት ነው፤  እኛ ግን ጠበቃችን በሆነው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ከጨለማ ወደ ምያስደንቅ ብርሃን የተጠራን፤ የእግዚአብሔርን አስደናቂ ስራ እንድናውጅ የተመረጥን ትውልድ፤ የንጉሱ ካህናት፤ እግዚአብሄር ለራሱ ያደረገን ቅዱስ ሕዝብ ነን"። ለዚህ ሁሉ ክብር መመረጣችን የኛ ተገቢዎች መሆን ሳይሆን ያምላካችን እግዚአብሔር ወሰን የማያውቀው፤ የኛ ህጢአት የማይገድበው፤ በፍቅሩና በርህራሄው ወደር የማይገኝለት፡ እንደኛ እንደሰዎች  ለፍርድ የማይቸኩል፡ ለነቀፋ ጊዜ የለለው፤ ፍጹም በሆነ ፍቅሩ ስለወደደን ነው። ዛሬ ሓዋርያው ዮሃንስ እንዲህ ይለናል "ሃጢሓት የለብንም ብንል ራሳችንን እናታልላለን፤ እውነትም በኛ ውስጥ የለም፤ ሓጢአታችንን ለእግዚአብሄር ብንናዘዝ እርሱ ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ሃጢአታችንን ይቅር ይልልናል፤ ከበደላችንም ሁሉ ያነጻናል"።

 

ዛሬ የእግዚአብሄርን ምህረት የተቀበልንበትን ፣ በአንድ ልጁ ራሱን ለኛ የገለጠበት፤ ፍቅሩ ለኛ ለልጆቹ እነዴት ጥልቅ እንደሆነ ያየንበትን የቅዱስ ቃሉን ክፍል ነበር ዛሬ ቅድስት ቤ.ክርስቲያን ያሰማችን፤ «እግዚአብሄርን ያየው ከቶ ማንም የለም ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ያለው አንድ ልጁ ብቻ ገልጦታል" ምክንያቱም "ቃል ስጋ ሆነ፤ ፀጋንና እውነትን ተመልቶ በኛ አደረ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን»። የጌታችንን መወለድ በታላቅ ደስታ እየጠበቅን ነው፤ የገናንም በዓል ለማክበር በዝግጅት ላይ እንገኛለን፤ በዚህ  ወቅት ሀገራችን ኢትዮጲያ ምስራቃዊው ክፍል በትልቅ ድርቅ የተመታበት ዓመት ነው፣ ብዙ ወገኖቻችን በረሃብ አለንጋ እየተቀጡ ነው፤ በውሃ ጥም እየደከሙ እየሞቱም ነው፡  ከብቶቻቸውም እያለቁባቸው የመኖራቸው ዋስትና አደጋ ላይ እየወደቀ ነው፡ ታዲያ እኛ ምን እያሰብን ነው? የክርስቶስ ልደት ማክበር ማለት እነዚህን ወገኖች ማሰብ ቢሆን፣ ካለን እና ለዓመት በዓል ብለን ከሚናባክነው ነገር ግማሽ እንኳን ብናደርግላቸው በእዉነት በብርሃን ነን፤ አለበለዚያ ግን ፡«ተሪቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፤ ታሪዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜ አልጠየካችሁኝም፤ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም፤ ታስሬ አልጎበኛችሁኝም» ለሚለን ጌታ ምን ይሆን መልሳችን? ዛሬም «እግዚአብሔር ወንድምህ የት ነው ይለናል» እርግጠኛ ነኝ ወንድሜ ማነው እንደማንል። መክንያቱም  የኛ  ወንድም የስጋ ወንድማችን ብቻ ስላልሆና ጌታ በደሙ የአንድ አባት ልጆች፤ ወንድምና እህት ስላረገን፤ የእግዚአብሄር ልጅ የህያው አብ ቃል ስጋ መልበስ የእግዚአብሄርን ከኛ ጋር መሆኑን የምያበስር ታላቅ ዜና ነው፡ ታዲያ እርሱ ከኛ ጋር ከሆነ እኛም ደግሞ ከደከሙት ጋር፣ ጉልበታቸው በረሃብና በዉሃ ጥም ከዛለባቸው ጋር ልንሆን የግድ ነው፣ ይህ ነው እንግዲህ ክርስቲና። ይህ ነው የተቀበልነውን የማያልቀውን የፍቅር ስጦታ ከተጎዱ ወገኖቻችን ጋር ልናሳልፍ ቃል ልንገባ የሚግባን፤

በሁለተኛ ደረጃ ማስብ የሚገባን ነገር ቢኖር ከድርቁና ከረሃቡ ባሻገር በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ያለመግባባቶች ይስተዋላሉ፡ ይህም  መተኪያ የለለውን የሰው ልጅ ህይወት እና ለወገን እና ለሃገር የሚሆን ንብረት የሚዎድሚበት ሁኔታ ይታያል፤ « ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ ስላሜን እተውላችኋለሁ፤ እኔ የሚሰጠው ሰላም ይህ አለም እንደሚሰጠው አይደለም» ውድ የክርስቲያኖች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ፤ ይህች አለም ሰላም ያስፈልጋታል፤ አለም ሰላም እንድትሆን በያንዳንዳችን ልብ ሰላም ልነግስ ይገባል፤ ጠላታችን ዲያብሎስ ሰላማችንን ለመንሳት ቀንና ሌሊት ይታትራል፤ እኛም የሱን አላማ ለማስካት እርስበርስ ጥላቻን ዘርተን ሞትን እናጭዳለን፤ ይህች አለም ለእያንዳንዱ ሰው የሚበቃ ያማያልቅ ሃብት ይዛለች፤ ግን ይህ አለማችን የያዘችው ሃብት ለአንድ ስስታም ግለሰብ በቂ መስሎ አይታየውም፤ ጌታችን ክርስቶስ ፍቅር ዘርተን ሰላምን እንድናጭድ እነሆ በመካከላችን መወልድን ፈቅዷል፤  ሰላም ባለብት ድህነት የለም፤ ሰላም ባለበት ረሃብ የለም፤ ዛሬ የሰው ልጅ እንጀራ ብቻ አይደለም የተራበው፤ የውስጥ ሰላምን ጭምር እንጂ፤ ዛሬ የሰው ልጅ ውሃን ብቻ አይደለም የተጠማው እውነተኛ ፍቅርን ጭምር እንጂ፤ ዛሬ ሰላም የሚመጣው የሰላሙ መሪ የሆነውን የሰላም ጌታ ኢየሱስን ስናዳምጠው ብቻ ነው'«ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት የእግዚአብሄር ልጅ የመሆን ስልጣን ሰጣቸው እነርሱም ከ እግዚአብሄር ተወለዱ እንጂ ከሰው ዘር ም`ማለትም ከስጋ ልማድ ወይም ከሰው ፍቃድ አልትወለዱም»። እንግድህ ሰላም በልባችን እንዲብቅል የእግዚአብሄር ልጆች ልንሆን ያስፈልጋል፤ ከእግዚአብሄር የሆነ ስለመለያየት አይስብክም ምክንያቱም ማለያየት የዲብሎስ የስራ ድርሻው ነውና፤ እኛ ዛሬ «ከርሱ የፀጋ ሙላት በፀጋ ላይ ፀጋን ልንቀበል ተጠርተናል፤ ምክንያቱም ህግ ስለበደላችንና ስለህጢአታችን ስከሰን ፀጋና እውነት የሃጢአታችን ስርየት በጌታ ኢየሱስ በኩል አገኘን፡ እንግዲህ ሳንስፈልገው ፈልጎ ለወደደን ጌታ ልባችንን ልንከፍትለት ይገባል፤ ለአለም ሁሉ ጌታ እና የታሪካችን ደራሲ የሆነው ኢየሱስ ዛሬ የሚወለድበትን ንፁህ ልብ በመፈለግ ይንከራተታል፤ በነፃ ለማከም፤ በነፃ ለማዳን፡ የለምንም ክፊያ ህይወት ልሰጠን እነሆ ወደ በረክት ይጠራና፤ አኡባልታን ትተን፤ እርባና ከለሌው ከፍሬ አልባ ሽኩቻ ርቀን ዛሬ የሰላሙን ነጉስ  በልባችን፤ በቤታችን፤ በሰፈራችን፤ በአካባብያችን፤ በአገራችን ብሎም በአለም ዙርያ ሁሉ ልንቀበልው እንዘጋጅ፤ 

 በመጨረሻም እግዚአሄር አምላክ በዚህ የምህረት አመት የበደሉንን ይቅር የንልበት፤ የተሳሳተ ስህተቱን የሚረዳበትና እውነትን የሚፈልግበት፤ በረሃብ የሚማቅቁ ወገኖቻችን እግዚአብሄር ዝናብን በፍጥነት እንዲልክላቸው፤ ምድርም ፍሬዋን በጊዜ እንድትሰጣቸው እየትፀለይኩ በአለም ዙሪያ በጦርነት ምክንያት ተሰደው የሚሰቃዩትን እግዚአብሄር ፍጥኖ ፍትህ እንድሰጣቸው ፈቃዱ ይሁን፤

በመጨረሻም የጌታችን እና የመድሃንታችን የልደት በአል ለአገራችን ኢትዮጲያ የጸጋና የበረክት እንዲሆን እመኛለሁ፤

የእግዚአብሀሔ ምህረት ለመላው ካቶሊካዊያንና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ ይሁን፡

የእግዚአብሄር ስም ለዘላለሙ የተመስገነ ይሁን።   
All the contents on this site are copyrighted ©.