2015-12-18 16:31:00

ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ለልደታቸው ቀን ከካቶሊክ ተግባር ማኅበር ወጣቶች ጋር


የመልካም የምህረት የሰላም የግብረ ሠናይ የመደጋገፍ መንገድ በመከተል ክፋትን ቂም በቀልተኛነትን ጦርነትና ስግብግብነትን እምቢ እንዲባል ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ እ.ኤ.አ. ታህሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. 79ኛው ዓመተ ልደታቸውን ባካበሩበት ቀን የኢጣሊያ የካቶሊክ ተግባር ማኅበር አባላት ወጣቶችን ተቀብለው በለገሱት ምዕዳን በአደራ እንዳሰመሩበት የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ ፓውሎ ኦንዳርዛ ገለጡ።

ቅዱስ አባታችንን በበዓለ ልደታቸው ቀን 60 የካቶሊክ ተግባር ወጣቶች ማኅበር አባላት ያቀረበላቸው የደስታ መግለጫ መልእክት በደስታ በመቀበል፣ በዚህ ከወዲሁ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ለማክበር በመዘጋጀት ላይ ባለንበት የምጽአት ቀናት ቅዱስነታቸው ለወጣቶቹ ከወዲሁ መልካም በዓለ ልደት ተመኝተው ይኽ ዓቢይ የድህነት ቀን ስደተኞችን በማስተናገድ ይከበር ዘንድ ምዕዳን ለግሰዋል።

ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ለተወለዱባት ቀን ምክንያትም ከወጣቶቹ ለቀረበላቸው ጣፋጭ ኅብስት ተቀብለው ወጣቶቹ ለቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ ለመሰከሩት ቅርበትና ፍቅር አድንቀው፣ ሁላችን ወደ ጌታ ተጓዦች ነን ብለው፣ ሁሉም ወንጌል በቅርብ በማወቅና በማስተዋል በቃለ ወንጌል ተነቃቅቶ ወንጌላዊ ልኡክ እንዲሆን መጠራቱ እንዳይዘነጋ አሳስበው፣ ያንን የካቶሊክ ተግባር ማኅበር የዘንድሮ መንፈሳዊ መርሆ እንዲሆነው የመረጠው ቃል ጎዙ ወደ አንተ የሚል መሆኑ አስታውሰው ዘወትር ወደ ጌታ ተጓዦች ነን እንዳሉ ኦንዳርዛ ገለጡ።

ወደ ጌታ መጓዝ ምን ማለት ነው? የሚለውን በለገሱት ምዕዳን ለሁሉም ያቀረቡት ጥያቄ ቅዱስ አባትችን፣ ሲመልሱም በመልካም ጎዳና በመጓዝ ለክፋት መንገድን እምቢ፣ በምህረት ጎዳና በመጓዝ ለቂም በቀልተኝነትን እምቢ፣ በሰላም ጎዳና በመጓዝ ለጦርነት ጎዳና እምቢ፣ በተባባሪነትና በግብረ ሠናይ ጎዳና በመጓዝ ለስግብግብነት እምቢ ማለት መሆኑ አብራርተው፣ አደራ ስደተኞችን በማስተናገድ ሁሉም የተቀበለው የጌታ ፍቅር ይኑር እንዳሉ ኦንዳርዛ አስታወቁ።

እ.ኤ.አ. 16 ታህሳስ 2015 ዓ.ም. ረቡዓዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በአጸደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባቀረቡበት ዕለት ስደተኞች ወደ ኤውሮጳ ለመግባት በሚደረገው የሜዲትራኒያን የባህር ጉዞ ወቅት የተወለደው የሦስት ወር ሕፃንና ቤተሶቦቹ ጋር መገናኘታቸው አስታውሰው፣ ስንቱ በስደት ጉዞ ይወለዳል፣ አደራ ለስደተኛው ከመደገፍ እትቦዝኑ፣ ክርስትናን በፍቅር ኑሩ፣ ለስደተኛው ሕዝብ የምትሰጡት አገልግሎት አደራ በእምነትና በጋለ ስሜት ቀጥሉበት፣ ስለ ሌላው ስለ ባለንጀራ የሚያስብ ክርስትና እንኑር አደራ በማለት ለወጣቶቹ የለገሱት ምዕዳን እንዳጠቃለሉ ኦንዳርዛ ገለጡ።








All the contents on this site are copyrighted ©.