2015-12-11 15:01:00

ዜና ዕረፍት


በቦሊቪያ የሳንታ ክሩዝ ደ ላ ሲየራ ሰበካ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ኹልዮ ተራዛስ ሳንዶቫል እ.ኤ.አ. ታህሳስ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በ 79 ዓመት ዕድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የቦሊቪያ ሰበካ መግለጫ ሲያመልክት፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ለሳንታ ክሩዝ ደ ላ ሲየራ ሰበካ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ሰርጆ አልፍረዶ ጉኣልበርቲ ካላንድሪና የቴሌግራም የሐዘን መግለጫ መልእክት አስተላልፈዋል።

ቅዱስ አባታችን ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልእክት፦ በእምነት ብርሃንና በተስፋ ኃይል ለተቀበሉት ጥሪ ታማኝ በመሆን በቸርነትና በብርታት ሕይወታቸውን ለወንጌል ለፍትሕና ለሰላም አገልግሎት ያዋሉ በማለት እንደገለጡዋቸው ያመለከተው የቅድስት መንበር መግለጫ አክሎ፦ ነፍሰ ኄር ብፁዕ ካርዲናል ኹልዮ ተራዛስ ሳንዶቫል እ.ኤ.አ. መጋቢት 1936 ዓ.ም. በቫለግራንደ ክፍለ ሃገር የተወለዱና መላ ሕይወታቸው ስለ ድኾች በመጣበቅ የኖሩ ላልተመቻቸለት ድኻው የአገሪቱ ሕዝብ በተለያየ መስክ የሚበጀው አገልግሎት በማቅረብና በማስተባበር የተጉ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ሁለተኛ ብፁዕ ካርዲናል መሆናቸው ያስታውቃል።

የቅዱሰ ቅዱሳት መድኃኔዓለም ማኅበር አባል እ.ኤ.አ. ሐምሌ 29 ቀን 1962 ዓ.ም. የክህነት ማዕርግ ተቀብለው በቫለግራንደ ክልል የማኅበሩ ቤት አለቃ ከዛም በ 1978 ዓ.ም. በላ ፓዝ ሰበካ ረዳት ጳጳስ በመሆን በማገልገል ላይ እያሉ እ.ኤ.አ.  በ 1982 ዓ.ም. ጳጳስ እንዲሆኑ ተሰይመው በ 1991 ዓ.ም. የሳንታ ክሩስ ደ ላ ሲየራ ሊቀ ጳጳስ የቦሊቪያ ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ለረዥም ዓመታት ሊቀ መንበር በመሆን እንዲሁም ቸላም በሚል አሕጽሮት አቃል ለሚታወቀው ለመላ ላቲን አመሪካና ካሪቢያን ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት የዓለማውያን ምእመናን ጉዳይ ለሚከታተለው ድርገት ሊቀ መንበር በመሆን ያገለገሉ፣ በቦሊቪያ የውፉይ ሕይወት ጥሪ ያነቃቁ እ.ኤ.አ. በ 2001 ዓ.ም. በቅዱስ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብፁዕ ካርዲናል የተሰየሙ መሆናቸው የቅድስት መንበር መግለጫ ገልጦ፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ በቦሊቪያ ባካሄዱት ዓለም አቀፋዊ ሐዋርያዊ ዑደት ወቅትም ነፍሴ ኄር ብፁዕ ካርዲናል ለሕክምና ይገኙበት ወደ ነበረው ሕክምና ቤት በመሄድ እንደጐበኙዋቸው በማስታወስ ጠቅሶታል።








All the contents on this site are copyrighted ©.