2015-11-28 10:44:00

2ኛ ሰንበት ዘአስተምህሮ - ሎቱ ስብሓት ወአኰቴት


«...በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን…እርሱ ከጨለማ ስልጣን አዳነን፣ወደሚወደው ልጁ መንግስትም አሻገረን፡፡» (ቆላስይስ 1፡12-14 )

በዚህ በሐዋርያው መልዕክት አማካኝነት ስለተሰጠን እና ስለተቀበልነው፣እንዲሁም አሁን ሆነን ስላለነው ሁሉ እግዚአብሔርን እናመሰግን ዘንድ ተጋብዘናል፡፡ ሐዋርያው እግዚአብሔርን ከምናመሰግንበት ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹን እንዲህ ያስቀምጣቸዋል፡- የቅዱሳን ርስት ተካፋዮች ስደረገን፣የጻድቃን ጉባዔ አባላት እንድንሆን ስለመረጠንና ከነሱም ጋር ስለቆጠረን፣ከጨለማ ግዛት ነጥቆ ስላወጣን፣በውድ ልጁ ደም ስለዋጀንና የኃጢአትን ይቅርታ ስላገኘን፣ሁሉን ውብ ማደረግ ስለሚችል ስላደረገና ውብም እያደረገ ስለሆነ፣ወደ ዘለዓለማዊው መንግስት ስላሻገረን ወዘተ፡፡ ስለነዚህና ቁጥራቸው ስለበዛ ስጦታዎቹና በረከቶቹ እግዚአብሔርን ማመስገን የአማኝ ባህሪ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ስጦታ እና ሌሎችንም የተቀበለ ክርስቲያን ቃለ እግዚአብሔር እንደሚለው በሰጪው ፊት ምንም እንዳለተቀበለ ባዶ እጁን ይቀርብ ዘንድ ተገቢ አይደለም (ኦ. ዘዳ. 16፡16 ተመ.)፡፡

የእግዚአብሔር ዓላማ የእጁ ስራ የሆነው ሰው ከዘለዓለማዊ ሞት ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንዲሻገር ስለሆነ ዛሬ በተሰጠን ዕድልና ፀጋ ተጠቅመንና ሰርተንበት ሰማያዊ ቤታችንን፣ዘለዓለማዊ ማረፊያችንን እናዘጋጅ፣ከጨለማ አስተሳሰባችን እና ከጠማማ መንገዳችን ወጥተን ለእግዚአብሔር እንለይ፤ እግዚአብሔር በልጁ መስዋዕትነት ለያንዳንዳችን መዳን ዋጋ ከፍሏል፣በልጁ ደም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡ ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀው በውስጣዊ መታደስና በንስሐ ወደርሱ መመለስ ነው፤ ከዚህ በኋላ የሚጠፋ እና የሚባክን ጊዜ የለንም፤ የማዕዘኑ ድንጋይ ራስ በሆነው በክርስቶስ፣በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ እንታነጽ (ኤፌ. 2፡20)፡፡

ከጨለማው መንገዳችን መልሶ በልጁ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከራሱ ጋር ያስታረቀን አምላክ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ የተመሰገነ ይሁን፡፡ አሜን!

ሠላም ወሰናይ!

አባ ዳዊት ወርቁ

ዘማኅበረ ካፑቺን








All the contents on this site are copyrighted ©.