2015-09-23 19:13:00

ር.ሊ.ጳ በተባበሩት የአመሪካ መንግሥታት ቤተ መንግሥት


ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ እ.ኤ.አ. ከመስከረም 19 ቀን እስከ መስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በኩባና በተባበሩት የአመሪካ መንግሥታት የሚያካሂዱት አስረኛው ዓለም አቀፋዊ ሓዋርያዊ ዑደት አንደኛው ክፍል ትናንትና በሳንትያጎ ደ ኩባ በሚገኘው የእመቤታችን ፍቅርት ድንግል ዘኮብረ መካነ ንግደት ክዩባ የጥበቃዋ ጕልት መሆንዋን በ1916 ዓም ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 15ኛ ባወጁባት ስለክዩባ ሕዝብ ባሳረጉት ጸሎትና መሥዋዕተ ቅዳሴ ብሎም የሓዋርያዊ ጉዞአቸው አንኳር የሆነ የቤተሰብ ሳምንት በፊላደልፍያ ሲጀምር ካስተላለፉት የቪድዮ መልእክት ባሻገር በሳንትያጎ ደ ኩባ ካተድራል በብዙ ሺ ከሚቆጠሩ ቤተሰቦችና ልጆቻቸው ጋር በመገናኘት ሰፊ አስተምህሮ ሰጥተው ማምሻውን ወደ ተባበሩት አመሪካ በመጓዝ ተፈጸመ፣ 

በክዩባ ሓዋርያዊ ጕብኝት የህዝብዋና የአገሪቱ ቡራኬና ስለሕዝብዋና ስለአገሪቱ ለእመቤታችን ያሳረጉት ጸሎት አንዱ ሲሆን ቡራኬውን ያካሄዱት በኦልጊን ከተማ በሚገኘው የመስቀል ኮረብታ በሚገኘው በ1790 ዓም በፍርናቸስካውያን አለቃ በነበሩ የተተከለ ታላቅ መስቀል የሚገኝ ሲሆን ቦታውም ገዢ ቦታ ሆኖ መላዋን የክ ዩባ ደሴት ያሳያል፣ “በመስቀሉ ላይ አንድ ሰው አለምን ለመዳን ተሰቅለዋል እኛም በየዕለቱ መስቀላችንን ተሸክመን እንከተለው” የሚል መዝሙር በሕጻናት እየተዘመረ ቅዱስነታቸው ስለክ ዩባና ሕዝብዋ ጸልየው መላዋ ክ ዩባንና ሕዝብዋን ከኮረብታው ባርከዋል፣ የዚሁ ዓይነት ጸሎትና ቡራኬም ትናንትና በእመቤታችን የፍቅር ድንግል ዘኮብረ መካነንግደት በቦታው ባለው ልጅዋን ያቀፈች የእመቤታችን ምስል ሥር ሆነው እንዲህ ሲሉ ጸልየዋል፣

“የክዩባ ጠባቂና ጠበቃ የሆንሽው ፍቅርት ድንግል ዘኮብረ የክ ዩባን ሕዝብ እንድትጐበኚና በታሪኩ በሚያደርገው ጉዞ እንድትሸኚው እንደ ክ ዩባ እናትና ንግሥት መጣሽ፣ ስምሽን መልክሽ በአገር ውስጥና ውጭ በሚገኙ ክዩባውያን ልብና አእምሮ ተቀርጾ የተስፋና ወንድማማዊ አንድነት ምልክት ሆነዋል፣ ቤተሰቦቻቸውን እንድትከላከሊ ወጣቶቻቸውና ሕጻኖቻቸው እንድትረጂ ለሚሰቃዩም እንድታጽናኚ እንለምንሻለን፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የዕቅርና የሰላም እናት የሆንሽ እናታቸን ለዚሁ በመላው ዓለም ተበታትኖ ያለው የክ ዩባ ሕዝብ እንድትሰስቢ እንለምንሻለን! ክ ዩባ የወንድማሞችና የእኅትማሞች ቤት እንዲሆን አድርጊ! አንድያ የዓለም አዳኝ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ልጅሽ ልቡንና አ እምሮውን እንዲከፍት አድርጊ!” ሲሉ ጸሎት አሳርገዋል፣

ማምሻውን ክሳንትያጎ ደ ኩባ አለም አቀፍ አየር ማረፍያ ተነሥተው ከሶስት ሰዓት ተኵል በረራ በኋላ አንድሪው አየር ኃይል ማእከል ዋሺንግቶን ዲሲ በደረሱበት ግዜ የተባበሩት መንግሥታት አመሪካ ፕረሲደንት ባራክ ኦባማ ከባለቤቱ ሚሸልና ሁለት ልጆቹ የዋሽንግተን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዶናልድ የሚግኙባቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትና የቤተ ክርስትያን መሪዎች ከሕዝብ ጋር የግል አቀባበል አድርገውላቸዋል፣

በዛሬው ዕለት በዋሽንግቶን ዲሲ ሰዓት አቆጣጠር ጥዋት ሶስት ሰዓት ላይ ወደ ዋይት ሃውስ የተባበሩት የአመሪካ መግሥታት ቤተመንግሥት ተግኝተው ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፣

በተለያዩ ሰልፎች ከተቀበልዋቸው በኋላ የቅድስት መንበርና የተባበሩት የአመሪካ መንግሥታት አገራዊ መዝሙሮች ተዘመሩ፣ ፕረሲደንት ባራክ ኦባማ  የሚከተለውን የእንኳን ደህና መጡ ንግግር አድርገዋል፣

“እንደምን ኣደራችሁ! ዛቲ ዕለት እንተገብረ እግዚኣብሔር ንትፌሳሕ ወንትሓሰይ ባቲ የሚለውን የመዝሙረ ዳዊት ቃል በመድገም እግዚኣብሔር ምን ያህል መልካም ቀን ሰጠን! ካሉ በኋላ ወደ ቅዱስነታቸው ዞር በማለት .. ቅዱስ ኣባታችን በሚሸል ስምና በስሜ ወደዚሁ ቤተመንሥት አንኳን ደህና መጡ፣ ጓዳችን እንዲህ በሰው ኣጥለቅልቆ ኣያቅም፣  የዛሬው ስብሰባ ብዛትና መንፈስ ግን ከ70 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ የኣመሪካ ካቶሊካውያን ምኑን ያህል በጥልቅ እንደሚያከብርዋችሁ የሚያሳይ ነው፣ እንዲሁም የፍቅርና የተስፋ መልእክትዎ በኣገራችንና በመላው ዓለም ምን ያህል እንደተስፋፋ ያመለክታል፣ በኣሜርካ ሕዝብ ስም ወደ ተባበሩት የኣመሪካ መንግሥታት አንኳን ደህና መጡ ስል የሚሰማኝ ክብርና ደስታ ወሰን የለውም፣ በዛሬው ዕለት ብዙ ለመጀመርያ ግዜ በማለት የምንገልጻቸው ፍጻሜዎች ኣሉ፣ ቅዱስነትዎ እንደ የመጀመርያ የኣሜሪካዎች ር.ሊ.ጳ ተሹመዋል; የተባበሩት መንግሥታት ኣመሪካን ስትጎበኙ የመጀመርያችሁ ነው፣ በትዊተር የር.ሊ.ጳ ሓዋርያዊ መልእክት የዘረጉም የመጀመርያ እርስዎ ነው፣

ቅዱስ ኣባታችን! ኣነስ ባለ መንገድም ቢሆን የእርስዎ ጉብኝት ኣምና በቫቲካን ላደረጉልኝ ታላቅ ኣቀባበል ለመካካስ ያስችለኛል, በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ የእምነት ዘርፎችና ታሪክ ያላቸው ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ኣመሪካን ለማጐልበት የምታደርገውን ኣስተዋጽኦ ታላቅ ግምት እንደሚሰጡትም ያመለክታል፣ በቺካጎ በደሀዩ ኣከባቢዎች መሥራት ከጀመርኩበት ግዜ አስከ ፕረሲደንት ሆኜ በተለያዩ ቦታ በተጓዝኩት በየቀኑ ካቶሊካውያን ማኅበራት ካህናት ደናግልና ምእመናን የተራበውን ሲመግቡ የታመመውን ሲፈውሱ ለቤተኣልባ መጠጊያ ሲሰጡ ልጆቻችን ሲያስተምሩ ብዙ ሰዎችን የሚረዳ እምነትን ሲያጠነክሩ እንዳየ ምስክርነቴን እሰጣለሁ፣ በኣጠቃላይ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን በመላው ዓለም የምታበረክተውን ከገለጡና ካመሰገኑ በተለይ ደግሞ ቅዱስነታቸው ለየት ባለ መንገድ ር.ሊ.ጳ ሆነው ከተመረጡ ወዲህ የካቶሊካውያንም ይሁን የመላው ዓለም ትኩረት በመሳብ ሕያው የኢየሱስ ክርስት ትምህርት ምሳሌ አንደሆኑና ሞራላዊ ሥልጥእናቸው በቃላት ሳይሆን በተግባር እንዳሳዩን ገለጠዋል፣ ጥሪኣቸው ለሁሉም ግልጽ መሆኑንም ኣልሸሸጉም፣

ለካቶሊኮችም ይሁን ካቶሊኮች ላልሆኑ ሁላችንን ለታናሹ ትኩረት እንድንሰጥ ለሁላችን ጥሪ እያቀረባችሁ ነው፣ እንደግለሰዎችም ይሁን እንደማኅበረሰብ በእግዚኣብሔር ዓይን ፊት የምንፈረድበት በሃብት በሥልጣን ወይንም በስመ ገናናነት ሳይሆን ድሃውንና የተገለለውን ለመርዳት ቃለ ወንጌሉን ምን ያህል እተግባር እንዳዋልነውና ስለፍትሕ የቆምነው እንዲሁም ሁላችን በእግዚኣብሔር መልክ የተፈጠርን ስለሆነም የእያንዳንዱ እኩልነትና መብት የተጠበቀ እንዲሆን ምን እንዳበረከትን እንደምንጠየቅ ታሳስቡናላችሁ፣ የእግዚኣብሔር ኃይለኛው መልእክት ምሕረት መሆኑንም ትነግሩናላችሁ፣ ይህም ስደተኛውን የተቸገረውን በእውነተኛ ፍቅርና እውነት በተከፈተ ልብ እንድንቀበል ትጠሩናላችሁ፣ የጦርነት ዋጋ በተለይ ደግሞ ኃይልና መከላከያ ለሌለው እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን አንድናስታውስና ሁላችን ለሰላም እንድንታገል የምትሰጡን ትምህርት ታላቅ ነው በማለት ስለኣጠቃላይ ትምህርታቸው ከተናገሩ በኋላ በተለይ ለኣሜሪካና ለክዩባ ሕዝብ ቅርበት ያደርጉት ጥረትም ኣመስግነው ስለኣጠቃላይ የሃይማኖት ነጻነትና ቅዱስነታቸው በቅርቡ ስለጻፉት ላውዳቶሲ ኣከባቢን የሚመለከት ሓዋርያዊ መልእክት በማመስገን ንግግራቸውን ደምድመዋል፣

ፕረሲደንት ባራክ ኦባማ ንግግራቸውን ከጨረሹ በኋላ ቅዱስነታቸው ሰላምታ አቅርበው የሚከተለውን ንግግር አቅርበዋል፣

“ክቡር ፕሬሲደንት፡ - በመላው አሜሪካዊያን ስም ስላደረጉልኝ አቀባበል እጅግ አመሰግናለሁኝ። እኔ የስደተኛ ቤተሰብ ልጅ በመሆኔ እንዲሁ በዚህች አገር በተባበሩት የአሜሪካ መንግስታት በተለያዩ ስደተኞችና ቤተሰቦች የተመሰረተችና የተገነባች ሃገር እንግዳ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ። በዚሁ ሃገር በማደርገው ቆይታ በደስታ ሲሆን ስብሰባዎች በሚካሄዱበትም ቦታዎች የአሜሪካን ሕዝብ ምኞትና ተስፋን ለማዳመጥና ለመካፈል ነው።

በዚህ ጉብኝት በሃገሪቱ ምክር ቤት በመገኘት ሃገሪቱን ለመምራትና ለማስተዳደር የተጠሩበትን የሃገሪቱን መሰረታዊ ሕግ መመሪያ የታማኝነት ኅላፊነት እንዳይዘነጉ ለማበረታታት እወዳለሁኝ።  

ወደ ፊላደልፊያም በመቀጠል 8ኛው አለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉና የሚከበረው ጉባኤ የቤተሰብን መሰረት ጥምረት ለማክበርና በተለይም ባሁን ወቅት በሕብረተሰባችን ታሪክ ቤተሰብ የሚለው ቃል ለመቀየር ያለው አመለካከት አስጊነትን ለማሳሰብ ነው።

የተከበሩ ፕሬሲደንት ካቶሊካዊያን አሜሪካኖች ከሃገራቸው ዜጎች ጋር ማኅበረሰባቸውን ለመገንባት የእያንዳንዱን ያገር ዜጋ ሕግ ለማክበርና ለማስከበር ዘረኝነትና ኢ-ፍትሐዊነትን ለማስወገድ እንዲሁም የሃገራቸውን ዴሞክራሲ ለማስከበር ከሌላ የመልካም ፈቃድና ተግባር ሰዎች ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ገልጠዋል። የአንድ ሃገርና ማኅበረሰብ ሰላምና ነፃነት ለማስከበር ከተፈለገ የመጀመሪያው የሃይማኖት ነፃነት አስፈላጊነት በማስገንዘብ ይህም ነፃነት የአሜሪካ ድል መሆኑን አስታውቀዋል። በዚሁ በተባበሩት የአሜሪካ መንግስታት የሚገኙት ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ወንድሞቼ የሚያስታውሱኝ ሁላችንም የተጠራነው ነፃነታችንን ለመጠበቅና ለማስከበር ነው። ነፃነታችንን ለመቀማት ከሚደርስብን የተለያዩ ዛቻዎችም ነፃነታችንን ለማስከበር መከላከሉ አስፈላጊነቱን ገልጠዋል።

በማያያዝም ቅዱስነታቸው ለፕሬሲደንት ኦባማ የተፈጥሮን አየር ንብረት ለመጠበቅ የአየር ብከላ ተጠያቂ የሆኑትን ለመቀነስ የጀመሩትን ቅስቀሳ አመስግነዋል። ይህ ችግር የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ለመጪው ትውልድ መተው አንችልም ብለዋል። ታሪክ ለምንኖርባት እናት መሬት ለጋራ ጥቅም እንድንከባከባት በሕብረት እንድንሰራ ይጠራናል። ለዚህም የስራ ውጤትና እድገት ለውጥ ለማስገኘትና ለመጋፈጥ ወቅትና ሰዓቱ አሁን ነው። ውዳሴ ለእግዚአብሔር ይሁን ቁ13 ባቀረቡት ትምህርተ ክርስቶስ ጽሑፋቸውን በመጥቀስ የተፈጥሮ አየር መበከል ያስከተለውን ችግር ለልጆቻችን ብቻ ሳይሆን በበዙ ሚልየን የሚቆጠሩ ሰዎች ከማሕበራዊው የአሰራር ስርዓት ዘዴ ግዴለሽነት ተጠቅተዋል። መሬት እናታችን የዚህ ሰዎች ዋይታና ጩኸት ተካፋይ ስትሆን ዛሬ እነዚህ ሰዎች በራችንን ከተሞቻችንን በኅይል ሲያንኳኩ እንመለከታለን።

የአስተዋዩን የተከበሩት የማርቲን ሉተር ኪንግ ቃላት በመውሰድ በአንዳንድ ስራዎች የሚጠበቅብንን አላሟላንም አሁን ግን ለሟሟላትና ለማስከበር የምንጠቀምበት ግዜ ነው።

በእምነታችን እንደምናውቀው እግዚአብሔር አባታችንን እንዲሁ አይተወንም በኛ ላይ ያለውን የፍቅር ኅሳብ አይለውጥም ስለፈጠረንም አይጸጸትም።

የሰው ልጅ በጋራ ለሚኖርባት መሬት ለመገንባትና ለመስራት ለጋራ ለምንኖርባት መሬት ተባብሮ ለመገንባትና ለመስራት ችሎታ አለው።

በመጨረሻም ለዘመናት በሁለት አገሮች ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት እንዳስ ተጀምሮ በሕብረት ለመስራት የተደረገው ጥረት በማንኛውንም ማኅበራዊ ቤተሰብ ለእርቅ ለፍትሕና ነፃነት መንገድ መልካምና ጠቃሚ ዓርዓያ ነው። ምኞቴ በዚህች የበለጸገች ሃገር የሚኖሩ ጥሩ ልቦና መልካም ፈቃድ ሰዎች በከተማቸውም ይሁን ባለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙትን ድሆችና በችግር ምክንያትም ከማኅበረሰቡ ተገለው የሚኖሩትን እንዲከባከቡና ግድ እንዲላቸው እንዲሁም ክርስቶስ ለሁሉም ልጆቹ የሚሻውን በረከትና ሰላም እንዲያውቁ የአደራን ጥሪ በማቅረብ ክቡር ፕሬሲደንት ኦባማን ስላደረጉላቸው አቀባበል በማመስገን እግዚብሔር አሜሪካን ይባርክ” ሲሉ ቅዱስ አባታችን ፍራንቼስኮስ ንግግራቸውን ፈጽመዋል።

ከዚህ በኋላ ቅዱስነታቸው በቀጥታ በዋሽንግቶን ዲሲ በሚገኘው የቅዱስ ማቴዎስ ካተድራል ተጉዘው ከተባበሩት የአመሪካ መንግሥታት ጳጳሳት ተገናኝተው አሁን ፕሮግራማችን በሚተላለፍበት ሰዓት እየተወያዩ መሆናቸው ተገለጠ፣ 








All the contents on this site are copyrighted ©.