2015-09-21 16:04:00

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ በኵባ፦ ነጻነት ሰላምና ተስፋ


ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ኩባ በሚገኘው ዓለም አቀፋዊ ኾሰ ማርቲ ደላ ሃባና ያየር ማረፊያ እንደደረሱ በአገሪቱ ርእሰ ብሔር ራውል ካስትሮ አቀባበል ተደርጎላቸው የእንኳን ደህና መጡ ሥነ ሥርዓት በሁለቱ አገሮች ብሔራዊ መዝሙር ተደምጦ እንዳበቃም፣ ቅዱስነታቸው ባስደመጡት መልእክት በኩባና ከኵባ ውጭ ለሚገኙት ለሁሉም የአገሩቱ ዜጋ ሰላምታ በማቅረብ ለፊደል ካስትሮ የከበረ ሰላምታ በርእሰ ብሔር ራውል ካስትሮ በኩል ይድረስ ብለው፣ ከዚሁ ጋር በማያያዝም ሰማንያ ዓመት እያስቆጠረ ያለው በቅድስት መንበርና በኵባ መካከል የጸናው ክሌአዊ ግኑኝነት አስታውሰው፣ የሳቸው ሐዋርያዊ ዑደት በኵባ ከሳቸው በፊት ቅዱስ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በመቀጠልም ቅዱስነታቸው ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ የፈጸሙት ዓለም አቀፋዊ ሐዋርያዊ ዑደት ዱካ ያደረገ መሆኑም ሲገልጡ፦ “ቤተ ክርስቲያን የኵባ ሕዝብ በተስፋውና በሚያሳስበው ሁሉ፣ ባላት መገልገያ መሣሪያ አማካኝነት በነጻነት በአገሪቱ የህልውና ጥጋ ጥግ ደረስ የእግዚአብሔር መንግሥት በማወጅ እንደምትሸኘው አረጋግጣለሁ” እንዳሉ የቅድስት መንበር መግለጫ አመለከተ።

ይኽ ሐዋርያዊ ዑደት ነጻና ልዑላዊት አገረ ኵባ ለመገንባት የአገሪቱ አበው የተማጠንዋት የፍቅር እመቤተ ዘ ኮብረ የኵባ ቅድስት ጠባቂ ተብላ የታወጀችበት ዝክረ 100ኛው ዓመት ከሚከበርበት ወቅት ጋር የተገናኘ መሆኑ አስታውሰው የኢየሱስ እናት በእያንዳንዱ የኵባ ዜጋ ልብ ውስጥ ኅልው መሆንዋ ገልጠው እያንዳንዱ በከፋ ችግር በሚገኝበት ወቅት ክብሩን እንድታቅብለትና የእያንዳንዱ ሰው ክብር የሆነውን ሁሉ ታነቃቃ በማለት በዚህ በሚያካሂዱት ሐዋርያዊ ዑደት አጋጣሚም ስለ ሁሉም የኩባ ልጆች ለመማጠን ያች እጅግ ለተፈቀረቸው አገረ ኵባ በፍትህ በሰላም በነጻነትና በእርቅ ጐዳና ትጓዝ ዘንድ ለመጸለይ እንደ የማርያም ልጅና እንደ መንፈሳዊ ነጋዲ ወደ ዘኮብረ ቅዱስ ሥፍራ እንደሚሄዱም ገልጠዋል።

የኩባ ጥሪ ሁሉም ሕዝቦች በወዳጅነት እንዲገናኙ የሚያደርግ አገናኝ ድልድይ መሆን ነው የሚለው የአገሪቱ የነጻነት አበው በክርስትናው እምነትና ባህል እጅግ የተካነው ኾሰ ማርቲ የገለጠው ሃሳብ ጠቅሰው፣ ቅዱስ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.ኤ.አ. በ 1998 ዓ.ም. በኩባ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባካሄዱበት ወቅት ኩባ ባላት ሊደነቅ በሚቻል ሁሉ ለዓለም ክፍት እንድትሆን ዓለምም በበኵሉ ለኩባ ክፍት እንዲሆን በማለት የገለጡት ሃሳብ አስታውሰው፦ ሁላችን ይኽው በሕዝቦች መካከል ከረዥን የመራራቅ ዓመታት ወዲህ ተስፋ የተጣለበት እየተረጋገጠ ላለው የመልካም ግኑኝነትና ስምምነቶች የቅርብ ምስክሮች ነን፣ ይኽ ደግሞ የግኑኝነት የጋራ ውይይት ዘወትር በሞት በዘርኝነት በወገጋኝነት አግባብ  ላይ  ኵላውዊነት አቢይ ግምት የሚሰጥ ባህል አሸናፊ (ኾሰ ማርቲ) መሆኑ የሚያረጋጋጥ ነው።

ቅዱስነታቸው የፖለቲካ የበላይ አካላት ሰላምና የሕዝቦቻቸውን የጋራው ጥቅም የሚያነቃቁ የመላ ላቲን ዓመሪካ በጠቅላላው ዓለም የእርቅ መሣሪያ ለመሆኑ ያንን የኾሴ ማራቲ ቃል የሚከተሉ እንዲሆኑ በማበረታታት፣ ዓለም በዚህ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት መሳይ ሁነት በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት የእርቅ አርአያ የሆኑትን ይሻል እንዳሉ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታወቀ።

የኵባው ርእሰ ብሔር ራውል ካስትሮ በበኩላቸውም ልባዊ የእንኳን ደህና መጡ ቃል ሲያስደምጡ፣ ቅዱስነታቸው ላስደመጡት ንግግር የተሰማቸው አድናቆት በማስተጋባት፣ በተለይ ደግሞ ፍትህና ስለ ምኅዳር እንክብካቤ ያሉትን ሃሳብ ጠቅሰው የምንኖርበት ዓለም መዋዕለ ንዋይነት ለዓለማዊ ትሥሥር መሠረት እንዲሆን ገንዘብ ጣዖት የሚያደርግ ባህል ተገዥ በሆነበት ወቅት የኵባው ማኅበራዊነት ስልት በተለይ ደግሞ በጤና ጥበቃ በሕንጸት ዘርፍ በጠቅላላ ለኤኮኖሚውና ለማኅበራዊው ሥልት መርህ የሚያደርግ የኵባው ማኅብራዊነት የላቀ ነው በማለት ተበቅለው፣ ከዚሁ ጋር በማያያዝም ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ በኩባና በተባበሩት የአመሪካ መንግሥታት መካከል ለምልካም ግኑኝነት ጅማሬ የሰጡት አቢይ አስተዋጽዖ በአድናቆት አመስግነው፣ የተባበሩት የአመሪካ መንግሥታት በኵባ ላይ የደነገገው ረዥም ዓመታት እያስቆጠረ ያለው ጨካኝ ኢግብረ ገባዊና ሕገ ወጥ ተግባር በማለት የገለጡት የኤኮኖሚ ማዕቀብ እንዲያበቃለት ጥሪ አስተላልፈው፣ በመጨረሻም የተባበሩት የአመሪካ መንግሥታት ለአገሪቱ ባሕር ኃይል ወታደራዊ ሠፈር በማድረግ የሚቆጣጠረው የጓንታናሞ ደሴት የኵባ መሬት በመሆኑ፣ ለኩባ ይረከብ ዘንድ ጥሪ በማቅረብ ያስደመጡት የእንኳን ደህና መጡ መልእክታቸው እንዳጠናቀቁም የቅድስት መንበር መግለጫ አስታወቀ።








All the contents on this site are copyrighted ©.