2015-07-24 14:54:00

ብፁዕ ካርዲናል ፊሎኒ፦ በኢራቅ የምትገኘው ሰማእት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጀግንነት


የአስፍሆተ ወንጌል ለአሕዛብ ተንከባካቢ ቅዱስ ማኅበር ኅየንተ ብፁዕ ካርዲናል ፈርናንዶ ፊሎኒ ቤተ ክርስቲያን በኢራቅ በሚል ርእስ ሥር በኢራቅ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከመባቻ እስካለንበት እድገትና ተልእኮ የሚያወሳ የደረሱት መጽሓፍ ለንባብ መብቃቱ ሲገለጥ፣ በኢራቅ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስነታቸው ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ጀብደኛ ቤተ ክርስቲያን በማለት የገለጡዋትና ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ለዚያች በአሁን ወቅት  በአገረ እስላም ጅሃዳውያን አማካኝነት በሚደርስባት ስደትና መከራ ሳትበገር የምትሰጠው ኅያው የእምነት ምስክርነት በማጽናናት ተጨባጭ ቅርበት በማረጋገጥ ዘወትር በጸሎት ቅርብ በመሆን ሰማዕት ቤተ ክርስቲያን በማለት የሰጡዋት መግለጫ የሚመስከር መጽሓፍ መሆኑ ብፁዕ ካሪዲናል ፊሎኒ መጽሐፉን አስደግፈው ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ገልጠዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፊሎኒ በኢራቅ በጋልፍ ጦርነት ወቅት ለአምስት ዓመት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ወኪል ሆነው እንዳገለገሉና ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ የኵላዊት ቤተ ክርስቲያን መንበረ ቅዱስ ጴጥሮስ በኢራቅ ለምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለስቃይና ለመከራ ለተዳረገው ሕዝብ ቅርብ መሆንዋ ለማረጋገጥም የኢራቅ ስደተኞችና ተፈናቃዮችን እንዲጎበኙ ሁለቴ ወደ ኢራቅ ለሐዋርያዊ ኡደተ እንደላኩዋቸው አስታውሰው፣ በኢራቅ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ኅያው ነች፣ የኢራቅ ማኅበረ ክርስቲያን የአገሪቱ ውሁዳን የኅብረተሰብ ክፍል ነው። ከሌሎች በአገሪቱ ከሚገኙት ውሁዳን የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጦ የሚገኝ ድኽነት የምትኖር ቤተ ክርስቲያን አባል ነው። ቤቱንና ንብረቱን አጥቶ ለስደትና ለመፈናቀል አደጋ ተጋልጦ በአገረ እስላማዊ ጅሃዳውያን አማካኝነት ከሚኖርበት ክልል ተባሮ በኩርድስታን ክልል መጠለያ አግኝቶ ወደ ሚኖርበት ሥፍራ በቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍላጎት መሠረት ተልእከው ሐዋርያዊ ጉብኝት በመፈጸም ያዩት ሁነት ጭምር የሚያወሳ መጽሓፍ ነው ብለዋል።

ማኅበረ ክርስቲያን በገፍ ለስደትና ለመፈናቀል አደጋ የተጋለጠው ሲሆን፣ እስላማዊ አገር ጅሃዳዊው ኃይል የሚያረማምደው አክራሪው የምስልምና ሃይማኖት ተግባር የማይደግፉ የምስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ኢራቃውያንና ሌሎች የምስልምና ተከታይ ያልሆኑትን ውሁዳን የኅብረተሰብ ክፍል ጭምር ለተመሳሳይ አደጋ ተጋልጦ ይገኛል። ለሞት የተዳረገው የቤተሰብ አባላቱንም ጭምር የሚያጣው የአገሪቱ ዜጋ ብዙ ነው።

ጉብኝት ባካሄዱበት ወቅት ለስደት የተዳረገው ማኅበረ ክርስቲያን ያጠቃለለ የአገሪቱ ውሁዳን የኅብረተሰብ ክፍል ቤቱንና ንብረቱን ጥሎ በእግር በመጓዝ መጠለያይ ለማግኘት ወደ ተሰደደበት ክልል ድረስ በመሄድ የቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በእምነት የማጽናት መልእክት አስተላልፈው ተጨባጭ ድጋፍ በማቅረባቸውና እ.ኤ.አ. በ 2015 ዓ.ም. በሕማማትና በበዓለ ፋሲካ ወቅት ለተመሳሳይ ጉብኝት ዳግም ወደ ኢራቅ መላካቸውንም ገልጠው፣ የተፈናቀለውና የተሰደደው የኢራቅ ውሁዳን የኅብረተሰብ ክፍል ለብቻው እንዳልሆነ ቤት ክርስቲያን ለዚያ የጌታ ህማማት በሱታፌ ለሚኖረው ሕዝብ ቅርብ በመሆን ህማማቱን አብራ በመካፈል፣ በአሁኑ ወቅት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህማማት በሕይወቱ ለሚመሰክረው ሁሉ ያላት ቅርበት እንደ መሰከሩም ገልጠው። ያካሄዱት ሐዋርያዊ ጉብኝት መንፈሳዊ ንግደት በማለት እንደሰየሙት ገልጠው፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ለኢራቅ ድጋፍና ትብብር የዓለም ማኅበረሰብ ኅሊና በማነቃቃት ሁሉም ማኅበረ ክርስቲያን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይና መከራ በተጨባጭ ተካፋይ ለሆነው ማኅበረ ክርስቲያን ቅርብ በመሆን ቅርበቱን እንዲያረጋግጥ በተለያየ ወቅት ስለ ኢራቅ በተመለከተ በሚያስተላልፉት መልእክት ጥሪ አቅርበዋል።

በደረሱት መጽሐፍ በኢራቅ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የኢራቅ ታሪክ ባህል ተካፋይ ብቻ ሳትሆን ለዚያች አገር ታሪክና ባህል መሠረትና እድገት ከሆኑት ውስጥ የምተጠቀስ መሆንዋ በስፋት በማረጋገጥ፣ ማኅበረ ክርስቲያን የመካከለኛው ምስራቅ ታሪክና ባህል ተሟይ ክፍልና አለ ማኅበረ ክርስቲያን የመካከለኛው ምስራቅ ታሪካና ባህል ምን ተመስለው ለመገመቱ የሚያዳግት መሆኑና በዚያ ክልል የማኅበረ ክርስቲያኑ ታሪክ ሁለት ሺሕ ዓመታት እንዳስቆጠረ የሚያረጋገጠው ታሪካዊ አመክንዮውን በጥልቀት ያብራሩበት መጽሐፍ እንደሆነም ገልጠዋል።

በኢራቅ የሚገኘው ማኅበረ ክርስቲያን ጥንታዊው የኢራቅ ተወላጅ ነው። ታሪክ የሚመሰክረው እውነትም ነው። የኢራቅ ሕዝብ ጭምር የሚመሰክረው ነው። ሆኖም ጂሃዳውያን ይኸንን እውነት ለመካድና የኢራቅ ታሪክ ጂሃዳዊው የሚከተለው ርእዮተ ዓለም መሠረት በማድረግ ለመጻፍ የሚከተሉት መንገድ ከእውነት የራቀ ነው። ይኸንን እውነት ጅሃዳውያን ጭምር ጠንቅቀው የሚያውቁት ነው። የመካከለኛው ምስራቅ ባህል ለምዕራቡ ዓለም ባህል ጭምር መሠረት ነው። ይኸንን ሁሉ ሃሳብም በደረሱት መጽሐፍ በስፋት እንዳብራሩት አስታውቀዋል።

የኦታማን ግዛት መውደቅ በመካከለኛው ምስራቅ የነበረው አንዳዊ ግዛት አብቅቶለት ዮርዳኖስ ሶሪያ ሊባኖስ ቱርክ ጭምር እንደ ሉኣላውያን አገር ሆነው የጸኑበት ታሪክ ከአንድ ዘመን በላይ ያለበለጠ ዕድሜ ነው ያለው፣ በ 1920 ዓ.ም. በኤውሮጳ የኦታማን መንግሥት መካፋፈል በታየበት ወቅት የዮርዳኖስ የኢራቅ የሳውዲ አረቢያና የቱርክ ግዛቶች እንደተመሠረቱ አስታውሰው በመካከለኛው ምስራቅ የአገር አድነት የሚለው ተጨባጭ የአንድ አገር መለያ ሆኖ የተረጋገጠበት ታሪክ የቅርብ ነው። የተረጋገጠው አገራዊ መልክአ ምድር የዚያ ክልል ሕዝብ ፍላጎት ያልተከተለ የምዕራቡ ዓለም ፍላጎት የተከተለ ነው። እንደ አብነትም የኩዋይት ጦርነት ጠቅሰው ይኽ ታሪካዊ ሁኔታ ጥሎት ያለፈው አለ መግባባት እስካሁን ድረስ መፍትሄ አላገኘም፣ የኩርድ ጥያቄም ከዚህ የመነጨ ነው። በሺዒዎችና በሱኒዎች መካከል የሚታየው ውጥረት የያዚዶች ጉዳይም እንደዚሁ። ስለዚህ ይኽ በጎሳና በሃይማኖት የተለያየው የኢራቅ ሕዝብ ተግባብቶ በመቀባበልና በመከባበር መኖር ብቻ ነው በሰላም እንዲኖር የሚያደርገው። ሃይማኖታዊና ጎሳዊ የአምባገነን ሥርዓት የሚል አመለካክት ለማጥፋት የውይይት ባህል መስፋፋት ወሳኝ መሆኑ በደረሱት መጽሓፍ እንዳሰመሩበት ገልጠው ያካሄዱት ቃለ ምልልስ አጠቃለዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.