2015-06-08 16:27:00

የቨነዝዋላ ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ጥሪ


ብፁዕ አቡነ ዲየጎ ፓድሮን የቨነዝዋላ ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ሊቀ መንበር የቨነዝዋላ መንግሥስት የአገሪቱ የፖለቲካ እስረኞችና በፖሊቲካ ምክንያት ከአገራቸው ተሰደው የሚኖሩትን ጭምር ምኅረት የሚያሰጥ ውሳኔ እንዲያጸድቅ እ.ኤ.አ. ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. የፖለቲካ እስረኞች ምኅረት ተደርጎላቸው ነጻ እንዲለቀቁ ለመንግሥታቸው ለመጠየቅ እያካሄዱት ባለው ምግብ የማቆም አድማ በመተባበር ላይ ከሚገኘው ከቨነዝዋላ የወጣቶች አንድነት ማኅበር ተጠሪዎች ጋር ግኑኝነት ባካሄዱበት ወቅት ጥሪ ማቅረባቸው ሲገለጥ፣ ብፁዕ አቡነ ፓድሮን እስረኞችና የእስረኞች ቤተሰቦች እንዲሁም የእስረኞቹ ጠበቃ ለዮፖልዶ ሎፐዝ ዳኔል ካባሎስና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ሰብአዊ መብትና ክብር ጥበቃ ተሟጋች ማኅበር አባላት ጋር በመሆን ይኸው 15 ቀናት ያስቆጠረው መግብ የማቆም አድማ አሳሳቢ ከመሆኑም ባሻገር ብዙዎቹ ለሞት አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉም ገልጠው፣ መንግሥት ሁኔታው ግምት በመስጠት አወንታዊ ምላሽ እንዲሰጥበት ጥሪ ማቅረባቸው የቨነዝዋላ ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ያሰራጨው መግለጫ ይጠቁማል።

በቅድስት መንበር የቨንዝዋላ ርእሰ ብሔር ማዱሮ ጉብኝት

የቨነዝዋላ ርእሰ ብሔር ኒኮላስ ማዱሮ በአገረ ቫቲካን ያካሄዱት ጉብኝትና ከቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ጋር ያካሄዱት ግኑኝነት አወንታዊ ውጤት እንደሚያስገኝ በቨነዝዋላ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተስፋ እንዳላት የቨነዝዋላ ኤል ናሲዮናል የተሰየመው ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱት ብፁዕ አቡነ ፓድሮን ገልጠዋል። የብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ድርገት የአገሪቱ መንግሥት የእስረኞች ሰብአዊ መብትና ክብር እንዲያከብር ባወጣው መግለጫ ጥሪ ማስተላለፉም የብፁዓን ጳጳሳቱ ምክር ቤት መግለጫ ይጠቁማል።

በቨነዝዋላ የፖሊቲካ እስረኞች ሰብአዊ መብትና ክብር ረገጣ እንደሚታይ የገለጠው የብፁዓን ጳጳሳቱ ምክር ቤት መግለጫ አክሎ፣ እስረኛ የካራካስ የቀድሞ ከንቲባ ዳኔል ቸባሎስ እ.ኤ.አ. ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ከነበሩበት ውህኒ ቤት ከካራካስ 150 ኪ.ሜ. ርቆ ወደ ሚገኘው ወህኒ ቤት መዛወራቸው እጅግ አሳሳቢ መሆኑ በማብራራት፣ በወህኒ ቤት የሚታየው የሰብአዊ መብትና ክብር ረገጣ የወህኒ ቤቶች ሁኔታ ሰብአዊ ልክነት የሌለው መሆኑም እንደሚያረጋግጥ የብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት መግለጫ ሲያመለክት፣ የቨነዝዋላ ብፁዓን ጳጳሳት የእስረኛ ሰብአዊ መብትና ክብር እንዲከበር ጥሪ በማስተላለፍ፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በቨነዝዋላ ያለው ውጥረት እልባት እንዲያገኝ ይገላግሉም ዘንድ ጥሪ ማስተላለፋቸውም ያመለክታል።
All the contents on this site are copyrighted ©.