2015-06-05 15:49:00

የኤውሮጳ የምስራቅ ሥርዓት የሚከተሉት የካቶሊክ አቢያተ ክርስቲያን ጉባኤ


የመላ ኤውሮጳ የምስራቅ ሥርዓት ተከታይ ካቶሊካውያን አቢያተ ክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ዓውደ ጉባኤ በረፓብሊካዊት ቸክ ርእሰ ከተማ ፕራግ እ.ኤ.አ. ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. መጀመሩ የመላ ኤውሮጳ አገሮች የብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤቶች ኅብረት ያሰራጨው መግለጫ የጠቀሰው ሲር የዜና አገልግሎት አስታወቀ።

ይኽ እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚዘለቀው የመላ ኤውሮጳ የምሥራቅ ሥርዓት ተከታይ ካቶሊካውያን አቢያተ ክርስቲያን ዓመታዊው ዓውደ ጉባኤ በጠቅላላ 14 አቢያተ ክርስቲያን ያሳተፈ መሆኑ የገለጠው ሲር የዜና አገልግሎት አክሎ የዓውደ ጉባኤው ዋናው ርእስ እ.ኤ.አ. በ 2015 ዓ.ም. በኵላዊት ቤተ ክርስቲያን ሊካሄድ ተወስኖ ያለው ቤተሰብ ዙሪያ የሚመክረው ሲኖድስ ምክንያት በማድረግ ቤተሰብ በኤውሮጳና በኤውሮጳ በምስራቅ ሥርዓት በሚከተሉት አቢያተ ክርስቲያን ያለው ተልእኮ የሚል መሆኑ አስታውቀዋል።

የዓውደ ጉባኤ የመጀመሪያው የውይይት ነጥብ ወቅታዊው ቤተሰብ በኤውሮጳ በሚል ርእስ ሥር የረፓብሊካዊት ቸክ ዜጋ የቢዛንታይን ሥርዓት ለምትከተለው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በቸክ ዲያቆን ያሮስላቭ ማዝ ካስፓሩ ያጠናቀሩት የጥናት ሰነድ ሲሆን፣ ሁለተኛው የውይይቱ ርእስ የቤተሰብ ቅዱስ ምጢራዊ እምቅ ኃይል በሚል ርእስ ሥር በኡክራይን የግሪክ ሥርዓት ለምትከተለው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካህን አባ ቮሎድይምይር ሎስ ባቀረቡት የጥናት ሰነድ ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን የገለጠው ሲር የዜና አገልግሎት አያይዞ በረፓብሊካዊት ቸክ የምትገኘው የግሪክ ሥርዓት የምትከተለው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሁኔታና ተልእኮ በሚል ርእስ ሥር ብፁዕ አቡነ ላዲስላቭ ሁችኮ ለጉባኤው ሰፊ መግለጫ እንደሚሰጡ ያመለክታል።

በዚህ እ.ኤ.አ. ሰነ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. የተከፈተው ዓውደ ጉባኤ ተሳታፊዎች ሁሉ ከፕራግ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ዶሚኪክ ዱካ ጋር እንደሚገኙ ሲር የዜና አገልግሎት ገልጦ፣ እ.ኤ.አ. ሰነ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ተጋባእያኑ በሁባሬ በቅዱስ ቀለመንጦስ ቤተ ክርስቲያን በሚያሳርጉት መለኮታዊ ሊጡርጊያ አማካኝነት እንደሚጠናቀቅም በማሳወቅ፣ በጉባኤው የምሥራቅ ሥርዓት የሚከተሉት አቢያተ ክርስቲያን ጉዳይ የሚከታተለው ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሓፊ ብፁዕ አቡነ ሲይሪል ቫሲልና የመላ ኤውሮጳ አገሮች የብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤቶች ኅብረት ዋና ጸሓፊ ብፁዕ አቡነ ዱአርተ ዳ ኩኛ በጉኤው በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙም ይጠቁማል።








All the contents on this site are copyrighted ©.