2015-06-05 18:49:00

ክብራችንን አናዋርድ ከሙስና እንታቀብ!


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍርናቸስኮስ ትናንትና ተዘክሮ ለዋለው በዓለ ቅዱስ ሥጋሁ ወክቡር ደሙ ለማክበር በቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራነንሰ ባዚሊካ መሥዋዕተ ቅዳሴ በማሳረግና ከባዚሊካው አደባባይ እስከ ቅድስት ማርያም ባዚሊካ ሳንታ ማርያ ማጆረ በቅዱስ ቍርባን ስግደትና አምልኮ ለተጓዙ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ምእመናን በቅዱስ ቍርባን የባረኩ ሲሆኑ በመሥዋዕተ ቅዳሴው ባደረጉት ስብከት “የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋሁ ወክቡር ደሙ ተበታትነን ክርስትያናዊ ክብራችን እንዳናጠፋና በሙስና ተዘፍቀን እንዳንዋረድ ይጠብቁናል” ሲሉ በሙስና ተዘባርቀን ክብራችንና ዕሴታችንን ዝቅ እንዳናደርግ አሳስበዋል፣

ክብረ በዓሉን በተመለከተ ባለፈው እሁድ የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ ላይ ምእመናን በዚሁ በዓል ለሚደረገው ቅዱስ ቍርባናዊ ዑደት እንዲሳተፉና በቅዱስ ቍርባን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስ በስግደትና ምስጋና አምልኮ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበው ነበር፣ የትናንትና ስብከታቸውንም ከዚህ ጋር በማያያዝ በኅብስትና ወይን አማካይነት ወደር የሌለው የፍቅር መሥዋትነት ተዝካር ለማድረግ ያዘዘን ጌታ ኢየሱስ በቅዱስ ቍርባን ሁሌ እንደሚሸኘን ሓዋርያትም ለመላው ዓለም ወንጌሉን ለማበሰር ያደረጉትን ረዥም ታሪካዊ ጉዞ ለመፈጸም አስፈላጊውን እርዳታ ከቅዱስ ቍርባን ነበር ያገኙት፣ ይህ የሕይወት እንጀራ ዛሬም ከእኛ ጋር አለ የእኛ ነው፣ ለዚህም ቤተ ክርስትያን የዚህ ታላቅ ጸጋ ተካፋይ በመሆን በምታቀርበው ክብርና ምሥጋና በምታደርገው አስተንትኖና ዝክር ትመግበናለች፣ ለዛሬ የሚሆንን ቃለ እግዚአብሔር “ላለመበታተን ከዚሁ የአንድነት ኪዳን የሆነ ቅዱስ ሥጋሁ ተመገቡ፤ ክብራችሁንና እሴቶቻችሁን ዝቅ እንዳታደርጉ ከዚሁ ለደኅንነታችሁ የተከፈለ ክቡር ደሙ ጠጡ” ይለናል በማለት ካሳሰቡ በኋላ ዛሬ በዘመናችን መበታተንና ዝቅ ማለት ምን ትርጉም አለው ሲሉ ይጠይቃሉ፣

“የጌታን ቃል ያልታዘዝንና በወንድማማችነት ያልኖርን እንደሆነ እንዲሁም የመጀመርያ ቦታን ለመያዝ እሽቅድድም ውስጥ የገባን እንደሆነና የጌታን ፍቅር ለመመስከር ብርታት ሲጐድለን በመጨረሻም ለሌሎች ተስፋ ለመስጠት ያልቻልን እንደሆነ እንበታተናለን” ካሉ በኋላ ቅዱስ ቍርባን የውኅደት ዋስትና መሆኑን ገልጠዋል፣ ከዚህ መበታተን የሚጠብቀን ቅዱስ ቍርባን ብቻ ነው ምክንያቱም ቅዱስ ቍርባን የኪዳን ፍጻሜ የውህደት ዋስትና በመሆን ስለ እኛ ሲል ዝቅ ያለውና እኛ አንድ እንድንሆን ኢምንት እስከ መሆን ትሕትና ተላብሶ የገለጠልንን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሕያው አድርጎ በመካከላችን ያኖረዋልና፣ ይህን ሁሉ ያደረገው ደግሞ እኛ አንድ እንድንሆን ዘንድ ነው፣ በህብስትና ወይን መልክ በመካከላችን ያለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንኛውንም መለያየት ጥለን ለድሆች አንድነት ለደካሙ ድጋፍ ዕለታዊ መስቀላቸው ለመሸከም ለሚቸግሩ ወንድማማዊ ፍቅር እንዲሁም በእምነት አደጋ ለሚገኙ እንድረዳ ይጠይቀናል፣ ካሉ በኋላ ዝቅ ማለት መዋረድስ ምን ይሆን በማለት ይጠይቃሉ፣

“ክርስትያናዊ ክብራችንን ማዋረድ ወይንም ዝቅ ማድረግ ምን ማለት ይሆን? ብለን የጠየቅን እንደሆነ በዘመናችን ጣዖቶች ከሥር መሠረታችን እንዲሰረስሩን መፍቀድ፤ በሚብለጨለጩ ነገሮች መስከር ጥቅም መፈለግ እኔነት አሸንፎን እኔ የሚለው የሁሉ ማዕከል ማድረግ እንዲሁም የሥልጣን ሽኩቻ በዕብሪት መወረር ስሕተትህን አለመቀበል የሌሎች እርዳታ እንደማያስፈልግህ አርጎ መገመትና የስም ክርስትያን ሆኖ የሞቀም የቀዘቀዘም ሳይሆን ማሀል ሰፋሪ ክርስትያኖች ስንሆን እንዲያው አረሜን ነን ለማለት ይቀላል፤ ይህ ከክብር ዝቅ ማለት ከክብር መውረድ” በማለት የዘመናችን ችግር ከገለጡ በኋላ ሌላ ዋነኛው ሕመም ደግሞ ሙስና መሆኑን አሳስበው ከዚህ የሚያድነን የጌታ ኢየሱስ ክቡር ደሙ ነው፣ የጌታ ኢየሱስ ክቡር ደም ከኃጢአቶቻችን ነጻ አድርጎ ክርስትያናዊ ክብራችንን ይመልስልናል፣ ከሙስናም ነጻ ያደገናል፣ ይህንን በደምብ የተረዳን እንድሆነ ቅዱስ ቍርባን ለበጎ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ሽልማት ሳይሆን ለደከሙ ኃይል ለኃጢአተኞች ምሕረት መሆኑን እንገነዘባለን፣ ወደፊት እንድራመድ ስንቅ ሆኖ የሚረዳን የእግዚአብሔር ምሕረት ነው፣ ሲሉ የቅዱስ ሥጋሁ ወክቡር ደሙ ዕሴት ምንኛ ያህል እንደሆነ ከገለጡ በኋላ ስለእምነታቸው መሥዋዕት ለሆኑ ክርስትያኖችን በማስታወስና ከእነርሱ አብረን ጌታን እንድናከብርና አምልኮ እንድናቀርብ አደራ በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.