2015-05-29 17:05:00

ብፁዕ ካርዲናል ቱክሶን፦ እርሃብና ከመጠን በላይ የተትረፈረፈ ኑሮ


በዓለም የሚታየው እርሃብ እስካልተወገደ ድረስ የሰው ዘር ጨርሶ በሰላም አይኖርም፣ የሚል ቅዉም ሃሳብ የሚያስትጋባ ጳጳሳዊ የፍትሃና ሰላም ምክር ቤት ዋና አዘጋጅነት ሥር በቫቲካን ማተሚያ ቤት የታተመው መሬትና ምግብ በሚል ርእስ ሥር የተደረሰው መጽሓፍ እ.ኤ.አ. ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚላኖ በመካሄድ ላይ ባለው ዓለም አቀፍ የምርት አቅርቦት ትርኢት ባለው የጉባኤ አደራሽ በቀረበው ዓውደ ጉባኤ ለንባብ መብቃቱ የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ አመድዮ ሎሞናኮ ገለጡ።

መጽሓፉን ለንባብ ለማብቃት በተካሄደው ዓውደ ጉባኤ ጳጳሳዊ የፍትህና ሰላም ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ፐተር ቱርክሶን ተገኝተው ንግግር ማስደመጣቸው የገለጡት የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ ሎሞናኮ አክለው፦

እርሃብና ከመጠን በላይ የተትረፈረፈ ኑሮ፣ ተጻራሪ ሁነት

በዚህ በሚላኖ በመካሄድ ላይ ባለው ዓለም አቀፍ የምርት አቅርቦት ትርኢት ቤተ ክርስቲያን ባላት የሰብአዊ ሊቅነት አማካኝነት ተሳታፊ መሆንዋ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህ ዓለም አቀፍ ትርኢት ምግብና የኃይል ምንጭ በሚል ርእስ ሥር እየቀረበ ባለው ትርኢትና በዚህ ርእሰ ጉዳይ በሚካሄዱት ዓውደ ጉባኤዎችና ጥናቶች በመሳተፍ አቢይ አስተዋጽዖ በመስጠት ላይ እንደምትገኝ ይኸው መሬትና ምግብ በሚል ርእስ ሥር የተደረሰው መጽሓፍ አብነት መሆኑ ብፁዕ ካርዲናል ቱርክሶን መጽሓፉን ለንባብ ለማቅረብ ባስደመጡት ንግግር ገልጠው፣ መጽሓፉ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ የሚላኖን ዓለም አቀፍ የምርት ትርኢት በይፋ ለመክፈት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ባስተላለፉት የድምጸ ምስል መልእክት፦ የተትረፈረፈ የምግብ ሃብትና እርሃብ የሚታይበት ዓለም ይኽ ሁለት ዓይነት ከልክ በላይና እጦት የሚል በዓለም የሚታየው ተጻራሪነት ተጨባጭ ሁነት እንዲቀረፍ ያቀረቡት ጥሪ በጥልቀት ያካተተ መሆኑ አብራርተው ዓለም አቀፍ የእርሻና ምግብ ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ 2012 እስከ 2014 ዓ.ም. ከ805 ሚሊዮን ሕዝብ በተመጣጠነ መግብ እጥረት መሰቃዩት የሰጠው መግለጫ ጠቅሰው፣ የምግብ እጦትና በምግብ የተትረፈረፈ ዓለም እንዴት በዚህ ምድር ሊኖር ይችላል የሚበላ የሌለው ሰው ክልክ በላይ የሚኖር ሰው። ለሁሉም የሚበቃ የምግብ ምርት እያለ እርሃብ መኖሩ ለኅሊናና ዓለም ለሚከተለው የኑሮ ሥልት ጥያቄ ነው እንዳሉ ሎሞናኮ አስታወቁ።

አመለካከትን መለወጥና ማደስ መብት ግዴትና ኃላፊነት ማክበር

ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ለዓለም አቀፍ የምርት ትርኢት መድረክ ባስተላለፉት መልእክት ትርኢቱ የሚያንጸባርቀው ርእሰ ጉዳይ ቃል ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ሁሉም አቅሙና ኃይሉ በማስተባበር እግብር ላይ እንዲያውለው፣ የአመለካከት ለውጥና ህዳሴ ብሎም የመብትና ግዴታ እንዲሁም ኃላፊነት እንዲከበር አደራ በማለት ያስተላለፉት ሃሳብ ብፁዕ ካርዲናል ቱርክሶን ጠቅሰው፣ አመለካከትን ለአንድ አዲስ ተቀባይነት ላለው እኩልነት የሚያረጋግጥ የልማት እቅድ መለወጥ ያለው አስፈላጊነት አብራርተው፣ ምግብ ማግኘት የሁሉ ሰው ልጅ መብትና ክብር አለ ምንም አድልዎና ማመንታት እንዲከበር የመንግሥታት ኃላፊነት መሆኑ ገልጠው፣ ቅድስት መንበር ይኸንን የሰው ልጅ ሰብአዊ መብትና ክብር ሙሉ በሙሉ ለማክበር የሚያበቃ መንገድ በሳቸው በሚመራው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ተደርሶ ለንባብ በበቃው መሬትና ምግብ በተሰየመው መጽሓፍ መብራራቱ ማሳወቃቸው ሎሞናኮ ገልጠዋል።

መሬትና ምግብ የተሰየመው መጽሓፍ ትንተናና የሚያቀርበው ሃሳብ

መጽሓፉ በሦስት ርእስ ሥር የተከፋፈለ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ክፍል ክርስትና እምነት አስተንፎ  መሠረት የእርሃብ መሠረታዊና መዋቅራዊ መንስኤው የሚተነትን መሆኑ ገልጠው፣ በሁለተኛ ክፍል ክርስትናው እምነት አስተንፍሶ በማስደገፍ በዓለም ያለው የምግብና የግብርና ፖለቲካ የሚተተንት ሦስተኛው ክፍሉ ደግሞ የዓለም የግብርናውና የምግብ ጉዳይ በተመለከተ ያለው ሁኔታ ለማሻሻል የሚደገፍ ሃሳብ የተኖርበት መሆኑ እንዳብራሩ ሎሞናኮ አስታወቁ።

በመቀጠልም የመላ ኢጣሊያ የቀጥተኛ ምረት አምራች ገበሬዎች ማኅበር ሊቀ መንበር ሮበርቶ ሞንካልቮ ባስደመጡት ንግግር በዓለም የእርሻ ምርት ላይ የሚፈጸመው ገማች የኤኮኖሚ አሰራር ያስከተለው የኤኮኖሚ ቀውስ በስፋት አብራርተው በዓለም ያለው እርሃብ ሳይቀር የሚሰጠው የግምት ኤኮኖሚያው ትንተና የሚያስከትለው የገንዘብ ሃብት ኪሳራ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑ መሬትና ምግብ የተሰየመው መጽሓፍ መሠረት በማድረግ ማብራራታቸው የገለጡት የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ ሎሞናኮ አክለው፣ በመጨረሻም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂው ዝነኛ ድምጻዊ ቦኖ ቮክስ ባስተላለፉት የድምጸ ምስል መልእክት በዚህ ዓለማዊነት ትሥሥር በተረጋገጠበት ዓለም የዓለም ሕዝብ እንደ አንድ ቤተሰብ በመኖር የሁሉም ምግብ የማግኘት መብት እንዲረጋገጥ በጋራ በተለያየ መስክ እንዲተጋ አደራ በማለት ዓለም የሁሉም ሰው ልጅ ሰብአዊ መብትና ክብር የሚከበርበት ሥፍራ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም በተለይ ደግሞ የመንግሥታት ኃላፊነት ነው እንዳሉ አስታውቀዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.