2015-05-27 16:41:00

Centesimus Annus-ምእተ ዓመት፦ ኤኮኖሚና ማኅበራዊ ሕይወት


እ.ኤ.አ. በ 1991 ዓ.ም. ር.ሊ.ጳ. ቅዱስ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ር.ሊ.ጳ. ሊዮነ ስምንተኛ እ.ኤ.አ. በ 1891 ዓ.ም. የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ሥልጣናዊ ትምህርት ሥር ቅርጽ ያስያዘው Rerum Novarum-አዳዲስ ነገሮች በሚል ርእስ ሥር የደረሱት ዓዋዲ መልእክት ዝክረ መቶኛው ዓመት ምክንያት Centesimus Annus-ምእተ ዓመት በሚል ርእስ ሥር የደረሱት ዓዋዲ መልእክት መርኅ በማድረግ ምእተ ዓመት በሚል መጠሪያ የተቋቋመው ማኅበር Centesimus Annus-ምእተ ዓመት ኤኮኖሚና ማኅበራዊ ሕይወት ርእስ ዙሪያ የጠራው ለሁለት ቀናት የተካሄደ ዓውደ ጉባኤ እ.ኤ.አ. ግንቦት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. መጠናቀቁ የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ አለሳንድሮ ጓራሺ አስታወቁ።

በተካሄደው ዓውደ ጉባኤ የተሳተፉት ጀነቭ በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብትና ክብር አስከባሪ ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ሐዋርያዊ ልኡክ ብፁዕ አቡነ ሲልቫኖ ማሪያ ቶማሲ ከዓውደ ጉባኤው ፍጻሜ በኋላ ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፦ የኢንዳስትሪው አብዮት ሥራ የሚጎዳ ነገር ግን አዲስ የሥራ ዕድል የፈጠረም ነው። ሥራ ይሻሻላል ልክ እንደ ማንኛውም ማኅበራዊና ሰብአዊ ጉዳይ ለውጥ ያጋጥመዋል። የሚያናገረውም ለውጡ ሳይሆን ኤኮኖሚ ሰብአዊነት ማእከል ከማድረግ ሂደት እየወጣ የገንዘብ ሃብት ላይ በማነጣጠር ብዝበዛና ትርፍ የተሰኙት ሁለት መንገዶች በመከተል እያስከተለው ያለው የኤኮኖሚ መዛባት የሥራ አጥነትና የድኽነት መስፋፋት ጉዳይ ነው።

በበለጸጉት አገሮች የሚመዘን ገበያ ሳይሆን ሁልንም አገሮች ለማሳተፍ ብቃት ያለው እኩል ገበያ ያስፈልጋል። የመተባበር የመደጋገፍ እሴቶች የሚከተል መሆን አለበት። በትክክል ለመናገር ከተፈለገ የበለጸገው አገር  በማደግ ላይ የሚገኙትንና ድኾች አገሮችን ትቶ በብልጽግና ጎዳና ለብቻው የሚራመድ ከሆነ በሙላት የበለጸገ አገር ፈጽሞ ሊሆን አይቻልም። በዚህ ዓለማዊነት ትሥሥር በተረጋገጠበት ዓለም ሰብአዊነት ማእከል ያደረገ ኤኮኖሚ እንዲረጋገጥ ካልተደረገ ዓለማዊነት ትሥሥር የሚያስከትለው ጉዳት ባለፉት ዘመናት ከታየው ማኅበራዊ ሰብአዊ ችግር እጅግ የባሰ ይሆናል፣ በመሆኑም ተከስቶ ያለው የኤኮኖሚ ቀውስ መፍትሔው ሰብአዊነት ማእከል ያደረገ በሥነ ምግባርና ግብረ ገብ የተካነ ኤኮኖሚ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ቤተ ክርስቲያን በማህበራዊ ዘርፍ የምትሰጠው ሥልጣናዊ ትምህርት አማካኝነት ለካቶሊኩ ዓለም ብቻ ሳይሆን ለሁሉም መልካም ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ጭምር የምታቀርበው ትምህርት ነው። በማኅበራዊ ዘርፍ የምትሰጠው ትምህርት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አገሮች በሚገኙት መናብርተ ጥበብ የጥናትና የምርምር ርእስ ሆነዋል። የቤተ ክርስቲያን ሥነ ማበራዊ ትምህርት በሚል የጥናት ዘርፍ በተለያዩ መናብርተ ጥበብ ትምህርት እንዲሰጥበት እየተደረገ ነው ብለው ያካሄዱት ቃለ ምልልስ አጠቃለዋል።   








All the contents on this site are copyrighted ©.