2015-04-27 16:43:00

ብፁዕ ካርዲናል ቨሊዮ፦ ኤውሮጳ ስስታምነትንና እራስ ወዳድነት ታስወግድ


የስድተኞችና የተጓዦች ሐዋርያዊ ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ቨሊዮ በብራሰልስ የኤውሮጳ ኅብረት አገሮች ማኅበር መሪዎች ስለ ስደተኞች ጸአት ርእስ ዙርያ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ያስቸኳይ ስብሰባ፣ ችግሩን ለምፈታት አቅዶ የወጠነው የስምምነት መርሃ ግብር ችግሩን ይፈታል ብሎ ለመናገር የሚያዳግት ነው። በመሆኑም የስደተኞች ጉዳይ የሚያስተዳድር ብቃት ያለው ረዥም እቅድ ላይ ያተኮረ የስድተኛ መስተዳድር ፖለቲካ ይወጥን ዘንድ አደራ በማለት አሁን ተወጥኖ ያለው እቀድ አርኪ አለ መሆኑ መግለጣቸው ሲር የዜና አገልግሎ አስታወቀ።

ማረ ኖስትሩም በሚል መጠሪያ ኢጣሊያ ትከተለው የነበረው በባህር በር በኩል ወደ ኢጣሊያ በኢጣሊያ በኩል ወደ ኤውሮጳ የሚገባው የስደተኛው ጸአት ለመቆጣጠርና ስደተኞችን ከሞት አደጋ ለማዳን ጥተጠቀምበት የነበረው መርሃ ግብር ትሪቶን በሚል መጠሪያ በኤውሮጳዊ መርሃ ግብር መተካተቱና ይኽ እቀድ እግብር ላይ ለማዋል በወር ከ ሶስት እስከ 9 ሚሊዮን ወጪ የሚጠይቅ መሆኑና ስደተኛው ከሞት አደጋ ማዳን የሚለው እቀድ ስደተኛው በገባበት አገር ለማስተናገድ የሚያበቃ እቀድ ያካተተ ባለ መሆኑ ለስደተኞች ችግር መፍትሄ የሚያሰጥ መርሃ ግብር ሊታከልበት ይገባል፣ እንዲህ ካልሆነ የተደረሰው ስምምነት መፍትሄ ያስገኛል ለማለት ያዳግታል እንዳሉ የገለጠው ሲር የዜና አገልግሎት አክሎ፦ ወደ ኢጣሊያ የባህር በር በኩል የሚገባው ስደተኛ ወደ 28 የኤውሮጳ ህብረት አገሮች ማከፋፈል ያስፈልጋል እንዳሉ አስታውቀዋል።

ከሊቢያ የሚነሱት ስደተኞች የሚያጓጉዙ መርከቦችና ባለ ሞተር ጀልባዎች ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅሱ የወንጀል ቡድኖች እንዳይገለገሉባቸው ገና ስደተኞች ከማሳፈራቸው ቀድሞ በተባበሩት መንግሥታት ጥበቃ ሥር በሚካሄደው ወታደራዊ ጥቃት አማካኝነት ለማውደም የኤውሮጳ ኅብረት የወጠነው እቅድ በቅድሚያ የዓለም አቀፍ ሕግ የሚቃወም ነው። በአንዲት ሉአላዊት አገር ድንበር ውስጥ የሚገኙት መርከቦችና ጀልባዎች ማውደም በሕግ የሚያስጠይቅ ውጥረትና የጦርነት የግጭት ምክንያት እንደሚሆንም አያጣራጥርም መርከቦችን ለማውደም የሚሰነዘረው ጥቃት ንጹሃን ሰዎች ለሞት የማይዳርግ ለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለ? በሊቢያ የባህር በር በኩሉ ወደ ኤውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩት ስደተኞች ከተለያዩ አገሮች በተለይ ደግሞ ግጭት ጦርነት የሰብአዊ መብትና ክብር ረገጣ ካለባቸው አገሮች የተወጣጣ ነው። ስለዚህ ጦርነትና አምባ ገነናዊ መንግሥታት እስካሉ ድረስ የሰብአዊ መብትና ክብር ረገጣ እስካለ ድረስ የስደተኞች ጸአት የማይቀር ነው እንዳሉ ሲር የዜና አገልግሎት አስታወቀ።

ስደተኛው እንዳይገባ ከማድረግ ይልቅ ለስደት የሚዳርጉት ምክንያቶችን ገጥሞ ለማጥፋት መተባበርና መረባረብ ያስፈልጋል፣ ጦርነትና ግጭት የሚታይባቸው አገሮች አምባ ገነን መንሥታት ሁሉ የጦሮ መሣሪያ የሚያገኙት የጦር መሣሪያ አምራች ከሆኑት ከበለጸጉት አገሮች ነው። ስለዚህ ለስደት የሚዳርገው ችግር ጨርሶ ለመቅረፍ ምን መደረግ እንዳለበት በውኑ የተሰወረ አይደለም እንዳሉ ሲር የዜና አገልግሎት አስታወቀ።








All the contents on this site are copyrighted ©.