2015-03-18 16:22:00

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ.፦ መኃሪዎች እንጂ የቤተ ክርስቲያን በር ለሌላው የምትዘጉ አትሁኑ


ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ሁሌ እንደተለመደው ጧት በአገረ ቫቲካን ቅድስት ማርታ ሕንፃ በሚገኘው ቤተ ጸሎት የሚያሳርጉት መሥዋዕት ቅዳሴ እ.ኤ.አ. መጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በመቀጠል “ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ቤት ነች፣ የምህረት ቤት ሁሉንም የምታቅፍ የምታስተናግድ ነች፣ እንዲህ በመሆንዋም በሮቸዋ በክርስቲያኖች የሚዘጋ አይደለም” በሚል ቋሚ ሃሳብ ላይ ያነጣጠረ አስተንትኖ መለገሳቸው የቅድስት መንበር መግለጫ አስታወቀ።

ቅዱስ አባታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን የሚቀበል ለሚፈልጉት ከእርሱ ለራቁት ሁሉ በሮቹን የሚከፍት ሆኖ እያለ ብዙዉን ጊዜ ክርስቲያኖች ግን ይኸንን ክፍት በር ለሚያንኳኩት ሁሉ የሚዘጉ ሆነው እንደሚገኙ በመደጋገም ክፍት ስለ ሆነው በርና ስለ ተዘጋው በር በተመለከተ የሚሰጡት ምዕዳን በመቀጠል፣ ይኽ ደግሞ የክርስቶስ ምሉእ ምህረትና በእርሱ የሚያምኑት ሆነው እያሉ በሚኖሩት አናሳ ምህረት መካከል ያለው ውጥረት የሚያመለክት ሲሆን፣ ቅዱስ አባታችን የዕለቱ ከትንቢተ ሕዝቂኤል ምዕ. 47 ከቁጥር 9 እስከ 12 የተወሰደው ምንባብ ላይ ተንተርሰው በቤተ መቅደስ ጕበን ፊት ስላለው በሙላት የሚፈሰው ኃይለኛ ወንዝ በመሆን በአሳ ሃብት የሚትረፈረፈ ማንኛውንም ነገር ሁሉ የሚፈውስ “ፈዋሽ ውኃ” ለመሆን ስለ በቃው የወንዝ ጅረት የሚናገረውን ቃል፣ ከዕለቱ የዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 5 ከቁጥር 1 እስከ 16 ጋር ካለው በተለይ ደግሞ ሳይዳ የተባለው ሁሉም የሚጠመቅበት ወንዝ ጋር በማገናኘት ይኽ ወንዝ በተናወጠ ጊዜ በሚያፈሰው ውኃ ለሚታጠብ የፈውስ ጸጋ የሚሰጥ መሆኑ አብራርተው፣ ያ ለ 38 ዓመት በዚያ ወንዝ ለመታጠብ ያልታደለ በዚያ ክልል ተኝቶ የነበረ በአካል መስለል በሽታ የተጠቃውን የፈውስ ጸጋ የሚመኝ ከኢየሱስ ጋር ስለ ተገናኘውና፣ ኢየሱስ ችግሩን ተረድቶለትም አልጋህን ተሸክመህ ሂድ የሚለውና ኢየሱስ እንዳለው በማድረግ እንደዳነና፣ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ይኸንን በማድረጉ ምክንያት የሕግ መምህራን ይከሱታል ሊገድሉትም ይፈልጋሉ፣ ዛሬም የሚታይ ታሪክ ነው። በአሁኑ ወቅት በሕይወቱ ግብረ እከይ የፈጸመ በውስጡ የሚሰቃይ መንፈሱ የታመመ የተከዘ ሰው በጥፋቱ ተማሮና ታምኖ ሕይወቱን ለመለወጥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሚናወጠው ውኃ ለመታጠብ ወይንም ውስጡን የሚነካው የእግዚአብሔር ቃል በማዳመጥ ወደዚያ የሕይወት ውኃ መሄድ እሻለሁ ብሎ ሲነሳ የሚያሰናክሉ፣ ይኸንን የመዳን በር ለመዝጋት የሚራወጡ አሉ። እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመግባት ሲፈልግ፣ አይ እሁድ ለቅዳሴ ና በቅዳሴ ተሳተፍ ኃጢአጠኛ ስለ ሆንክ በውጭ ቆመሆ ቅዳሴውን ተከታተል፣ ብለው የሚያዙ ክርስቲያኖች የስነ ልቦና ሊቃውንት ነን ባዮች እንዳሉ አስታውሰው፦ “ቤተ ክርስቲያን ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤት ነች የክርስቶስ በመሆንዋም በሮችዋ ዘወትር ክፍት ነው። ለማንም የማይዘጋ በር። እንዳውም ለኃጢአተኛው፣ ኢየሱስ ሁሉ ተቀባይ ሁሉንም የሚያስተናግድ ነው። ቤቱም እንደእርሱ ነች፣ ኢየሱስ የሚያስተናግድ ብቻ ሳይሆን እራሱ ወጥቶ ተስተናጋጁን የሚፈልግ ነው፣ ወጥቶ በጎዳና በመጓዝም የታመመውን ሁሉ ወደ እርሱ ይጠራል፣ የቆሰለው መራመድ የማይችለውንም አቅፎ በመሸከም ወደ ቤቱ ይወስደዋል፣ አዎ ይኽ ምሉእ ምህረት ይባላል፣ ጌታ መኃሪ ነው። ይኽ ደግሞ እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚፈልገው ምህረትን እንጂ መሥዋዕት አይደለም ሲል የተናገረውን ቃል ያስታውሰናል” እንዳሉ የገለጠው የቅድስት መንበር መግለጫ አክሎ “ኢየሱስ ፍቅር ሕግ ያደርጋል፣ ሕጉ ፍቅር ነው። አንተ ማነህ የልብህን በር ለሌላው ሰው የምትዘጋ፣ ገዛ እራሱ ሊለውጥ መንገዱን ለማስተካከል ለሚፈልገው በር የምትዘጋ እንተ ማን ነህ፣ በልቡ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ላነቃቃው መንፈስ በር የምትዘጋ አንተ ማን ነህ? በዚህ እየኖርነው ባለው የአቢይ ጾም ወቅት ልክ እንደ ሕግ ሊቃውንት ያንን በአካል መስለል ለታመመው ቀርቦ በሰንበት ቀን ስላዳነው ይኸንን እንደ ጥፋት በማየት እንደወቀሱት ላለ መሆን እንትጋ፣ በኢየሱስ አማካኝነት ፍቅር ሕግ ሆነዋል፣ የፍቅር ሕግ እርሱም እግዚአብሔርን አፍቅር ባለእንጀራህን እንደ ገዛ እራስህ አፍቅር የሚል ነው፣ ስለዚህ ወደ ኢየሱስ እንለወጥ በእርሱ እንለወጥ እንደ እርሱ መኃሪዎች እንሁን”  ብለው ያስደመጡት አስተንትኖ እንዳጠቃለሉ አስታወቀ።








All the contents on this site are copyrighted ©.