2015-02-11 17:27:51

የ.ር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ፣


RealAudioMP3 ውድ ወንድሞችና እኅቶች! እንደምን አደራችሁ!
ባለፉት ቀናት በቤተሰብ ውስጥ የእናትና የአባት ቦታን አስመልክተን አስተንትነናል ዛሬ ደግሞ ስለ ልጆች ለመናገር እወዳለሁ፣ ለትምህርቱ መግቢያ እንዲሆነን ከትንቢተ ኢሳያስ 60፡4-5 “ዓይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል።
በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፥ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፥ አይተሽ ደስ ይልሻል፥ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል።” የሚለውን እንመለከታለን፣ ይህ ታላቅ የደስት ምልክት ሆኖ እውን የሚሆነውም ለብዙ ዘመናት ተለያይተውና ሲሰቃዩ የነበሩ ወላጆችና ልጆች በኅብረት ወደ ነጻነትና ሰላም ሲጓዙ ነው፣ ሁኔታው በቀጥታ የሚመለከተው ከአገራቸውና ከቤታቸው ርቀው ለረዥም ጊዜ የተጓዙ እስራኤላውያንን ይመለከታል፣ ስለሆነም አንድ ሕዝብ ባለው ተስፋና በትውልዱ ውህደት ኃይለኛ መተሳሰር አለ፣ ይህንን ልብ ብለን እናስታውስ፣ አንድ ሕዝብ ባለው ተስፋና በትውልዱ አንድነት ኃይለኛ መተሳሰር አለ፣ የልጆች ደስታ የወላጆች ልብን ይሞላል መጻኢያቸውንም እንደገና ይከፍታል፣ ልጆች የቤተሰብና የአንድ ኅብረተሰብ ደስታ ናቸውና፣ የሥነሕይወት ማንኛ ውጤት ወይንም የወላጆቻቸው የግል ንብረት አይደሉም፣ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፣ እያንዳንዱ ልጅ አንድያና የማይደገም ነው፣ ሆኖም ግን ምንጩ ከሆኑ ሥሮቹ ጋር የተሳሰረ ነው፣ ልጅ ሆኖ መወለድ በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ለአንድ አዲስና ልዩ የሰው ልጅ ፍጡር ሕይወት በመስጠት የፍቅር ዝክርና ተስፋን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍና ወደፊት ማራመድ ነው፣ ለወላጆች እያንድንዱ ልጅ ራሱ የቻለና ልዩ ነው፣ የግል ሕይወቴና የቤተሰቦቼ ሁኔታ አንስቼ ልናገር ፍቀዱልኝ፤ በቤተሰባችን ውስጥ አምስት ልጆች ነበርን፣ እናቴን ከአምስቱ ማንን ትመርጭያለሽ ብለን በጠየቅናት ጊዜ የእጇ ጣቶችን እያሳየች እንደእነዚሁ አምስት ጣቶች አምስት ልጆች አሉኝ፣ አንድዋን ጣት ቢመቱኝ ያመኛል እንዲሁም ሌላዋን የመቱኝ እንደሆነ ያመኛል፣ ሁላም ልጆቼ ናቸው ግን እንደ የእጆቼ ጣቶች የተለያዩ ናቸው” በማለት ትመልስልን ነበር፣ ቤተሰብም እንዲሁ ነው፣ ልጆች የተለያዩ ቢሆኑም ግን ሁላም ልጆቻችን ናቸው፣ አንድን ልጅ የምንወደው መልከ መልካም ወይም ሌላ ደስ የሚያሰኝ ነገር ኖሮት ሳይሆን ልጃችን በመሆኑ ብቻ ነው፣ ሕይወቱ ምንም እንኳ ከእኛ የምትመንጭ ቢሆንም ለገዛ ራሱ ለገዛ ራሱ በጎ ነገር እንዲሁም ለቤተሰቡ ለማኅበረሰቡና ለመላው ዘመደ አዳም በጎ ነገር የተሰጠ ነው፣
ከዚህ የሚከተል ሌላ ነገርም አለ! ልጅ መሆን የሚያስደንቅ ውሉዳዊ ፍቅርን የምናገኝበት ነው፣ ልጆች ገና ከመወለዳቸው በፊት የተፈቀሩና በፍቅር የሚጠባብቅዋቸው ናቸውና፣ በአደባባዩ ስንት ያረገዙ እናቶች ሆዳቸውን በማመልከት በውስጡ ያለውን ሕጻን እንድባርክላቸው ይጠይቁኛል፣ ገና ከመወለዳቸው በፊት የተፈቀሩ ናቸው፣ ይህ ፍቅር ስጦታ ነው፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደወደደን ሁሉ ይህም ፍቅር ገና ከመወለድ በፊት ያለ ነው፣ እዚህ ዓለም ውስጥ ከመወለዳቸው በፊት መልካምም ይሁን መጥፎ ምንም ሳያደርጉ ንግግር ሳይጀምሩ ማሰብ ሳይጀምሩ የተወደዱ ናቸው፣ የመወለድ ታላቁ ነገር የእግዚአብሔር ፍቅር እንድናውቅ ይረድናል፣ በእያንዳንዱ ሕጻን ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር የዚህ ፍቅር ማኅተም ያኖራል፣ ከዚህም ማንም ሊነጥቃቸውና ሊደምሣቸይ የማይቻለው ሰብአዊ መብቶቹ ይፈልቃሉ፣ በዘመናችን ብዙ ልጆች መጻኢን በመፍራት ወደኋላ የማንፈግፈግ ችግር ይታያል፣ ነገር ግን ከሰማያዊ አባታችን መጻኢን መፍራት እንደሌለብን ለመማር እንችላለን፣ እግዚአብሔር አባታችን ሁሌ ወደፊት እንድንራመድ ነጻ ይተወናል ሆኖም ግን ብቻችን አይተወንም ሁሌ ይሸኘናል፣ ብንሳሳትም ፍቅሩን ሳያጐድል እየተከታተለን በትዕግሥት ይጠባበቀናል፣ ሰማያዊ አባታችን በምንም ተአምር ከዚህ ፍቅር ወደኋላ አያፈገፍግም፣ ልጆቹ ብርታት ኖሮአቸው ወደ ፊት እንዲራመዱ ይፈልጋል፣
ልጆችም በበኩላቸው አዲስ ዓለም ለመገንባት መፍራት የለባቸውም፣ ከተቀበሉት የበለጠ ዓለም እንዲያገኙ ይገባቸዋልና፣ ይህንን ግን አለምንም አስመሳይነትና ማስፈራራት መሆን አለበት፣ የልጆች ዕሴት ማወቅና ወላጆችን ማክበር ሁሌ መረሳት የሌለበት ነው፣
አራተኛው የእግዚአብሔር ትእዛዝ ልጆች አባታቸውና እናታቸው እንዲያከብሩ ይነግረናል (ዘጸ 20.12) ሁላችን የተወለድን ስለሆንን ይህ ት እዛዝ ሁላችንን እንደሚመለከት መዘንጋት የለብንም፣ ይህ ት እዛዝ ስለእግዚአብሔር ከሚናገሩ እዛዞችን ተከትሎ ወዲያውኑ ሲነገረን አንድ መለኮታዊ የሆነ ነገር አለበት ማለት ነው፣ ወላጆችን አክብር ብቻ ብሎ አያበቃም እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ አገር ዕድሜህ እንዲረዝም ይላል፣ በትውልድ መካከል ያለው መተሳሰር የመጻኢ ዋስትና ሲሆን የሰውልጅ እውነተኛ ታሪክ ዋስትናም ነው፣ ወላጆችን የማያከብር ማኅበረሰብ ክብር የሌለበት ማኅበር ነው፣ ወላጆችን የማናከብር ከሆነ ክብራችን እናጠፋለን፣ ደፋርና ደረቅ ወጣቶች የበዛባት ማኅበረሰብ እናቆማለን፣ በዚህ አንጻር ልጆችን እንደአንድ ሸክም አድርገው የሚገምቱም አይጠፉም፣ ያለንበት ኤውሮጳን የተመለከትን እንደሆነ የወሊድ መጠን አንድ ከመቶም አይደርስም፣ ይህ ሁኔታ ብዙ ልጆች ላልዋቸው ቤተሰቦችን እንደ ማኅበረሰብ ሸክም አድርጎ ማየትም አስከተለ፣ ነገር ግን ልጆች መውለድ ኃላፊነታዊ መሆን አለበት፣ ር፣ሊ፣ጳ ብፁዕ ጳውሎስ ስድስተኛ በሁማነ ቪቴ በተሰኘው ሓዋርያዊ መልእክታቸው ስለዚሁ ኃልፍነት በሰፊው ገልጠውታል፣ ልጆች ላለመውለድ የመምረጡ ጉዳይ ከራስ ወዳድነት የሚመነጭ ምርጫ ሲሆን ሕይወት ለመቀጠልና ሃብታም ለመሆን ልጅ ለመውለድ መምረጥ ያስፈልጋል፣ ልጆቹ ከወላጆች ጋር መተባበርና መተጋገዝ እንዳለባቸው ቤተሰብን ወደፊት ለማራመድ እያንዳንዱ ድርሻውን ማበርከት እንዲማሩ ያስፈልጋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.