2015-02-02 15:13:55

ክርስትያኖች ሁላቸው የእግዚአብሔር ቃል አድማጮችና ሰባኪዎች መሆን አለባቸው፣


RealAudioMP3 ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና እሁድ እኩለ ቀን ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምእመናንና ነጋድያን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት “ክርስትያኖች ሁላቸው የእግዚአብሔር ቃል አድማጮችና ሰባኪዎች መሆን አለባቸው፣” ሲሉ ካስተማሩና ጸሎት ከደገሙ በኋላ እፊታችን ሰኔ ወር የቦዝንያና ሀርዘጎቪና ዋና ከተማ በሆነችው ሳራየቮ ሓዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፣
“የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ የሆነ እንደሆነ እፊታችን ሰኔ ወር ቅዳሜ ስድስት ቀን የቦዝንያና ሀርዘጎቪና ዋና ከተማ በሆነችው ሳራየቮ ሓዋርያዊ ጉብኝት አደርጋለሁ፣ ይህ ሓዋርያዊ ጉብኝት ስኬት አግኝቶ በቦታዊ ለሚገኙ ካቶሊካውያን ም እመናን ብርታት የሚሰጥ እንዲሁም በአገሪቱ ለወንድማማነትና ለሰላም ጽናት ለሃይማኖታዊና የጓደኝነት ውይይት አስተዋጽኦ እንዲኖረው ካሁን ጀምራችሁ እንድትጸልዩ እማጠናለሁ” ሲሉ አደራ ብለዋል፣
ቅዱስነታቸው ከሁለት ዓመት በፊት የመንበረ ጴጥሮስ በትረ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ይህ ሓዋርያዊ ጉዞ አሥራ አንደኛው ሲሆን ካሁን በፊት ይፋ በሆኑት መርሓ ግብሮች መሠረትም እፊታችን ወርኃ መጋቢት 21 ቀን ወደ ናፖሊ እንዲሁም ሰኔ 21 ቀን ወደ ቶሪኖ በመጨረሻም ከመስከረም 22 ቀን እስከ 27 ቀን በፊላደልፍያ በሚካሄደው ስምንተኛ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ለመሳተፍ ወደ ተባበሩት መንግሥታት አመሪካ እንደሚሄዱም የሚታወስ ነው፣ በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ መሠረት ትንናትና የተነበበው ወንጌል “ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ።
እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ።
በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤ እርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።
ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ። ሁሉም። ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ።
ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ። (ማር 1፤21-27) የሚል ነበር፣
ቅዱስነታቸው ወደ ቅፍርናሆም ገቡ የሚለውን ቃል መነሻ በማድረግ ቅፍርናኖም በኢየሱስ ዘመን በገሊላ ከሚኙ ታላቅ ከተማ እንደነበረችና ኢየሱስ ከሁሉ አስቀሞ ወንጌልን እንደሰበከ ገልጠው ኢየሱስ ወንጌልን ለመስበክ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዳላስፈለገው ቃለ እግዚአብሔርን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሰበከው አብራርተዋል፣ ይህም የሚያመለከተው ኢየሱስ ከሁሉ አስቀድሞ ለማድረግ ይፈልገው የነበረ ተልእኮ መሆኑን ነው፣ በወንጌሉ እንደተጠቀሰው ሕዝቡ ኢየሱስ እንደ ባለ ሥልጣን እንጂ እንደ ጸሓፊዎቻቸው እንዳላስተማራቸው ተመልክተዋል፣ ቅዱስነታቸው አሁንም ቃለ ወንጌሉን መሠረት በማድረግ በሥልጣን ሲል ምን ማለት ይሆን ብለው ይጠይቃሉ፣
“ለመሆኑ በሥልጣን ሲል ምን ማለት ይሆን? በሰብአዊ የኢየሱስ ቃላት የእግዚአብሔር ቃል ሙሉ ኃይል ይሰማ ነበር ማለት ነው፣ የመጽሓፍ ቅዱስ ደራሲና ገላጭ የሆነ የእግዚአብሔር ሥልጣን ይሰማ ነበር ማለት ነው፣ የእግዚአብሔር ቃል የተባለውን እውን የሚያደርግ ነው፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ከፈቃዱ ጋር አንድ ስለሆኑ ነው፣ በዚሁ አንጻን የእኛ የሰው ልጆች ሁኔታ የተመለከትን እንደሆነ ባዶ የሆኑ ቃላት መሠረት የሌላቸውና ከአስፈላጊ በላይ የሆኑ ከእውነት ጋር የማይገናኙ ቃላት እንደረድራለን፣ የእግዚአብሔር ቃል ግን እውነት ነው ከፈቃዱ ጋር አንድ ስለሆነም የሚለውን ይፈጽማል፣ ስለዚህ ወንጌል የሕይወት ቃል ነው፣ ሰዎችን አይጮቅንም፣ በተቃራኒው በዚሁ ዓለም እርኩሳን መንፍስት ተይዘው በባርነት ለሚገኙት ነጻ ያወጣል፣ የዓለማችን እርኩሳን መናፍስት የሚያስከትሉት ከንቱነት የገንዘብ ፍቅር እብሪት ስሜታዊ መሆንና የሚመስልዋቸው ናቸው፣ ወንጌል ልብን ይቀይራል! ሕይወትን ይቀይራል! ለክፉ ነገር ያለንን ዝንባሌ ለመልካም ነገር እንዲሆን ይለውጣል፣ ወንጌል ሰዎችን ለመለወጥ ኃይል አለው፣ ይህንን አትርሱ! በየዕለቱ ከወንጌል አንድ ክፍል እንድታነቡ ይሁን፣ ይህ ሊለውጣችሁ የሚችል ሕይወትንና ልብን ሊለውጥ የሚችል ኃይል ነው፣ ሲሉ ካስተማሩ በኋላ ክርስትያኖች ሁላችን የቃለ እግዚአብሔር አድማጮችና ሰባኪዎች እንድንሆ አደራ ብለዋል፣
እመቤታችን ድንግል ማርያም ቀናተኛ የእግዚአብሔር ቃል አድማጮችና እውነተኞች ሰባክያነ ቃለ ወንጌለ እግዚአብሔር እንድንሆን ታስተምረን ሲሉ ተማጥነው ከሕዝቡ ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳርገዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.