2015-01-05 16:33:05

መጥፎ ነገር የሚያደርግ ሁሉ የሰላም ጠላት ነው፣ በየቦታው ሰላምን እንድትገነቡ ይሁን፣


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍርናቸስኮስ ትናንትና እኩለ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከምእመናንና ነጋድያን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት ባቀረቡት ጉባኤ አስተምህሮ “በዓመቱ መጀመርያ በልቦቻችን የሰላም ተስፋን እንደገና በማብራት በየዕለቱ የሰላም ገንቢዎች መሆን አለብን” ሲሉ ምንም እንኳ ጨለማን ተገን በማድረግ ሰላምን ለማደፍረስ የሚታገሉ ቢኖሩም ሰላምና ዕርቅ ሊገኙ እንደሚቻል ገልጠዋል፣
ቅዱስነታቸው እ.አ.አ በአዲስ ዓመት ስለሰላም የጀመሩትን ትምህርት በመቀጠል “ብዙ ሰዎች አፋቸው ስለ ሰላምና ብርሃን ሲለፈልፍ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሚመርጡት ጨለማና ውግያ ነው፣ ስለሰላም ስንናገር የውግያ መቆም ብቻ በቂ አይደለም፣ ሰላም መገንባት ያለበት ብዙ መስዋዕትና ጥረት የሚያስፈልገው ስለሆነ ውግያ ማቆም የመጀመርያው መነሻ ሲሆን ለግንባታው ግን ሁላችን መሥራት አለብን፣ ባሁኑ ግዜ በአእምሮዬ የሚመላለሰው በዓለማችን ስላሉ የተለያዩ ግጭቶች ከሁሉ በላይ ደግሞ በቤተሰብ በተለያዩ ማኅበረሰዎች የሚያስከትለውን ችግር ነው፣ ስንት ቤተሰብና ስንት ማኅበረሰዎች በውግያ ሲጎዱ በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉ ሰላም ነው እየተባለ በሚወራላቸው ከተሞቻችን በብዙ ቤተሰቦችና ማኅበረሰቦች መካከል እንዲያው በቍምስናዎችም ሳይቀር ሌላ ውግያና መለያየት ይታያል፣ በሰለጠኑት አገሮች ከተማዎች በባህል በዘርና ጐሳ እንዲሁም በሃይማኖት ተከፋፍለው አንዱ ቡድን ሌላውን ሲያጠቃ እንታዘባለን፣ ስለዚህ የሰላም ብርቱ ፍላጎትና የግንባታው እቅድ ከሌለ መጻኢ የሚባል እንደሌለ መገንዘብ አለብን” ሲሉ አሳስበዋል፣
በዕለቱ የተነበበው የወንጌል ክፍል ስለብርሃንና ጨለማ የሚናገር በመኖሩ እንዲሁም በሰማዩ አሸብርቃ የነበረቸውን ጸሓይ በመመልከት ሰላም እንደብርሃን ተቃራኒውም እንደጨለማ አቅርበው “ክፋት የሚሰራ ሰላምን ይጠላል፣ ስለብርሃን ብዙ የሚናገሩ ሰዎች በተግባር አታላዩን ጨለማ ይመርጣሉ፣ አብዛኛውን ግዜ ስለሰላም እንናገራለን ነገር ሁሌ ወደ ውግያ እንሮጣለን፣ ወይንም እጆቻችንን አጣምረን ምንም እንደማይመለከተን ዝም ማለትን እንመርጣለን! እንዲህ በማድረግም ለሰላም ግንባታ ምንም አናበርክትም ማለት ነው፣ ስለዚህ ማንኛው ክፋት የሚሰራ ብርሃንን ይጠላል! መጥፎ ተግባሩ እንዳይታይም ወደ ብርሃን አይወጣም፣ በአጠቃልይ መጥፎ የሚያደርግ ሁሉ ሰላምን እንደሚጠላ ነው፣ ለዚህም ነው የዘንድሮ የሰላም ቀን መልእክታችን ርእስ “ወንድማሞች እንጂ ባሮች አይደለንም” የሚለው፣ ይህ ማለትም ሁላችን የሰው ልጅ በሰው ልጅ መመዝመዝ የለበትም፣ የሰው ልጅ ምዝመዛ ኃጢአት ሆኖ በኅብረተሰብ ያለውን ግኑኝነት በመግደል መከባበር ፍትህና ፍቅር ያለበት ማኅበረሰብ ውስጥ መኖርን ያግዳል፣ እርግጥ ነው በዓለማችን ውስጥ ያሉ ሁላቸው የሰላም ጥማትና ረሃብ አላቸው፣ ለዚህም በማንኛው ቦታና ሁኔታ ሰላምን መገንባት ያስፈልጋል፣” ሲሉ በአደባባዩ የነበረውን በታላላቅ ፊደሎች የተጻፈውን “በሰላም ስር ጸሎት አለ” የሚለውን እንደገና በማንበብ “የጌታ ታላቅ ስጦታ የሆነው ሰላምን ለመቀበል በየዕለቱ መጸለይና በምንገኝበት ሁሉ በኃላፊነት ተቀብለን ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፣” ሲሉ ተማጥነዋል፣







All the contents on this site are copyrighted ©.