2014-12-27 18:31:49

ሰንበት ዘብርሃን!


መዝ፤ አቅዲሙ ነገረ በኦሪት
ንባብ፤ ሮሜ 13፡11-ፍጻሜ፤ 1ዮሓ 1፡1-ፍጻሜ፤ የሓዋ ሥራ 26፡12-19፤ ዮሐ 1፤1-19
ምስማክ፤ ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፤ እማንቱ ይምርሓኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ፤ ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ፣
በዛሬው ሰንበት ከሚነበበው ወንጌል ኃይለ ቃል አድርገን የምንወስደው «ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም ፤» የሚለውን ነው (ዮሐ፡ 1፡11)፡፡
RealAudioMP3
እዚህ ላይ መነሳት ከሚችሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ይሆናሉ፡ «እነማን ናቸው ወገኖቹ…ይህን ያህል እምነት የተጣለባቸው? ይህ ክብር የተሰጣቸው? ምናልባት በስልጣን ከፍ ያሉ ወይም በሀብታቸው ዓለም በልዩ መዝገብ ላይ ያሰፈረቻቸው ናቸው? ምናልባት በመገናኛ ብዙኃን ቀን ከሌሊት የሚወራላቸው ይሆኑ የእርሱ ወገኖች?» መጽሐፍ ግን የክርሰቶስን ወገኖች «ታናናሽ» ብሎ ነው የሚጠራቸው፡፡ የክርስቶስ ወገኖች እርሱን በቅን እና በትሁት ልብ የሚፈልጉት ናቸው፣ ምክንያቱም በወንጌሉ መሰረት ግን የእግዚአብሔር ወገን ነኝ ያለ ሁሉ እውነትም ወገን ሆኖ ክርሰቶስን የተቀበለ አልተገኘም በዘመኑ፡፡ ስለዚህ በተስፋው መሠረት ቃል የተገባለት እና የተመረጠው ሕዝብ ሳይሆን ለአሕዛብ ሆነ፣ መዝሙረኛው ዳዊት «የማላውቀው ሕዝብ ተገዛልኝ…ትዕዛዜን እንደሰሙ ይታዘዙልኛል» እንዳለው (መዝ፡ 18፡43)፡፡ የመዳኛው ቀን መምጣቱን መሲሕም በመካከሉ መቆሙን ያላወቀው፣ የተመረጠ ሕዝብ በመሆኑ ብቻ ይታበይ የነበረው ግን ዐይኑም ልቡም ታውሮ ነበርና ወገኔ ብሎ የመጣውን አምላክ ሊቀበለው አልቻለም፡፡ ክርሰቶስም ይህን የመዳኑን ጊዜ ላላወቀው ሕዝብና ከተማ አለቀሰለት (ሉቃ፡ 19፡41-44)፡፡ ልበ ትሁታን ግን አንዴ ሲያዩት፣ የአፉን ትምህርት ሲሰሙ፣ የእጁን ድንቅ ስራዎች ሲመለከቱ በአግራሞት ተሞሉ፣ ጨለማቸው በራላቸው፤ ቅ. ጳውሎስ «እስራኤል አጥብቀው የፈለጉትን አላገኙትም፣ የተመረጡት ግን አገኙት፣ የቀሩት ልባቸው ደነደነ» እንዳለው (ሮሜ 11፡7)፡፡
የዛሬው ወንጌል «ሁሉ በርሱ ተፈጠረ» ይላል (ዮሐ 1፡3)፡፡ ከዚህ የምንማረው ደግሞ ሁሉ በክርስቶስ ተፈጥሮ ሳለ ፍጡር ግን ከዳተኛ ሆነ፤ ፈጣሪውንም ጠንቅቆ ባለማወቁ አምላኩ በጎበኘው ጊዜ ወደ ልቡ ሳያስገባው፣ ሳይቀበለው ቀረ፣ በፈጣሪው ላይም ልቡን አሸፈተ፡፡ ነገር ግን በፍጥረታችን ደካማ፣ አንዳንዴም አስቸጋሪ ብንሆንም ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛን የማይጠላ አምላክ ነውና «ወገኖቼ» ብሎ መምጣቱን አያቋርጥም፡፡ ከሰው የሚጠበቀው ደግሞ በበር ቆሞ የሚያንኳኳውን እና ብርሃን የሆነውን ወደ ልቡ ማሰገባት ነው (ራዕ 3፡20)፡፡ ለእግዚአብሔር ጥሪ ጆሮውንም ልቡንም የሚዘጋ ግን ለመጥፋቱ ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡ «ብርሃን ወደ ዓለም መጣ» እንዲል መዝሙሩ፣ ይህን ብርሃን መጥራት፣ መጋበዝ፣ በርሱም መመላለስና መኖር ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ካልሆነ ግን ወይም ማመናችን ወደዚህ ብርሃን ካላቀረበን ወይም የክርሰቶስ ወገናዊነታችንን ካላመለከተ ጎዶሎ እምነት ነው፤ የምንመላለሰውም በደመዘዘ ብርሃን ውስጥ ነው፡፡
እንግዲህ ክርስትናችን የሰንበት ወይም የዓመት በዓል ክርስትና፣ የአጋጣሚ ክርስትና እንዳይሆን ብርሃን እና የብርሃንም አባት የሆነው ክርስቶስ ጸጋውን ያብዛልን፤ የጨለማን ሥራ አስወግደን በብርሃን እንድንመላለስ የእርሱም ወገኖች እንድንሆን ያበቃን ዘንድ የአምላካችን መልካም ፍቃዱ ይሁንልን! አሜን!

አባ ዳዊት ወርቁ
የካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር








All the contents on this site are copyrighted ©.