2014-10-10 17:26:06

ጸሎት ስናሳርግ ታላቁ ስጦታ መንፈስ ቅዱስ ነው፣


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍርናቸስኮስ ትናንትና በቅድስት ማርታ ቤተ ጸሎት ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ በዕለቱ የተነበበውን ወንጌል መሠረት በማድረግ “ጸሎት ስናሳርግ ብዙ ነገሮች እንጠይቃለን እግዚአብሔር ሊሰጠን ከሚቻለው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ግን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው፣” ሲሉ ሰብከዋል፣
በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ ትናንትና የተነበበው ወንጌል የቅዱስ ሉቃስ ሆኖ ም ዕራፍ 11 ላይ “ለምኑ፥ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፥ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፍትላችኋል። ምክንታቱም የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል” የሚል ክፍል ነበር፣
የእግዚአብሔር ርኅራኄና መሓሪነት የሚገልጠው ይህ የወንጌል ክፍል እኛ ክፉዎች ሳለን ለልጆቻችን መልካም ነገር የምንመኝና የምንሰጥ ከሆንን ሰማያዊው አባታችን ሌትና ቀን ለሚለምኑት ምኑን ያህል አብልጦ እንደሚሰጥና ባለብዙ ምሕረት መሆኑን የገለጡ ቅዱስነታቸው ይህ እጅግ እንደሚያሳስባቸውና እንደሚያደንቃቸው እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፣
“ሁላችን እንደምናውቀው የእግዚአብሔር ርኅራኄ ይቅር በማለት ብቻ አይወሰንም በሚያስገርም ሁኔታ ለጋስና ሁሌ አለምንም ገደም እንደሚሰጥ እንመለከታለን፣ የጠየቅነውን ብቻ ሳይሆን በጸሎት ልንጠይቀው የማንችለውን ይሰጠናል፣ የጠየቅነውን ሁሉ ይሰጠናል፣ ይህ ደግሞ ሁሌ ነው፣ በሰማነው ወንጌል ሶስት ቃላት አሉ፣ ጓደኛ አባት እና ስጦታ፣ እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ጓደኛ ሂዶ በሚጠይቅ ምሳሌ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያስተምራል፣ በሕይወት ዘመናችን ውስጥ ከወርቅ የሚከብሩ ጓደኞች ሆነው የጠየቅነውን የሚሰጡን ጓደኞች ሊኖሩን ይችላሉ፣ እንደዚሁ ዓይነት አንድ ወይንም ሁለት ገፋ ቢልም ሶስት ሊሆኑ ይችላሉ፣ ሌሎችም ጓደኞች ሊኖሩ ይችላሉ ግን እንደምርጦቹ አይደሉም፣ ጌታ ኢየሱስ ከዚህ ወደፊት በመሄድ ስለአባት ይናገራል፣ የትኛው አባት ነው ልጁ እንጀራ ሲለምነው ድንጋይ የሚሰጥ እናንተ እንኳ ክፉዎች ስትሆኑ ይህንን ካደረጋችሁ ሰማያዊ አባታችንስ ሌትና ቀን ለሚለምኑት የማይመልስ ይመስላችኋልን ለሚለምኑት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸዋል ብሎ የጸሎት አስፋላጊነትንና መልሱን በማረጋገጥ ለምኑ ይሰጣችኋል ፈልጉ ታገኛላችሁ መዝጊያውን አንኳኩ ይከፈትላችኋል ይላቸዋል፣
“ታላቁ ስጦታ ይህ ነው እግዚአብሔር ከዚህ በላይ ሊሰጠን አይችልም፣ ስትለምነው እግዚአብሔር ስጦታውን ሸልሞ ነው የሚያቀርብልን፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ይሰጠናል፣ የምንፈልጋቸውን ነገሮች በመዘርዘር እነኚህን ከሰጠኝ ይበቃኛል እንላለን እርሱ ከለመነው በላይ መንፈስ ቅዱስን ይሰጠናል፣ ልመና ከጓደኛ በሕይወትህ አብሮ ከሚጓዝ ከእግዚአብሔር አብ እንዲሁም ከኢየሱስ ጓደኛ ከሆነው ከመንፈስ ቅዱስም ይደረጋል፣ ሲሉ ስብከታቸውን ደምድመዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.