2014-10-08 17:39:11

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ፤


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በብዙ ሺ የሚቆጥሩ ምእመናንና ነጋድያን በተገኙበት የመክፈቻ ጸሎት ካሳረጉ በኋላ ከዮሓንስ ወንጌል “አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ። ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ያውቃሉ፤ የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ …. ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።” (17) የሚለው በኤውሮጳ ዋና ዋና ቋንቋዎችና በአረብኛ ቋንቋ ከተነበበ በኋላ ስለቤተ ክርስትያን አንድነት ይህንን ትምህርት አቅርበዋል፣
ውድ ወንድሞችና እኅቶች! እንደምን አደራችሁ!
እመጨረሻ ላይ ባቀረብክዋቸው ትምህርቶች የቤተክርስትያን መልካመነትና ባህርይ ለማብራራት ሞከርኩኝ፣ የዚህ ሕዝብ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆነችው ቤተ ክርስትያን አባል ለመሆን ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል ብለንም ጠይቀን ነበር፣ እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለብን አንድ ነገር አለ፣ ከእኛ ጋር ያልሆኑ በጌታ ኢየሱስ እምነት የሚሳተፉ ወንድሞች እንዳሉ ነገር ግን ከእኛ ለየት ባሉ ሌሎች አብያተ ክርስትያናትና ማኅበራት እንደሚገኙ መርሳት የለብንም፣ ብዙ ሰዎች በዚህ መከፋፈል ወደቁ፤ በካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ውስጥም ሳይቀር የዚሁ መከፋፈል ሰለባ የሆኑ አሉ፣ እነኚህ መከፋፈሎች በታሪካችን ውስጥ የግጭትና ስቃይ ምክንያት ሆነዋል፣ በሚያሳፍር ሁኔታ የውግያ ምክንያትም ሆነዋል፣ ዛሬም ቢሆን ያሉ ግኑኝነቶች ለመከባበርና ልብ ለልብ ለመቀባበል የሚያበረታቱ አይደሎም፣ ወደገዛ ራሳችን መለስ ብለን እስቲ እኛስ በዚሁ ሁኔታ እንዴት መሆን አለብን ብለን እንጠይቅ፣ እኛስ እላይ እንደጠቅስናቸው በዚሁ መከፋፈል ውስጥ እንገኛለን ወይ! ወይንም የባሰውኑ ምን ቸገረኝ በማለት ቸል እንለዋለን? ወይንም በዕርቅ ጐዳና እስከ የተሟላ ውህደት መጓዝ እንዳለብንና እንደሚቻል በጽናት እናምናለን? ፍጹም ውህደት ማለት በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ሁላችን አብረን ስንሳተፍ ነው፣
በክርስትያኖች ያለው መከፋፈል ቤተክርስትያንን ያቈስላል ክርስቶስን ያቆስላል፤ የኛም መከፋፈል በክርስቶስ ቁስል ላይ እንጨት በመስደድ ቍስሉን መጕዳት ነው፤ አዎን ቤተ ከርስቲያን በክርስቶስ የተመሰረተችና የቆመች ነችና፣ እኛም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቶቹ በሱ ፍቅር እንዲጣመሩ ምን ያህል ፍላጎት እንደነበረው እናውቃለን፣ ይህንንም በዩሐንስ ወንጌል ም.17 ቁ.11 በጸሎቱ እንመለከተዋለን “እኔ ከእንግዲህ ወዲህ በአለም ላይ አልኖርም እነርሱ ግን በአለም ናቸው እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው ቅዱስ አባት ሆይ እነዚህ የሰጠኸኝ እንደኛ አንድ እንዲሆኑ ለእኔ በሰጠኸኝ ስምህ ጠብቃቸው” ይላል፣ እዚህ ላይ የክርስቶስ ሐዋሪያት ክርስቶስ በሕይወት እያለም በእርግጠኛ ሕብረት ሳይሆን የመከፋፈል አደጋም ሊከሰት ይችል እንደነበር ያመለክታል፣ በሉቃስ ወንጌል ም.9 ቁ.46 ከተመለከትን ሐዋሪያት እርስ በእርሳቸው “ከሁሉም ማን ይበልጣል” በማለት ክርክር ይከራከሩ እንደነበር ነው የሚያመለክተው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ደጋግሞ በሕብረት በአባቱ ስም ጸንተን እንድንኖር አደራ ይላል፣ እኛም የዚሁ መልዕክተኞች ምስክርነታችን በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው፤ እርስ በእርሳችንና ከሌሎች ጋር በሕብረትና በፍቅር መኖር ስንችል ብቻ ነው፣ ይህንን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሊረዱት የቻሉት በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታ ነው፣ ለዚህም ነው ሐዋሪያው ጳውሎስ በክርስቲያኖች መከፋፈል እንዳይኖር ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልእክት ቁ. 1 ም.10 “ወንድሞቼ ሆይ መለያየት በመካከላችሁ አይኑር ሁላችሁም ተስማምታችሁ በአንድ ሃሳብና አላማ ጸንታችሁ ኑሩ ብዬ በጌታችን በኢየሱስ ስም እለምናችኋለሁ” ይላል፣
ቤተ ክርስቲያንን ያሳለፈችውን የታሪክ ጉዞዋን ስንመለከት ዲያቢሎስ ቤተ ክርስቲያንን ሊከፋፍላት እንደተፋታተናት ነው፣ አዎን! በቤተ ክርስቲያን ከባድና አሳዛኝ መከፋፈሎች ተከስተዋል፣ እነዚህ አዛሳኝ የቤተ ክርስቲያን መከፋፈሎች ለብዙ ዘመናት በመቆየታቸው ምክንያት ባሁን ወቅት ቤተ ክርስቲያን የተከፋፈለችበትን ምክንያት መወያየትና አንድ ቤተ ክርስቲያን መገንባቱ አስቸጋሪ ነው፣
የተለያዩ ምክንያቾች ሃሳቦችና አመለካከቶች ቤተክርስቲያንን እንድትከፋፈል ሲያደርጉ እነሱም የተለያዩ የዶግማ እምነቶችና ሞራላዊና ንባበ መለኮታዊ ሓዋርያዊ የእረኝነት ተግባር ለኑሮና ለፖለቲካ ጥቅምና ለግል ምቾችና ለስልጣን ሽሚያ ሲያስከትሉ፤ እንዲሁም ጸብና ክርክርን ከሁሉም በላይ ደግሞ የሌላውን ሃሳብ ለመስማትና ለመቀበል ፈቃደኝነት ባለመኖሩ ነው፣ ከዚህም በስተጀርባ ትዕቢትና ራስ መውደድ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፣
ታዲያ እነዚህን የጠቀስናቸው ባሕሪያት በኛም በእያንዳንዳችን ቅድስት እናት ቤተ ክርስልቲያን አባላት ቢገኝም ይህንን እንዴት ነው መከላከል የምንችለው! ምንስ ማድረግ ይገባናል ያልን እንደሆነ ጸሎትን ያለ ምንም ጥርጥር ማቋረጥ እንደማይኖርብን ሁል ግዜ በጸሎት ከፈጣሪያችን ጋር በመገናኘት ጸሎትን የክርስቲያኖች የአንድነት አርማ እናደርገዋለን፣
ክርስቶስ እንድንታደስ የሚጠይቀን በጸሎት ነው፣ ሌላው ክርስቶስ ከእኛ የሚፈልገው ከኛ የተለየ ሃሳብ ያለውን ሁሉን በመቀበልና በጥሞና በማዳመጥ መልካሙን እንድንቀበል ነው፣ክርስቶስ በሚከፋፍለን ነገር ብቻ ሳይሆን ሊያጣምሩን የሚችለውን በማየት በእርሱ ፍቅር ልንጣመርና ፍቅሩን ልንካፈል ይጠይቀናል፣
ይህም እውነትን በመከተልና በሕብረት ይቅር መባባልን ያስከትላል፣ አንዱ ለሌላው በመተሳሰብና በሕብረት እንደ አንድ ቤተሰብ እራሱን በመመልከት በሕብረት መልካም ሥራን በመፈጸም ይደረጋል፣የፍቅር ምልክቱ ይህ ነው፣ መከፋፈል በጣም ጐጂ ነው፣ እኛ ክርስቲያኖች ተከፋፍለናል፤ ግን ሁላችንም አንድ የጋራ ነገር አለን፣ ሁላችንም የምናምነው በጌታችን አየሱስ ክርስቶስ ነው፣ ሁላችንም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፣ ሁላችንም ክርስትያኖች በሕብረት እንጓዛለን፣ ስለዚህ እርስ በእርሳችን እንረዳዳ፣ እናንተስ ይህንን እንዴት ትመለከቱታላችሁ?
በሁሉም ማህበረሰቦች ብዙ የትምህርተ ንባበ መለኮት ሊቃውንት አሉ ሥራውን ለእነርሱ እንተውላቸው ሊቃውንቱ ይወያዩ ንባበ መለኮታዊ እውነትን ያፈላልጉ እኛ ግን አንዱ ለሌላው እየጸለየንና በመልካም ሥራ እየረዳን በኅብረት እንጓዝ፣ ይህ መንፈሳዊ ኤኩመኒዝም ይባላል፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ውስጥ ያለንን ሕይወት አብረን በመጓዝ እናጠነክረዋለን፣ ስለግል ጉዳዮች መናገር ጥሩ ነገር አይደለም ይባላል ሆኖም ግን ይህንን ፈተና ለማሸነፍ አልቻልኩምና ስለ ግል ሕይወቴ ልናገር ፍቀዱልኝ፣ ዛሬ ዕለት የመጀመርያ ቍርባን ካደረግኩኝ ሰባ ዓመት ሆነኝ፣ የመጀመርያ ቍርባን ማድረግ ማለት ምን ማለት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል ከማኅበረ ክርስትያኑ ጋር አንድ መሆን መዋሃድ ነው፣ ይህም ከቤተ ክርስትይናችን አባሎች የሆኑ ወንድማሞችና እኅቶቻችን ጋር አንድ መሆን ማለት ነው፣ ነገር ግን ከወገኖቻችን ብቻ ሳይሆን በጌታ ኢየሱስ በሚያምኑ ሌሎች አብያተ ክርስትያን አባሎችም ጋር አንድ እንሆናለን፣ ጌታችንን ስለ ጥምቀታችንና ስለቍርባናችን እናመስግነው በዚህም የክርስትያኖች ሁሉ መከፋፈል ተወግዶ ወደ ፍጹም አንድነት እንድንመራ ይርዳን፣

ስለዚህ ውዶቼ! በኅብረት እስከ ፍጹም አንድነት እንገስግስ! ታሪክ ብትከፋፍለንም ለዕርቅና ለውህደት እየተጓዝን ነው፣ ይህ እውነት ነው ይህንን መጠበቅ አለብን፣ እኛ ሁላችን ወደ አንድነት እየተጓዝን ነው፣ ምናልባት አንዳንዴ ዒላማው የራቀና ልንደርሰው የማይቻል ሆኖ ሊሰማን ይችላል በዚህም ተስፋ የመቍረጥ ፈተና ያጋጥመናል፣ መዘንጋት የሌለብን ነገር ግን ጌታ ልጁ ሲማጠነው ጆሮውን ደፍቶ ልመናውን ሳይሰማይ እንደማይቀር ማወቅ ያስፈልጋል፣ እሁላቸው አንድ እስኪሆኑ ድረስ እለምናለሁ ብሎ ልጁ ኢየሱስ የለመነውን ሳይመልስለት እንደማይቀር እርግጥ ነው፣








All the contents on this site are copyrighted ©.