2014-09-29 18:58:11

የዓለማችን መጻኢ በወጣቶችና አዛውንቶች መካከል በሚደረገው ግኑኝነት ይወሰናል፣


RealAudioMP3 የዓለማችን መጻኢ በወጣቶችና አዛውንቶች መካከል በሚደረገው ግኑኝነት ይወሰናል፣ የሽምግልና ዘመን የጸጋ ጊዜ ነው፣
ይህንን ያሉት ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከብዙ የዓለማችን ክፍሎች ከተሰባሰቡ አዛውንት በተለይ ደግሞ አያቶችን የሚመለከት ግኑኝነት በማለት ጳጳሳዊ የቤተሰብ ምክር ቤት “የዕድሜ ባለጸጋ የመሆን ቡራኬ” በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው ጉባኤ በተካሄደው የምስክርነትና የጸሎት ጊዜ ነበር፣ በዚሁ ግኑኝነት ልሂቅ ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ አስራስድስተኛም በዚሁ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ነበር፣ ቅዱስነታቸውም በታላቅ አክብሮት እንደተቀበሉዋቸውና ሰላምታ እንዳቀረቡላቸው ተመልክተዋል፣
በአደባባዩ ሁሉም ከተሰበሰቡ በኋላ ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት የመጡ አያቶችና የልጅ ልጆቻቸው ምስክርነታቸውን በመስጠትና ለር.ሊ.ጳ ሰላምታ አቅርበዋል፣
ምንም እንኳ ጊዜው ከባድ ቢሆንም እንዲህ በአንድነት ተሰብስቦ የሕይወት ጌታ የሆነውን እግዚአብሔር ማመስገን ትልቅ ደስታ የሚሰጥ አጋጣሚ ነበር፣ አዛውንቶቹ አብዛኛዎቹ በምርኩስ ተደግፈው እንዲሁም በዊል ቸየር ሆነው በቦታው ማየት እንዲሁም አንዲት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑ አዛውንት በልጆቻቸውና በልጅ ልጆቻቸው ተከበው ዕድሜአቸው 106 ዓመት መሆኑን የሚያሳይ ሰሌዳ ይዘው ስትመለከት ልዩ ስሜት የሚፈጥር ሁኔታ ነበር፣
ቅዱስነታቸው ለቀረበላቸው ሰላምታ አጸፌታውን ሲመልሱ በተልይ ደግሞ በቦታው እንዲገኙ ላቀረቡላቸው ዕድሜ አክበረው እዛው የተገኙት ልሂቅ ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ አስራ ስድስተኛን እንዲህ ሲሉ አመስግነዋል፣
“ደጋግሜ እንደተናገርኩት ልሂቅ ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ አስራስድስተኛ እዚህ ቫቲካን ውስጥ መኖር እጅግ ደስ ያሰኛል፤ በቤት ውስጥ በጥበብ የተካነ አያት እንደመኖር ነው እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ሲሉ በቫቲካን መኖራቸውን እንደ ታላቅ ቡራኬና ጸጋ እንደሚቈጥሩት ገልጸዋል፣
ምስክርነታቸውን ካቀረቡ ቤተ ሰቦች መካከል በኢራቅ ከሚገኘው ስደት ያመለጡና የቃል ኪዳናቸውን 51ኛው ዓመት ያከበሩ ስለነበሩ ለነዚህም ቤተሰብ ልዩ ምስጋና አቅርበዋል፣
“ዛሬ እዚህ መገኘታችሁ ደስ ያሰኛል ለቤተ ክርስትያንም ስጦታ ነው፣ እኛም ቅርበታችን ጸሎታችንና ተጨባጭ እርዳታችንን እንለግሳችኋለን፣ በአዛውንቶች ላይ የሚደረገው ዓመጽ ልክ እንደ የሕጻናቱ ኢሰብአዊ ድርጊት ነው፣ እግዚአብሔር አይተዋችሁም ከእናንተ ጋር ነው፣ በእግዚአብሔር እርዳታ እናንተ ለሕዝባችሁ እንዲሁም ለታላቁ የቤተ ክርስትያን ቤተሰብ ሕያው ታሪክ ናችሁ እንደዚሁም ትቀጥላላችሁ፣ ለዚህም እናመሰግናችኋለን፣ እነኚህ ወንድሞቻችን በፈታኝ ችግር ውስጥም ቢሆን እምነት ያላቸው አዛውንት ፍሬ እንደሚሰጡ አትክልቶች ምስክርነታቸውን ይሰጡናል፣ የዕድሜ በለጸጋ መሆን ቡራኬ ነው፣ በዚህም ጌታ እምነታችንን እንድንጠብቀውና ለትውልድ እንድናስተላልፈው እንዲሁም ጸሎት እንድናሳርግና ምንም ለሌላቸው እጐናቸው እንድንሆን ይጠራናል፣
“በተለይ አዛውንቶች አያቶች ከባድ ሁኔታዎችን ለመረዳት ታላቅ ችሎታ አላቸው፤ ስለዚህ ሁኔታዎች ሲጸልዩም ጸሎታቸው ኃይለኛ ነው ሁኔታዎችን ሊቀይርብ ችሎታ አለው፣ አያቶች የሕይወት ተመክሮአቸው የቤተሰባቸው የማኅበራቸውና የሕዝባቸውን ታሪክ እንዲሁም ክቡር ውርሻ የሆነው እምነታቸው ከትውልድ ለትውልድ እንዲያስተላልፉ ታላቅ ኃላፊነት አላቸው፣
“አያቶቻቸው በቅርብ ያልዋቸው ቤተሰቦች ብፁዓን ናቸው! አያት ሁለት ጊዜ አባትና ሁለት ጊዜ እናት ናቸው፣ የሃይማኖት ስደት እጅግ ጨካን በሆነባቸው አገሮች ውስጥ ለምሳሌ ያህል ባለፈው እሁድ እንደጐበኘኅዋት እንደአልባንያ በመሰሉ አገሮች በድብቅ ሕጻናትን ያስጠምቁና እምነትን ያስተላለፉ አያቶች ነበሩ፣ በስደት ጊዜ እምነትን በእነዚህ አገሮች ያዳኑ እውነቶም ጀግኖች ናቸው፣ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ አዛውንት የሚደግፋቸው ቤተሰብ አያገኙም፣
“ስለዚህ አዛውንትን ለማስጠጋት የሚያገለግሉ ቤቶች ማዘጋጀት እስር ቤት ሳይሆን መኖርያ ቤት እስከሆኑ ድረስ እና ለአዛውንቶች አገልግሎት እንጂ ለሌላ ጥቅም እስካልሆኑ ድረስ የሚደገፍ ነው፣ አዛውንት ተረስተው ተደብቀውና የተተው ሆነው የሚኖሩባቸው መሆን የለባቸውም፣ የአዛውንት ቤቶች የሰው ልጅ ሳንባዎች ሆነው ያረጀናና የደከመውን እንደ ታላቅ ወንድምና እኅት የሚያስታምሙባቸውና የሚጠብቁባቸው የሰው ልጅ መካነ ንግደቶች መሆን አለባቸው፣
“አንድ አዛውንትን መጐበኘት ጤናማ ኅብረተሰብ ይገነባል፣ ልጆቻችሁ ትንሽ የተከዙ ወይንም የደከሙ ሆነው ሲታዩ አያቶቻቸውን እንዲጐበኙ አድርግዋቸው፣ ደስተኞችም ሊሆኑ ነው፣ ሲሉ አያቶች ደስታ እንደሚያመጡ ቢገልጡም የዘመናችን ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታ ግን ነገሮችን ስለለዋወጠው አያቶችና አዛውንቶች በምርትና ትርፍ ዓይን እየተመልከትናቸው እንደማይረቡና ዋጋ ቢስ በመቆጠር ጥግ እንደምስናይዛቸው እንዲያው እንደምንረሳቸው ይህም ታላቅ በደል መሆኑን እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፣
“ይህንን መርዘኛ የሆነ የጥቅም ባህልና አዛውንቶችን የሚያስገልል ሁኔታ እንቃወመው፣ እኛ ክርስትያኖች ከሌሎች ባለ በጎ ፈቃዶች ጋር በመተባበር በትዕግሥት አዛውንቶችን የሚያቅፍና ሰብአዊ በሆነ መንገድ የሚንከባከባቸው እንጂ በአካልም ይሁን በአእምሮ የደከሙትን የማይገልል ልዩ ማኅበረሰብ ለማቆም የተጠራን ነን፣ አያቶቹን የማይጠብቅና የማይከንከባከብ መጻኢ የሌለው ሕዝብ ነው፣ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ በአያት ሲደባበሱ ወይም አንድ ሕጻን አያቱን እንዲደባብስ መተው ስንቱን ደስ የሚያሰኝ ነው፣ ሲሉ በአያቶችና በልጅ ልጆች መካከል ስላለው ግኑኝነት ከገለጡ በኋላ መሥዋዕተ ቅዳሴ ለማሳረግ ጀምረዋል፣
በቅዳሴውም እመቤታችን ድንግል ማርያም ቅዱስ ገብርኤል መል አክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጸንሳ እንተምትወልድ ባበሰራትና ኤልሳቤጥ ዘመድዋም እንደጸነሰች በነገራት ጊዜ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወዲያውኑ ኤልሳቤጥን ለመጐበኘት መሄድዋንና ለሶስት ወር ያህል እንዳገለገለቻት የሚገልጸውን ክፍል በማንበብ የአሮጌዋ ቅድስት ኤልሳቤጥ እና የወጣትዋ ድንግል ማርያም ግኑኝነት ትውልድን ከትውልድ ጋር እንዴት እንደሚያተሳስር ለዝምድናም ኃይል እንደሚሆን አመልክተው ባለነው ዘመን ወጣቶች በተለያዩ የታሪክና የባህል ምክንያት ዘመዶቻቸውስ ይቅር ከወላጆቻቸውም ርቀው ነጻው ሆነው ለመኖር ሲጥሩ ማያት እንዴት እንደሚያሳዝን አሳስበዋል፣ ይሄው አብዮታዊ ወጣት ስንት ሃብት እንደሚያጠፋ አያውቅም፣ የቤተሰብ መጠሳሰር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም ኤልሳቤጥንና ዘካርያስን ብታገልግላቸውም ከሁለቱ አዛውንቶች ብዙ ጥበብ እንደዘገበች ይህም እንደ ሴትልጅ እንደእጮኛና እንደ እናት ሕይዋን ለመምራት ረድቶታል፣
“እንዲህ በማድረግም እመቤታችን ድንግል ማርያም መንገዱን ማለትም በወጣቶችና በአዛውንቶች ያለውን የመገናኛ መንገድ ታሰያናለች፣ የአንድ ሕዝብ መጻኢ በእንዲህ ዓይነት ግኑኝነት ይመሠረታል፣ ወጣቶቹ አዛውንቶች እንዲያው በአጠቃላይ ዘመደአዳም ሁሉ ወደፊት እንዲገሰግሱ ኃይል ይሰጥዋቸዋል፤ አዛውንቶቹም ይህንን የወጣቶች ኃይል በዝክርና በጥበባቸው እጅግ እንዲሚጐለበት ያደርጉታል፣ ሲሉ ካስተማሩ በቅዳሴው ፍጻሜ የመል አከ እግዚአብሔር ጸሎት ካሳረጉ በኋላ ቅዳሜ ዕለት በእስፓኛ በማድሪድ ከተማ ስለተፈጸመው የአቡነ አልቫሮ ደል ፖርቲሎ የኦፑስ ደይ መሥራች የነበሩ የቅዱስ ኾሰማርያ ኤስሪቫ ደ ባላግወር ተከታይ አለቃ የነበሩ ሥር ዓተ ብፅ ዕና በማስታወስ የብፁዑ ክርስትያናዊና ክህነታዊ ምስክርነት ለሁላችን ለክርስቶስና ለወንጌሉ ተገዢዎች እንድንሆን ይርዳን ሲሉ ካሳሰቡ በኋላ እፊታችን እሁድ የሚጀምረውን ስለቤተሰብ የሚወያይ የጳጳሳት ሲኖዶስ ስኬታም እንዲሆን ሁላችን እንድንጸልይ አደራ ብለዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.