2014-09-08 16:58:44

በእግዚአብሔር ፊት ሁላችን ኃጢአተኞች ነን የእግዚአብሔር ምሕረትም ያስፈልገናል:


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና እኩለ ቀን ላይ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት የዕለቱን ቃለ ወንጌል በመመርኰዝ “በእግዚአብሔር ፊት ሁላችን ኃጢአተኞች ነን የእግዚአብሔር ምሕረትም ያስፈልገናል” ሲሉ ካስተማሩ በኋላ ለኡክራይናና ለለሶቶ ሰላም እንዲሁም በኢራቅ የሚሰደዱትንም መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፣
ባለፉት ቀናት በለሶቶ የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት እንዳሳሰባቸው በመግለጥ እንዲሁም ለወራት በኡክራይና እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት በተደረገው የተኵስ ማቆም ስምምነት እንዲገታና ለሁላቸውም ሰላም እንዲወርድ ሁላችን መጣር እንዳለብን እንዲህ ሲሉ አሳስበዋል፣
“ኡክራይናና ለሶቶ ምንም እንኳ አንዱ ከአንዱ እጅግ የራቁ አገሮች ቢሆኑ ባሁኑ ጊዜ ግን በዓመጽና በግፍ ተቀራርበዋል፣” ሲሉ በብርቱ ሥቃይ ለሚገኙ ሕዝቦቻቸው ቅርበታቸውን የገለጡ ቅዱስነታቸው በተለይ በዚሁ ቀናት በምሥራቃዊው የኡክራይን ክፍል ያለውን ግጭት ለማብረድ የተደረገው የተኵስ ማቆም ስምምነት አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፣
“እነኚሁ ስምምነቶች ለሕዝቡ እርካታ የሚሰጥና ለነዋሪ ሰላም ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው እመኛለሁ፣ የተጀመረው ውይይት ቀጣይ እንዲሆንና ተስፋ የተደረገለትን ፍሬ እንዲያስገኝ እንጸልይ፣ የሰላም ንግሥት የሆንሽው እመቤታችን ድንግል ማርያም ሆን ለምኝልን! የለሶቶ ጳጳሳት ካደረጉት ጥሪ ጋር ድምጼን በመጨመር በአገሪቱ ሰላም እንዲነግሥ እመኛለሁ፣ ማንኛውን አመጽ ሳውግዝ ጌታ በለሶቶ ግዛት በፍትሕና በወንድማማችነት ሰላም እንዲያነግስ እጸልያለሁ፣ ሲሉ ለሰላም ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል፣
በሌላ በኩል ደግሞ የኢጣልያ ቀይ መስቀል በኢራቅ ለሚገኙ ችግረኞችና ስደተኞች ለመርዳት ኤርቢል በተባለው ቦታ እርዳታ ይዞ ስለሚሄድ ምስጋናቸውን እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፣
“ለዚሁ ተጨባጭ የልግሥና ተግባር ምስጋናየን ሳቀርብ ለእነኚሁ በስደትና በጭቆና ለሚገኙ ወንግሞቻችን ለመርዳት ለተነሡ ሁላቸው እባርካለሁ፣ ጌታ ይባርካችሁ! ብለዋል፣
እላይ እንደተጠቀሰው ቅዱስነታቸው ይህንን ጥሪ ከማቅረባቸው በፊት የዕለቱን ቃለ ወንጌል በመመርኮዝ የተሳሳተ ወንድማችንን እንዴት በት ዕግሥት መምከር እንዳለብን የሚገልጠውን እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል፣
“በወንጌል ውስጥ ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ የሚለው ወሬ ከማብዛትና ሕሜታ ከመንዛት ይልቅ ብቻችሁ አንተና እርሱ ሆናችሁ ምከረው ለማለት ነው፣ ይህ ለወንድሞቻችን ማሳየት ያለብን የትሕትናና የመተማመን ዝንባሌ መሆን አለበት፣ በተለይ ደግሞ የበደለንን ወንድማችን በምናነጋግርበት ጊዜ ከሚያቈስሉና ሊገድሉ ከሚችሉ ቃላት መቆጠብ አለብን፣ ምክንያቱም እንደምታውቁት የሚያቈስሉ ሊገድሉም የሚችሉ ቃላት አሉና፣ ወንድሜን ሳማው የማይሆን ፍርድ ላይ በእርሱ ሳስተላልፍ ወንድሜን እገድላለሁ ማለት ነው፣ ስም ማጥፋት እንደመግደል ነውና፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብቻውን ማነጋገር ማለት ኃጢአተኛ ከኃጢአት እንዲመለስ ብቻውን በለሰለሰ ቃና ስትናግረው ከሞት ታድነዋለህ ለማለት ነው፣ ይህን ለወንድሞቻችን ስናደርግ እኛም ከቂመ በቀልና ከቁጣ እንደምንድንም መረዳት ያስፈልጋል፣
“ይህ ተግባር እኛንን ከቁጣና ከቂመ በቀል ነጻ እንድንሆን ይረዳናል፣ እነኚህ ነገሮች ልባችንን በማቍሰል ከማሰቃየት ወንድማችን እንድንሰበው እንድምናቍሰለው ስለሚደርጉን መጥፎ ነገሮች ናቸው፣ ከአንድ ክርስትያን አፍ ስድብና የሚያዋርዱ ቃላት ሲወጡ ማየት እጅግ አስቀያሚ ነው፣ ይህንን ተረዱት ልብ ብላችሁ ስሙኝ መሳደብ የክርስትያን አይደለም፣ በእግዚአብሔር ፊት ሁላችን ኃጢአተኞች ነን ምሕረቱም ያስፈልገናል፣ ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳትፈርዱ ብሎ የሚያዘን፣
“በቅዱስ ቍርባን ዙርያ የሚሰበሰቡና የሚጸልዩ ክርስትያኖችን የሚያመሳስልዋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፣ ሁላቸው ኃጢአተኞች ናቸው ሁላቸውም ምሕረት ያስፈልጋቸዋል፣ ወንድማችን ለመምከር በምንሄድበት ጊዜ ሁሌ እነዚህን ነገሮች እናስታውስ፣ ሲሉ ካስተማሩ በኋላ ዛሬ ዕለት የሚታወሰውን የእመቤታችን ድንግል ማርያም በዓለ ልደታ በማስታወስም፤ “አንዲት እናት ዕለተ ልደትዋን ስታከብር ምን ይድረጋል? ሰላምታ ያቀርቡላታል፤ እንኳን አደረስሽም ይሏታል፤ ስለዚህ በዚሁ የእመቤታችን ድንግል ማርያም በዓለ ልደታ ከልባችሁና ከከንፈሮቻችሁ ሰላምታ በማቅረብና እንኳን አደረሰሽ በማለት ከውሉድ በሚቀርበው ሰላምታም “በሰላመ ቅዱስ ገብርኤልን አቅርቡላት” ሲሉ ትምህርታቸውን ካቀርቡና የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካሳረጉ በኋላ ሓዋርያዊ ቡራኬ በመስጠትና መልካም ምሳ በመመኘት ሕዝቡን ሸኝተዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.