2014-07-02 16:12:39

የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክት፣ ክፍል ሁለት።


RealAudioMP3 ለአንድ ዓመት ሲከበር ቆይቶ የተገባደደውን የእምነት ዓመት በስፋት የተመለከተው የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክት እንደሚለው ዓመቱ ለእምነት ጉዞአችን ብርታትን አግኝተን ባዲስ ስሜት እንድንነሳሳ ልዩ ፍላጎት አሳድሮብናል። ስለዚህ የእምነት ዓመት መታየት ያለበት መገባደጃው ሳይሆን ላለፉት ዓመታት እምነታችን ያስገኛቸውን ፍሬዎች እንደ መሣሪያ ታጥቀን የሕይወትና የእምነት ጉዞ የምንጀምርበት መሆን አለበት። በእምነታችን ውስጥ ያለውን ደስታ ዓይነቱንና መጠኑን እንደገና ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። በሚያምኑትና በማያምኑት ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ምን እንደሆነና ምን ያህልስ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፤ የእምነት ስጦታ እንዲኖረን የሚያደርጉ መለኮታዊ የውስጥ ፍላጎቶች የትኞቹ ናቸው? የእምነት ማነስን ወይም ጨርሶ የእምነት ማጣትን ሊያመላክተን የሚችል ምን ያህል የደስታ መጠንና ዓይነት ይጎድላል? ያለዚህ ስጦታ ሕይወታችን መጨረሻው በማይታወቅ ባሕር ውስጥ እንድንገባና የጉዞአችንን አቅጣጫ መሳት ብቻ ሳይሆን መነሻችንንና መድረሻችንን ሳናውቅ እንቀራለን። ለሁሉም ነገር ገደብ አለው። እምነት ላለው ሰው እግዚአብሔር ለፍጥረታቱ ሁሉ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ተጠሪ እንደመሆኑ፣ እኛንም የራሱን ሃላፊነት በጋራ እንድንወጣው ይጋብዘናል።
ያለ እምነት በሰው ልጅ ላይ የሚደርሱ ሕመሞችና በደሎች ትርጉም ሊኖራቸው አይችልም። በእምነት በኩል እግዚአብሔር ራሱ የስቃይተኞችን እንባ ከዓይናቸው እንደሚጠርግ፣ ሰውም ሁሉ የእርሱን ማዳን እንዲያይና እርግጠኛ እንዲሆን ይነግረናል። ያለ እምነት መልካም የተባሉት ሁሉ፦ ሕይወት፣ ፍቅር፣ ስምምነት፣ ምሕረት፣ እርስ በርስ መረዳዳትና በጎነት የሰውን ግብረ ገብ የመግዛት አቅም የላቸውም። ነገር ግን እምነት ካለ መልካም ሥራዎቻችን በሙሉ ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለመውረስ የመጀመሪያ እርምጃዎቻችን ናቸው። እምነት ካለ እግዚአብሔር በቸርነቱ እና በአዳኝነቱ ለሰዎች መልካም ሥራ በሙሉ ባለቤቱና መሠረቱ እርሱ ነው፤ በሥራዎቻችን ሁሉ የእምነታችን መሪና ፈጻሚ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ያለ እምነት ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜና የግንኙነቶችም ማብቂያ ነው። ነገር ግን እምነት ካለ ሞት የምድራዊ ሕይወት ማብቂያ፣ በእግዚአብሔር ሙሉ ሕይወት መጀመሪያ እና ቀድሞ በሞት ከተለዩን ሰዎች ጋር ኅብረት የምንመሠርትበት ዕድል ነው።
እምነት ከሌለ ዓለምም ቢሆን በአጋጣሚ የተገኘ፣ ሕይወታችንም እንደ ሣር ደርቆ የሚጠፋ ገለባ፣ ጉዞአችንም ውጤት አልባ ሆኖ ይቀራል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ እምነት ካለን በውበት ስለመፈጠራችን መሠረቱ፣ በወንድማማችነት ፍቅር ስለመተሳሰራችን ምክንያቱ፣ የመጨረሻ ግባችን እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ እንገነዘባለን። ሕይወት በብዙ ችግሮችና ስቃዮች መካከል ቢገኝም እግዚአብሔር ዘወትር በሚሰጠን ሃይልና ብርታት መጽናናትን ያገኛል። ቅዱስ በርናርድ እንደሚለው እያንዳንዱ ነገር ኢየሱስ ክርስቶስ ገብቶበት ካላጣፈጠው በቀር ኮምጣጣና መራራ ሆኖ ይቀራል። መንገድ፣ እውነትና ብርሃን በሆነው በኢየሱስ ላይ ያለን እምነት ለሕይወታችን ብርሃንና መሪ ይሆነናል። ጽኑ እምነት ከሌለን መጽናትን አናገኝም፤ በጨለማ ውስጥ ተቅበዝብዘን እንዲሁ እንጠፋለን።
ዓለምን የምናሸንፈው በእምነታችን ነው ስንል ዓለምን መጥላታችን ወይም ማንቋሸሻችን ሳይሆን ነገር ግን በዓለም ውስጥ ያለውን ኩራት፣ ጥላቻ፣ ኃጢአትና ጊዜያዊ የሆኑ ምድራዊ ነገሮችን ሁሉ ማሸነፍ የምንችለው ወደ ሙሉ ሕይወትና ደስታ ከሚመራን ከአምላካችን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሲኖረን ነው። በእምነት በኩል የእግዚአብሔር አምሳያነታችን ይገለጣል። በእምነት በኩል የአንድ እግዚአብሔር ልጆች፣ ወንድማማቾችና እህትማማቾች መሆናችንንና በዚህም አንዱ ሌላውን ለመርዳት ዝግጁዎች መሆናችንን እንገነዘባለን። በእርግጥ እግዚአብሔር ሰዎችን በራሱ አምሳል ፈጥሮ የማይጠፋ ሕይወት ስለሰጠ “ወንድምህ የት አለ?” ብሎ መጠየቅን አያቋርጥም።
ሰው በሃይማኖት ላይ ከሚነሱ ችግሮች ራሱን ሊያገልል አይችልም። ስለዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ የማያቋርጥ ድጋፍ ያስፈልገዋል። በዘመናችንም ይህን ሃቅ የሚያረጋግጡ ገጠመኞችን እናያለን። ሰው ሁል ጊዜ ስለ ሕይወቱ ትርጉም፣ ስለ ሥራውና ስለ ሕይወቱ መጨረሻ ማወቅ ይፈልጋል። ቅዱሱ አባታችን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እንዳሉት፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅና አለማወቅ አንድ አይደለም፤ እንደዚሁም ከእርሱ ጋር መጓዝና ያለ እርሱ ዓይናችንን ጨፍነን መጓዝ አንድ አይደለም። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንሆን ሕይወት ሙሉ እንደሚሆንና ከእርሱ ጋር ስንሆን ለእያንዳንዷ ነገር ትርጉም ማግኘት ቀላል እንደሆነ እናውቃለን።
የወንጌልን ብርሃን በምድራችን ሁሉ አንድታበራ ተልዕኮ ያላት ቤተክርስቲያን፣ እምነት የዚህን ዓለም ስቃዮች ላለመርሳት እገዛ እንደሚያደርግ ታስተምረናለች። እምነት ወደ ጨለማ ስፍራ ብቻ የሚሰራጭ ብርሃን ሳይሆን ጨለማውንም እየመራን እስከ ጉዞአችን ፍጻሜ የሚሸኘን ኩራዝ ነው። የእግዚአብሔር ዓላማ ለሚሰቃዩት ሁሉ የስቃዮቻቸውን መንሰኤ ማስረዳት ሳይሆን ከሚሰቃዩት ጋር አብሮአቸው በመሆን ስቃያቸውን ወደ ብርሃን መግለጥ ነው። እግዚአብሔር ራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የስቃይ ጉዞአችንን አብሮን በመጓዝ በዚህ ጉዞ መካከል ብርሃንን ማየት እንድንችል ያግዘናል። በዚህ መልክ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር “ወንድምህ የት አለ?” ብሎ የጠየቀውን ጥያቄ እንድንቀበል አደራ ትለናለች። እኛም የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ይህን ጉዳይ በአንክሮ የተመለከትነው ማንነትን ለመግለጽ ወይም የግል ፍላጎትን ለማንጸባረቅ ሳይሆን ሐዋርያዊ እረኞች እንደመሆናችን መጠን፣ ሕዝባችንን በእውነትና በግልጽነት ለማገልገል ባለን ጽኑ ፍላጎት ነው። በእርግጥም የተደላደለና የጋራ የሆነ እውነተኛ እምነት፣ ዓለምን ለመለወጥ፣ መንፈሳዊ እሴቶችን ለሌሎች ለማስተላለፍና ምድርን ከነበረችበት አውጥቶ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሁል ጊዜ ጽኑ ፍላጎትን ይጠይቃል ይላል የጳጳሳቱ መልዕክት።
በእምነት ብርሃን ማየት ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የመጣውን ታላቅ ስጦታ መቀበል ማለት ነው። ከእግዚአብሔር በተሰጠን የእምነት ስጦታ አማካይነት ወደር የማይገኝለት ፍቅር እንደተሰጠን፣ መልካም የምሥራች ቃል እንደተነገረን፣ ይህን የምሥራች ቃል ስንቀበል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መገለጡን፣ በመንፈስ ቅዱስ መለወጣችንን፣ የወደፊት ጉዞአችን በብርሃን የታገዘ እንደሚሆንና ይህን ጉዞ በተስፋ ደስ እያለን መጓዝ እንደምንችል እናምናለን። ስለዚህ እምነት፣ ተስፋና ልግስና በክርስትና ሕይወት ውስጥ ከእግዚአብሔ ጋር ለምንመሠርተው ሙሉ አንድነት አጋዦቻችን ናቸው። ነገር ግን እምነት የሚከፍትንል መንገድ ምን ይመስላል? ለተዋጣና ፍሬያማ የሕይወት ጉዞ መብራት ምንጩ የት ነው?
ከረጅም ጊዜ ጅምሮ ዛሬም ወደ ልብ ጠልቆ ገብቶ የሰውን ልጅ ሁኔታ ለማወቅ ሲባል ለተለያዩ ሃይማኖቶች የሚቀርቡ ያልተፈቱ እንቆቅልሾች ወይም ጥያቄዎች አሉ። እነርሱም፥ ሰው ማነው? የሕይወታችን ትርጉምና ዓላማ ምንድር ነው? መልካም ስነ ምግባር ምንድር ነው? ኃጢአት ምንድር ነው? ስቃይ ከየት የማጣና ለምን አስፈለገ? ወደ እውነተኛ ደስታ የሚወስደው መንገድ የቱ ነው? ከሞት በኋላ የሚከፈል ዕዳ እና የመጨረሻ ፍርድ ምንድር ናቸው? የሚሉ ናቸው። በመጨረሻም በጊዜአችን የሚቀርቡ የሕይወትና የሞት እንቆቅልሾች፣ ኃጢአትና መከራ መልስ ሳያገኙ ቀርተው የሰውን ልጅ ያስጨንቁታል።
ይቀጥላል....








All the contents on this site are copyrighted ©.