2014-06-28 17:50:51

ሰንበት ዘአስተምህሮ 2006 ዓ.ም. ሰኔ 22 2006 ዓ.ም (6/29/2014)


«ከዚያም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፡ የሠርጉ ድግስ ዝግጁ ነው ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሠርጉ ድግስ ጥሩ» (ማቴ 22፡8-9)፡፡
RealAudioMP3 ይህ የወንጌል ንባብ ለዘመኑ አማኝ ምን ዓይነት ትምህርት ያስተላልፋል?
እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ዕድል ሁልጊዜ ለተመረጠው ሕዝብ ይሰጣል፡ ምክንያቱም የኔ ሕዝብ ብሎ የተማማለበት ስለሆነ፤ በቃሉም እንዲህ ነው የሚለው፡- «እናንተ ሕዝቤ ትሆናላችሁ እኔ አምላካችሁ እሆናለሁ» (ዘጸ 6፡7፤ ዘሌ 26፡12፤ ኤር 30፡22)፡፡ በዛሬው ወንጌል ግን የተጠሩት ሰዎች ስንኩል በሆነ ምክንያት ለጋባዡም ሆነ ለግብዣው ቁብ ሳይሰጡ ወደየተግባራቸው ተሰማሩ፡፡ እኛስ ስንት ጊዜ የእግዚአብሔር መልክተኞች፣ጥንታውያኑ አባቶቻችን፣ጳጳሳቱ፣የቅድስና ሕይወት ይኖሩ የነበሩት ካህናትና አሁንም በስብከተ ወንጌል ተግባር ላይ የተሰማሩ አገልጋዮች ወደ እግዚአብሔር የመዳን አዳራሽ፣ ወደ መንግስተ ሰማይ ገበታ ጠርተውናል? አዎን እግዚአብሔር ወደ ነፃነት ይጠራል፣ ወደ እረፍት ይጠራል፣ወደ ብርሃን ይጠራል፡፡ ግን ስንት ጊዜ በተለያየ ምክንያት ለዚህ ጥሪ ጆሮአችንን ደፍነናል፣ከቅዳሴም ይሁን ከተለያዩ መንፈሳዊ ትምህርቶች ቀርተናል፣ ስንት ጊዜስ ወደ ጥፋት የሚወስደውን መንገድ የሙጥኝ ብለን ይዘነዋል? የእግዚአብሔር ጥሪ «ተመለሱ፣ ኑ ወደ እረፍት» የሚል ነው፡፡ ካልሆነ ግን እግዚአብሔር የሰው ድሃ ሆኖ አያውቅምና፣ወንጌልም ተማሪ አጥታ አታውቅምና፣አማኝም ጠፍቶ አይጠፋምና በተሰጠን ጊዜ እና ዕድል ካለተጠቀምን ይህ በረከት ከእኛ ተወስዶ ለሌላው ይሰጣል፤ ቀድሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ ያልነበረው እግዚአብሔር ራሱ «ሕዝቤ» ብሎ በመጥራት (ሆሴ 1፡10፤ 2፡23) ለኛ የተዘጋጀውን የመዳኛ ፀጋ ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ የሚባክን ጊዜ የለምና ተራ ምክንያቶቻችንን ትተን ወደዚህ አምላክ እንጠጋ፤አሉታዊ ሳይሆን አወንታዊ ምላሻችንን እንስጠው፤ እርሱ ደግሞ እኛነታችንን በአዲስ መንፈስ ሸልሞ እና ሙሉ አድርጎ ለዘለዓለማዊ ሕይወት ዝግጁ ያደርገናል፡፡
ሠላም ወሰናይ

አባ ዳዊት ወርቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን








All the contents on this site are copyrighted ©.