2014-06-26 10:56:02

የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዐን ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክት።


RealAudioMP3 ግንቦት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. አራቱ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዐን ጳጳሳት “ወንድምህ የት አለ?” በሚል ርዕሥ ከአስመራ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት ትርጉም የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ ቀጥሎ እናቀርብላችኋለን።
በእምነት እውነተኛ ልጆቻችን ለሆናችሁና በጎ ፈቃድ ላላችሁ ሰዎች በሙሉ፣ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ለእናንተ ይሁን። በፋሲካ ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአትና በሞት ላይ ድል የተቀዳጀበትን እውነት ስናስታውስ፣ ቀድሞ በጨለማ ከምትኖሩበት ወጥታችሁ አሁን ግን ኢየሱስ ክርስቶስ አብዝቶ የሰጠን ጥበብና ማስተዋል እንዲኖራችሁ እንመኛለን።
በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች ሆይ! እምነታችን በተስፋ የምንጠባበቃቸውን ቡራኬዎች እንደምንቀበል የሚያረጋግጥልን፣ የማናያቸውም ነገሮች ስለመኖራቸው የሚይስረዳን ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም በሙሉ በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ የምናውቅበት መንገድ ነው። በዓለማችን ለሚሆኑት ነገሮች በሙሉ ትክክለኛ ትርጉማቸው ተገልጠውልን የምንረዳው በእምነት ብርሃን በኩል ነው። እኛም በዚህ እምነት በመታገዝ ይህን ሐዋርያዊ መልዕክት እንልክላችኋለን።
በርካታ ስዎች ለአጠቃላይ ሰብዓዊ ዕድገት ባላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ከእምነታቸው ርቀዋል። ሁል ጊዜ በጸሎታችን እያስታወስናችሁ በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። በእምነታችሁ ምክንያት እንዴት እንደምትሠሩ፣ በፍቅራችሁ ምክንያት እንዴት እንደምትደክሙና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁ ተስፋ እንዴት የጸና እንደሆነ በ አምላካችንና በአባታችን ፊት ያለማቋረጥ እናስታውሳለን። በቅርቡ የተገባደደው የእምነት ዓመት ብዙዎቻችንን የሕይወት ልምዳችን ምን ይመስል እንደነበር በጥልቀት እንድንረዳ አግዞናል። እምነትም የሰዎችን ሕይወት በሁሉም አቅጣጫ እንዴት እንደሚያሳድግ ግልጽ ሆኖናል።
የእምነት ዓመትን በታላቅ ስሜት እንድንጀምረው ጸጋን አግኝተናል። መንፈሳዊ ጉዞአችንን በእርጋታ እንድናሰላስል፣ ወደ አምላካችን እንድንጸልይ፣ ለስሙም ምስጋናን እንድናቀርብና የበደሉንን ይቅር እንድንል መልካም አጋጣሚን አግኝተናል። በተጨማሪም በአባቶቻችን ታላቅ እምነት የተነሳ በጎ ስጦታ የሆነልን የሰገነይቲ ኤጳርቃ ሊቋቋም ችሎአል። ለዚህም ሁሉ ደስታን የተሞላ የምስጋና ዜማን ወደ እግዚአብሔር አምላካችን እናቀርባለን።
የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክት 16ኛ የእምነት በር በሚለው የግል መሪ ቃላቸው፣ ለመላዋ ቤተክርስቲያንና ለእኛም ሐዋርያዊ መሪዎችዋ፣ ይህን የምንኖርበት ዘመን ከልብ በመገንዘብ እንዲህ በማለት አስተያየታቸውን ለግሰው ነበር። መላዋ ቤተክርስቲያንና መሪዎችዋ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝቦችን ሕይወት ከሌለበት በረሐማው ሥፍራ አውጥተው ሕይወት ወዳለበትና ሕይወትን አትረፍርፎ ከሚሰጠው ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር ወዳጅነትን ወደሚመሠርቱበት ሥፍራ መምራት ይኖርባቸዋል። ብዙን ጊዜ ክርስቲያኖች የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የሚሏቸውን ለይተው ለማወቅ እምነትን ይጠቀሙ ነበር። ዛሬ ይህ መሆኑ ቀርቶ ከእምነት የምናገኛቸው መልሶች በሙሉ ችላ እየተባለላቸው ነው። ከዚህ በፊት የስዎች የጋራ ባሕል የሚመሠረተው ከእምነት የሚገኙትን እሴቶች ጨምሮ እንደሆነ ማየት ይቻል ነበር። ዛሬ ግን በእምነትም ላይ ከፍተኛ ውድቀት ስለደረሰ የብዙዎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ እናያለን።
ስለዚህ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክት 16ኛ በእምነት ዓመት እንዳሳሰቡት ሁሉ እምነት ላይ ከባድ ውድቀት በደረሰበት ባሁኑ ዘመን እኛ በእምነታችን ጠንክረን መቆም ይኖርብናል፤ ይላል የጳጳሳቱ ሐዋርያዊ መልዕክት። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቅርብ ረዳቱና የሥራ ተባባሪው ለሆነው ለወጣቱ ጢሞተዎስ፦ “ከልጅነትህ ጀምሮ ከወጣቶች ክፉ ምኞት ሽሽ፤ በንጹህ ልብ ጌታን ከሚጠሩ ሰዎች ጋር ሆነህ ጽድቅን፣ፍቅርን፣ ሰላምን ተከታተል” እንዳለው እኛም የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዐን ጳጳሳት፣ ማንም በእምነቱ እንዳይዝልና እንዳይታክት የማበረታታት ሐዋርያዊ አደራና ጥሪ አለብን።
የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች ሆይ! እምነታችሁ እንዳይጠፋ በጸሎታችን እንድንደግፋችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ወንድሞች በእምነታቸው ይበረቱ ዘንድ ድጋፍ እንዲሆንላቸው ብሎ ያቀረበው ማሳሰቢያ ለእኛም ጭምር ደርሶናል። “ከቅዱስ ወንጌል የሚገኝ ደስታ” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍርራንሲስ ሐዋርይዊ መልዕክት በሥሩ “ወንድምህ የት አለ?” የሚለውን የእግዚአብሔርን ጥያቄ በማስታወስ ለእኛም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦልናል። የወንድሞቻችን በርካታ ችግሮችንና ስቃዮችን አብረን ለመሸከም በማሰብ፣ ከእምነት የሚገኘውን ደስታ ተካፋዮች እንድንሆን፣ እምነታችን የሚገልጥልንን ድንቅ ሥራ ተመልክተን ለመመስከርና በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ሥራ በእምነታችን ታማኝና ጽኑዎች እንድንሆን በማለት ይህን ሐዋርያዊ መልዕክት እንጽፍላችኋለን። ይቀጥላል....








All the contents on this site are copyrighted ©.