2014-05-24 19:09:11

የር.ሊ.ጳ ሁለተኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ዑደት በመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች፣


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች በዮርዳኖስ በፍልስጥኤም እና በቅድስት መሬት በቤተ ልሔም እስራኤል ውስጥ ሐዋርያዊ ዑደት ለማድረግ ዛሬ ቅዳሜ እ.አ.አ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓም ጥዋት በሮም ሰዓት አቆጣጠር ስምንት ሰዓት ከሩብ ከፍዩሚቺኖ ዓለም አቀፍ የሮም አውሮፕላን ማረፊያ ተነሡ፣
ቅዱስነታቸው ዘወትር እንደሚያደርጉት ትናንትና ማምሻውን በሳንታ ማርያ ማጆረ ባዚሊካ በመሄድ ይህንን ጉዞ ለእመቤታችን ድንግል ማርያም በማማጠን ጉዞው የተሳካና ፍሬ ያለበት እንዲሆን በእመቤታችን መንበረ ታቦት ተንበርክከው ለረጅም ጊዜ ጸሎት እንዳሳረጉ ከቅድስት መንበር የወጣ ዜና አመልክተዋል፣
ቅዱስነታቸው የመንበረ ጴጥሮስ ሥልጣን ከተረከቡ ወዲህ ይህ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉዞ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የሚደረገው፤ አንደኛውና የመጀመርያው ባለፈው ዓመት ለዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን ለማክበር ወደ ብራዚል ሪዮ ዲ ጃነሮ ያደረጉት ጉዞ መሆኑ የሚታወስ ነው፣
የአሁኑ ሐዋርያዊ ጉዞ ዋና ዓላማ የእምነት ንግደት ሆኖ የዛሬ ሓምሳ ዓመት በቅርብ ጊዜ ብፅዕነታቸው እንዲታወጅ የምንጠባበቀው ነፍሰኄር ር.ሊ.ጳ ጳውሎስ ስድስተኛና የቍስጥንጥንያ ፓትርያርቅ የነበሩ ብፁዕና ቅዱስ አተናጎራ በኢየሩሳሌም የተደረገው የመጀመርያው የተዋህዶና የካቶሊካ ግኑኝነት ለአብያተ ክርስትያን አንድነት መሠረት የሆነውን ግኑኝነት ለማስታወስ እና ስለአከባቢው ሰላም ለመጸለይ መሆኑም ተመልክተዋል፣ ያ ከአምሳ ዓመት በፊት የተደረገው ግኑኝነት በኦርቶዶክስና በካቶሊክ መካከል የነበረውን ልዩነት ለማጥበብና ይቅሬታ ለመለዋወጥ እንዲሁም በሁሉቱም አብያተ ክርስትያን መካከል የነበረውን ውግዘትን ለማንሳት ነበር፣
ቅዱስነታቸው ዛሬ ጥዋት ከለዮናርዶ ዳ ቪንቺ አለም አቀፍ የአየር ማረፍያ ሲነሱ የቤተ ክርስትያንና የኢጣልያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሸኝዋቸዋል፣ ከሶስት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ የበረራ ጊዜ በኋላ አማን ሲደርሱ ታላቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል ከቤተ መንሥት ባለስልጣናትና ከንጉሳዊ ቤተሰብ ከተገናኙና የተለያዩ ዲስኩሮች ከቀረቡ በኋላ በዮርዳኖስ ወንዝ አከባቢ በሚገኘው ሜዳ መሥዋዕተ ቅዳሴ አሳርገዋል፣ ማምሻውን በ2009 ዓም ልሂቅ ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ መሠረት ያኖሩበት ቤተ ክርስትያን ተሳልመው በአከባቢው የሚገኙ ከ600 በላይ የሚሆኑ ስደተኞችና በሽተኞች ጋር ተገናኝተው ወደ ሚያድሩበት ቦታ ተጉዘዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.