2014-05-05 13:42:07

የእግዚአብሔር ቃልና ቅዱስ ቍርባን ብደስታ ይመሉናል፣


RealAudioMP3 ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የንግሥተ ሰማያት ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት በዕለቱ ቃለ ወንጌል የተመለከተውን እስከ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩ ሐዋርያት ጌታ ኢየሱስ በቃሉና በቅዱስ ቍርባን ተገልጦላቸው ያገኙትን ደስታ በማመልከት ዛሬም ቢሆን ቃለ እግዚአብሔርና ቅዱስ ቍርባን በደስታ እንደሚሞሉን ገልጠው በዩክረይን ተከስቶ ያለው ሁኔታ በእርጋታና በሰላም እንዲፈታ የሰላምና የወንድማማችነት መንፈስ እንዲዳብር እንዲሁም በአፍጋኒስታን ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት በተጉዱ ወገኖች እጅግ እንዳዘኑና በጸሎታቸው እንደሚያስብዋቸው ገለጠዋል፣
በዚሁ ቀናት በኡክራይና እየተከናወነ ያለው አለመረጋጋት እጅግ እንዳሳሰባቸውና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝለት እንዲህ ሲሉ ተማጥነዋል፣
“ውድ ወንድሞችና እኅቶች! ውጥረቶችና ግጭቶች የማይቆምባት ኡክራይናን ለእመቤታችን ድንግል ማርያም እንድናማጥን እጠራለሁ፣ በዚሁ ዕለታት ሕይወታቸው ስላጡ ከእናንተ ጋር አብሬ እጸልያለሁ እንዲሁም ጌታ በሕዝቡ ልቦች የሰላምና የወንድማማችነት ስሜት እንዲያሳድር እጸልያለሁ” ሲሉ ተማጥነዋል፣
አያይዘውም በአፍጋኒስታን በመሬት መንሸርተት በናዳ የተቀበሩትን በማስታወስም እንዲህ ብለዋል፣
“ከሁለት ቀናት በፊት በታላቅ የመሬት ናዳ ተቀብረው ስለሞቱት እንጸልይ፣ የእያንዳንዳቸውን ስም የሚያውቀው ሁሉ ቻይ አምላክ ነፍሶቻቸውን በላሙ ይቀብላቸው፣ በሕይወት ለተረፉትም ከሁኔታው ወጥተው እንዲችሉና ስቃዮቻቸውን እንዲችሉ ዘንድ ኃይል እንዲሰጣቸው እንጸልይ” ሲሉ አሳስበዋል፣
በትናንትና እሁድ የተነበበው ወንጌል ከሉቃስ የተወሰደ ሆኖ ከክርስቶስ ሞት በኋላ ከሐዋርያቱ ሁለት አዝነውና ተስፋ ቈርጠው ወደ መንደራቸው ወደ ኤማሁስ ሲጓዙ ኢየሱስ አብሮዋቸው የተጓዘበትና ስለሁኔታው ጠይቆዋቸው ባዘነ ልብ ሲመልሱለት እርሱም ቅዱሳት ጽሑፎችን ከነቢያትና ከአበው ጀምሮ ስለእርሱ የሚናገረውን እንዳተስማረቸውና እንጌራን ባርኮ በቈረሰ ጊዜ እንዳወቁትና ወዲያውኑ እንደተሰወረባቸው የሚተርክ ክፍል ነበር፣ ቅዱስነታቸው የሁለቱ ሐዋርያት ሁኔታን በመዘከር እንዲህ ብለዋል፣
“ከጌታ ጋር ለመገናኘት ዋነኛ ነገሮች ቅዱሳት ጽሑፎችና ምስጢረ ጥቀ ቅዱስ ቍርባን ናቸው፣ እኛ ሁላችን በእሁድ ቅዳሴ ለማስቀደስ በምንሄድበት ጊዜ የተለያዩ ሃሳቦችና ጭንቀቶች ይዘን እንደርሳለን፣ አንዳንዴ ሕይወት እጅግ ታቈስለናለች እኛም እንደሁለቱ ሐዋርያት ወደ ኤማሁሳችን እንሸሻለን፣ ከእግዚአብሔር እንርቃለን፣ ሆኖም ግን ቃለ እግዚአብሔርና ሥርዓተ አምልኮ ወደ ጌታ እንድንመለስ ያሳስቡናል፣ ኢየሱስም ልክ ከሓዋርያት ጋር እንዳደረገው ቅዱሳት ጽሑፎችን ይገልጥልናል፤ ልቦቻችንን በእምነትና በተስፋ ሙቀት ያቀጣጥልናል በቅዱስ ቍርባንም ኃይል ይሰጠናል፣ ኢየሱስን በቅዱስ ቍርባን ለመቀበል መጀመርያ ቃልን ልብ ብሎ መስማትና ማስተንተን ያስፈልጋል፣
“ይህንን ልብ ብላችሁ እንድታስታውሱት ይሁን! በየዕለቱ አንድ የወንጌል ክፍል ማንበብ እንዲሁም በእሁድ ኢየሱስ በቅዱስ ቍርባን እንድትቀበሉ ይሁን፣ በኤማሁስ መንገድ ይጓዙ የነበሩ ሐዋርያት እንደዛ ነው ያደረጉት መጀመርያ ቃሉን ተቀበሉ ከዛም ጌታ ባርኮና ቈርሶ የሰጣቸውን ቍርባን ከተቀበሉ በኋላ ሃዘን ሸፍኖዋቸው እንደተሸነፉ ሆኖ ይሰማቸው የነበሩ በደስታ ተሞሉ፣ ውዶቼ ዘወትር የእግዚአብሔር ቃልና ቅዱስ ቍርባን በደስታ እንድንሞላ ያደርጉናል፣ ይህንን እንድታስታውሱት ይሁን ያዘንክ እንደሆነ ወይንም የተከፋህ ሆኖ የተሰማህ እንደሆነ ቃለ እግዚአብሔርን አንብብ፣ ብስጭትና ጭንቀት የተሰማህ እንደሆነ ቅዱስ መጽሓፍን ይዘህ ወደ ቅዳሴ ሂድና ቍረብ በዚህም በኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢር ትሳተፋለሁ፣ አስታውሱ ቃለ እግዚአብሔርና ቅዱስ ቍርባን በደስታ ይሞሉናል፣ ሲሉ ካስተማሩ በኋላ ጸሎተ ንግሥተ ሰማያት አሳርገዋል፣
ከጸሎት በኋላ በትናንትናው ዕለት የተዘከረውን የጥቀ ቅዱስ ልብ ካቶሊካዊ መካነ ጥበብ 90ኛ ዓመትን አመልክተው ለዚሁ በዓል የተመረጠው መሪ አሳብም የመጻኢ ተረካቢዎች ከሆኑ ከወጣቶች ጋር የሚል መሆኑን አመልክተው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለነበሩት ወጣቶች እንዲህ ሲሉ ተማጥነዋል፣
“እናንተ መጻኢአችን ናችሁ፣ ይህ መካነ ጥበብ ሲመሠረት ለተሰጠው ተልእኮ ታማኝ በመሆን ከዘመናዊ ትውልድ ጋር የሚራመድ እንዲሆን ስለዚሁ ታላቅ ዪኒቨርሲቲ እጸልያለሁ፣ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ይህ ዛሬ 50ኛ ዓመቱን የሚያከብረው የጀመሊ ፖሊክሊኒክ የመድኃኒትና የቀዶ ጥገና ክፍል የያዘው በሮም የሚገኘውን የጥቀ ቅዱስ ልብ ካቶሊካዊ ዪኒቨርሲቲ እጉበኛለሁ” ሲሉ መካነ ጥበቡን ለመጐበኘት ያላቸውን ምኞት ገልጠው በአደባባዩ ለነበሩት አመስግነው ሓዋርያዊ ቡራኬ በመቸርና መልካም ምሳ በመመኘት ሸኙ፣ይህ በእንዲህ ሳለ ዘወትር እንደሚያደርጉት ቅዳሜና ዛሬ ሁለት አጫጭር መል እክቶች ትዊተር በተሰኘው የዘመናችን መገናኛ ብዙኃን ጽፈዋል፣ ቅዳሜ ዕለት የጻፉት ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሓሳብ የተወሰደ ሆኖ “ፍራቻ አይኑራችሁ! በሮቻችሁን ለክርስቶስ በርግዳችሁ ክፈትዋቸው” የሚል ሲሆን ዛሬ ጥዋት የጻፉት ደግሞ “ስብከተ ወንጌል ማለት ምን ማለት ነው? በደስታና በየዋነት የሆነውንና የምናምነውን መመስከር ነው፣” የሚል ነበር፣









All the contents on this site are copyrighted ©.