2014-05-05 13:49:51

ወርኀ ግንቦት የማርያም ወር፤


የመላው ዓለም ካቶሊካውያንና ኦርቶዶክሳውያን እንዲሁም የእመቤታችን ድንግል ማርያም አፍቃሪዎች የግንቦት ወርን ለእመ አምላክ እንደ ጕልት ጐልተው ልክ እንደ ዘመነ ፍልሰታው ምህለላ ሰአሊ ለነ ማርያም ኀበ ፍቁር ወልድኪ ኄር ወመድኀኔ ዐለም እያሉ አልያም ጸሎተ መቍጠርያን ብዙ ግዜ በመድገም በአንዳንድ አከባቢዎች ደግሞ በየዕለቱ ለእመቤታችን ክብር አንዳንድ መንፈሳዊ የመልካም ሥራ ውሳኔዎች በማድረግና በየዕለቱ ተአምረ ማርያምን በመድገም ጥልቅ ፍቅራቸውን እና ትስስራቸውን ይገልጣሉ፣
ይህንን በተመለከተ በሮም ውስጥ የሚገኘው የእመቤታችን ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ሊቀ ካህናት ብፁዕ ካርዲናል ሳንቶስ አብሪል ኢ ካስተሎ ለቫቲካን ረድዮ የሰጡት ቃል እንዲህ ነበር፣
በትናንትናው ዕለት የቫቲካን ረድዮ ባልደረባ የሆኑ አቶ ሰርጅዮ ቸንቶፋንቲ ብፁዕነታቸውን ስለ ጸሎተ መቍጠርያ ጥቅምና ይዘት እንዲነግርዋቸው ጠይቀዋቸው ሲመልሱ፤ “እንደሚታወቀው ጸሎተ መቍጠርያ የምናስተንትናቸው ምሥጢራት በአርእስተ ሊቃነ ጳጳሳት ትምህርት ታላቅ ግምት የተሰጣቸው ሲሆን አራቱም የጸሎተ መቍጠርያ ምሥጢራት የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሕይወት ባጭሩ ያቀርባሉ፣ ስለዚህም እመቤታችን ድንግል ማርያምን በምናደርገው የክርስትና ጉዞ እንደምሳሌያችንና በሕይወት ጉዞ አችን እንደምትሸኘን በማወቅ ጌታን ለመከተል በምናደርገው ትግል ዋነኛ ምሳሌአችን ናት” ሲሉ መልሰዋል፣ ቀጥሎ የቀረባቸው ጥያቄም ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራቸስኮስ እመቤታችን ድንግል ማርያምን በሕይወታቸውና በትምህርታቸው እንዴት እንደሚያቀርብዋት ነበር፣
ብፁዕነታቸው ይህንን ጥያቄ ሲመልሱ “ቅዱስነታቸው የእመቤታችን ታላቅና ጥልቅ መንፈሳውነት እንዳላቸው እናውቃለን፣ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ታላቅ ባዚሊካ ሊቀ ካህናት እንደመሆኔ መጠን ያየሁትን ልመስክር፤ በጋዜጦችም እንደተገለጠው ር.ሊ.ጳ ሆነው በተመረጡበት ጊዜ ወዲያውኑ ማታ ራቴን እየበላሁ “የእመቤታችን ድንግል ማርያም ባዚሊካን ለመሳለም እና አጠቃላዩን ዘመነ ሥልጣኔን በእርሷ ጥበቃ ሥር ለማኖር ነገ ጥዋት ወደ ባዚሊካ እሄዳለሁ” አሉኝ፣ የመንበረ ጴጥሮስ ሥልጣን ከተቀበሉ ወዲህ ለሰባት ጊዜ በባዚሊካው በመገኘት ተሳልመው ጸሎት አሳርገዋል፣ ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ በታላቅ ደስታ እንደሚያደርጉት ምክንያቱም ይህንን ሲያደርጉ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም መመሪያ እና መጽናናት እንደሚያገኙ ይገልጣሉ፣” ሲሉ መልሰዋል፣
ጋዜጠኛችን ያቀረበላቸው ሌላ ጥያቄ ደግሞ ጸሎተ መቍጠርያ በቤተ ሰብ የሚመለከት ጉዳይ ነበር፣ ይህም ነፍሰ ኄር ቅዱስ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዳሉት ቤተ ሰብን አጣምሮ ስለሚይዝ መሆኑን አመልክተው ሲጠይቅዋቸው እንዲህ ሲሉ መልሰዋል፤ “ይህ ቅዱስ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ያቀረቡት ሓሳብ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው ሌሎች አር እስተ ሊቃነ ጳጳሳትም ደጋግመው አስምረውበታል፣ ይህም እውነት ነው ምክንያቱም በአንድ ቤተሰብ ወላጆችና ልጆቻቸው በጸሎተ መቍጠርያ አንድ የሆኑ እንደሆነና ለፍላጎታቸውና ለሌሎች ሰዎች የጸለዩ እንደሆኑ የሁሉ አንድነት በተለይ ደግሞ በወላጆችንና ልጆች መካከል ያለውን እውነተኛ አንድነት ስለሚያሳድግና በዚህም ያ “የቤት ቤተ ክርስትያን” የምትሰኝ ቤተሰብ ስለሚያዳብር ነው ሲሉ ቃለ መጠይቁን ደምድመዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.