2014-03-01 19:48:51

ዐቢይ ፆም - ዘቅድሰት


1ተሰ 4፡1-12፤ 1ጴጥ 1፡13-25፤ ሐዋ 10፡19-31፤ ማቴ 6፡16-23
“በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ” (ማቴ 6፡16) RealAudioMP3 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዝነትን በተደጋጋሚ በማንሳት ለመንፈሳዊው ህይወታችን ረብ እንደሌለው፣ በተለይም በማቴዎስ ወንጌል ምዕ. 6 ላይ ግብዝነት በዕለታዊው የክርስትና ጉዞ ውስጥ እና ከምናከናውናቸው መንፈሳዊ ተግባራት ጋር የሚጻረር ከመሆኑመ በላይ በተለይ ሦስቱን መሰረታዊ የሆኑትን ነገሮች ዋጋ እንደሚያሳጣቸው አስተመሮናል፡፡
1ኛ ከባልንጀሮቻችን ጋር የሚያገናኘንን ነገር በተመለከተ ሲሆን፡ በዋነኛነትም የፍቅር አገልግሎት ወይም ምጽዋት በምንሰጥበት ጊዜ በግብዝነት (ለታይታ) እንዳይሆን፤ ለድሃ ስንመጸውት ቀን ቀጥረን፣ አዋጅ አስነግረን በአደባባይ ተላላፊ በሚበዛበት አይሁን (ማቴ 6፡2-4)፡፡
2ኛ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ ደግሞ (በተለይ በጸሎት ከእርሱ ጋር መነጋገር ስንሻ) እንደ አሕዛብ በአደባባይ ሰው እንዲያይልን እና እንዲሰማልን እንዳይሆን፡፡
3ኛ በዛሬው ወንጌል እንደተጠቀሰው ከራሳችን ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ እየፆምን ወይም ራሳችንን እየተቆጣጠርን ወይም ስርዓትን እየተከተልን፣መንፈሳዊነትንም እየተለማመድን መሆናችንን ሰዎች እንዲያዩልን አለማድረግ፡፡
እነዚህን ሦስት ነጥቦች ጌታችን “በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ” በሚለው ዐረፍተ ነገር አስሮታል፣
በቀላሉ “ይህ ዓይነት ፆም፣የታይታ መንፈሳዊነት፣በግብዛዊነት የተሞላ መመላለስ አይማርከኝም፣ ፊቴንም ወደናንተ እንድመልስ፣ጆሮዬንም ወደ ጸሎታችሁ እንዳዘነብል አያደርገኝም” ማለቱ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ትክክለኛና በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያለው ፆም የትኛው እንደሆነ ነቢዩ ኢሳይያስ ግልጽ አድርጎ ያስቀምጥልናል፡፡ (ኢሳ 58፡1-ፍጻ)፡፡
ፆም ምንም እንኳ በክርስትና ሕይወት ዋነኛ ከሚባሉት ተግባራት የሚጻፍ ቢሆንም ስለዚሁ የእግዚአብሔር ጸጋና በረከት መገኛ ስለሆነው ነገር ያለን ግንዛቤ ጠለቅ ያለ አይደለም፡፡ በዓለማችን ላይ፣በቤተክርሰቲያንም ጭምር እጅግ ጠንካራ የሆኑ ተግዳሮት የታዩበትና እየታዩም ያሉበት ጊዜ ነበር አለም፤በዚያ ወቅት የሃይማኖት መሪዎች ፆምንና ጸሎትን ያውጃሉ፤ ጦርነት እንዲቆም፣ሰላም እንዲመጣ፣ድርቅ እንዲወገድ፣የእግዚአብሔር በረከት መገለጫ ከሆኑት አንዱ የሆነው ዝናብ እነዲዘንብ፣በሽታ እንዲጠፋ…እንዲሁም ደግሞ ስለወዳጅ፣ስለተቸገረ ሰው ይፆማል ይጸለያል፡፡
ጌ.ኢ.ክ. በኖረበት ዘመንና ባህልም ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የፆም ነገር ሲነገርም ሲተገበርም እንደነበር በሕግ መጽሐፍት ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ የስርየት ቀንም ነውና ይህ የፆም እና የመንጻት ሥርዓት በዓመት አንድ ጊዜ እንደሚደረግ መጽሐፍቱ ያስረዳሉ፡፡ (ዘሌ 16፡29-31፤ 23፡27-31)፡፡
በተቀደሰችው የወንጌል ዘመን የምንኖር ደግሞ እንደጥንታውያኑ በዚህ ወቅት በተለየ መልኩ ወደ መንፈሳዊው ሕይወት በማድላት ውስጣችንን እንድንመረምርና የበለጠ ወደ አምላካችን እንድንቀርብ ነው ቃለ እግዚአብሔር የሚያስተምረን፡፡ ለዚህም እንዲያመቸው ሰው በዚህ ቅዱስ ጊዜ ሥጋውን ቆንጠጥ ልጓሙንም ሳብ ጠበቅ ማድረግ ይጠበቅበታል ፡ ምክንያቱም የፆማችን ዋና ዓላማ ነቢዩ ኢዩኤል እንዳለው ቅዱስ ፆምን በማወጅ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነውና (ኢዩ 2፡12፣15)፡፡ በተጨማሪም ፆማችን የልማድ ፆም እንዳይሆን የእግዚአብሔር ቃል ያስጠነቅቀናል፡፡ ስለዚህ ፆም ማለጽ እንደው ፊት አጠውልጎ ማቅረብ እና መቅረብ ሳይሆን በውስጣዊ ደስታ የታጀበ እንዲሆን ያስፈልጋል፤ ይህ ተግባር ደግሞ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ተግባር ነው…እንደው መስሎ-ተመሳስሎ መቅረብ የለም፡፡ እያንዳንዱ አማኝ ለስጋው ተገዢ ላለመሆን ራሱንም ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርግ መሆን ይገባዋል፡፡ ቅ. ጳውሎስ እንዲህ ነው የሚለው “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር ሰውነቴን እየጎሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” (1ቆሮ 9፡26-27)፡፡ ይህ ማለት ደግም ራስን፣አንደበትን፣ምላስን መቆጣጠር ማለት ነው፡፡ ወንጌሉ “ፊትህን ታጠብ ቅባትም ተቀባ ይላል”፡፡ ይህ ደግሞ በኛ ግምት ፆምን ሳይሆን ወደ አንድ ድግስ ወይም ግብዣ ለመሄድ የሚደረግ ዝግጅት ይመስለን ይሆናል፡፡ ነገር ግን መልዕክቱ ግልጽ ነው፣፤ የታጠበ፣የተቀባ፣ፈገግታ የማይለየው እንዳቅሙም የለበሰ ሰው ድሃ ይሁን ሀብታም ወይም ምን ውስጥ እንደሚኖር እንደማይታወቅበት ሁሉ፣ ፊቱን ሳያጠቁር የሚፆምም እንዲሁ ነው፣የውስጡን አምላኩ እና ሕሊናው ብቻ ናቸውና የሚያውቁት፡፡ የወንጌሉም የመደምደሚያ ምክር “የተደበቀ ንጽህናን እና ጽድቅን ገንዘባችሁ አድርጉት” የሚል ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት አኳኋን የተፆመ ፆም እግዚአብሔርን ጆሮውን ወደ ጸሎታችን እንዲያዘነብል ያደርገዋል፡፡
ሠላም ወሰናይ!

አባ ዳዊት ወርቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን








All the contents on this site are copyrighted ©.