2013-10-13 14:17:05

የዘመነ ጽጌ ሁለተኛ ሰንበት


ሉቃስ 12፡16-32 «አንተ ሞኝ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊወስዱት ይፈልጓታል» (ሉቃስ 12፡20)፡፡
RealAudioMP3 እንደ አገራችን የሉጡርጊያ ዘመን አቆጣጠር መሰረት አሁን የምንገኝበት ወቅት «ዘመነ ጽጌ» በትርጓሜውም «የአበባ ዘመን» ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ በዚህ ሰንበት የምናነበው ወንጌል የተሰፈረልንን የዕድሜ ዘመናችንን እንዴት መኖር እንደሚገባን አንድ እርሻው ብዙ ምርት የሰጠውን ሀብታም ምሳሌ አድርጎ ያስተምረናል፡፡ ሀብታሙ ገበሬ ምድርን ባረኮ ብዙ ፍሬ እንድታፈራለት ያደረገውን፣ በዝናብ አብቅሎ በፀሓይ አብስሎ የሚመግበውን እግዚአብሔርን ከማመስገን እንደመጀመር በራሱ ጥበብ ብቻ ያገኘው ይመስል ሃሳቡን ሁሉ ትልልቅ ጎተራ መስራትና የግል ደስታውን ብቻ ማመቻቸት ላይ አድርጎት ነበር፡፡ የዚህ ሰው ምርጫ በእግዚአብሔር ፊት ሳይሆን በራሱ ጎተራ ውስጥ ሀብትን ማጠራቀም ነበር፡፡ የሀብቱ ብዛት ግን እድሜውን ሊያረዝማት ነፍሱንም ሊያድናት አልቻለም፤ አንዲት ቀን እንኳ ሳይበላው ምድራዊ ኑሮው አበቃ…ሞት ቀደመው፡፡ ይህ ሰው ሀብታም ሳይሆን የሀብታም ድሃ ሆነ፡፡ ወንጌሉ በመሠረታዊነት የሚያስተላልፍልን መልክት «ሰው ለኑሮው አያስብ» የሚል ሳይሆን «ከመስመር በወጣ ወይም ከመጠን ባለፈ ሁኔታ አይጨነቅ» የሚል ነው፡፡ ሰው ያቅሙን ካደረገ ፍጡሩን በምግቡ የማይረሳው አምላክ ያስብበታል፤ የሚያስፈልገው ማመን ብቻ ነው፡፡ ትንሿን ነገር እንኳን ማድረግ የማንችል ከሆነ ከባዱንና የማንችለውን ለማድረግ መጨነቅ እንደሌለብን የዛሬው ወንጌል ማዕከላዊ መልዕክት ነው፡፡
ሠላም ወሰናይ

አባ ዳዊት ወረቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን








All the contents on this site are copyrighted ©.