2013-10-09 17:32:52

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ውድ ወንድሞችና እኅቶች! መልካም ቀን እመኝላችኋለሁ ሆኖም ግን ዛሬ ብርዱና ዝናሙ ከበድ ብለዋል እናንተ ግን በብዛት እዚህ በመገኘታችሁ ብርታታችሁን አሳያችሁ! ምስጋና ይገባችኋል!
“አንዲት በሆነችው ቅድስትና ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን አምናለሁ”፣ ዛሬ ካቶሊካዊ ስለሚለው ቃል እናስተነትናለን፣ ቤተ ክርስትያን ካቶሊካዊት ናት ስለዚህ ስለ ካቶሊካውነት እንመለከታለን፣ በመጀመርያ ካቶሊካዊ ማለት ምን ማለት ነው? ብለን የጠየቅን እንደሆነ ቃሉ ካቶሎን ከሚለው ቃል የመነጨ ሲሆን ትርጓሜው ደግሞ ሁሉን የሚያቅፍ ፍጹም አጠቃላይ ማለት ነው፣ ይህ የሁሉን ማቀፍ ኵላውነት እንዴት ለቤተ ክርስትያን ይመለከታል? ቤተ ክርስትያን ካቶሊካዊት ናት ስንል ደግሞ ምን ማለታችን ነው? ለዚሁ ለመመለስ ሶስት መሠረታውያን ነገሮች ማቅረብ እወዳለሁ፣
1ኛ ቤት ክርስትያን ካቶሊካዊት ናት የምንልበት ምክንያት ለሁሉ የሚሆን ቦታ ስላላት በእምነት አማካንነት ሁሉ የሚጠቀለልበት ቤት ነው፣ ክርስቶስ ያመጣው ድኅነት ለሁሉም ይሰጣል፣ በመካከልዋ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላለም ሕይወታችን የሚለውጥ የእግዚአብሔር ምሕረት በቤተ ክርስትያን እናገኛለን፣ እውነተኛ የእምነት ምስክርነት በቅዱሳት ምሥጢራት የሚገኝ የሕይወት ሙላት እና የምሥጢረ ክህነት ስልጣን የሚሰጣት ክርስቶስ ከእርሷ ጋር ነውና፣ በቤተ ክርስትያን እያንዳንዳችን ለማመን እንደ ክርስትያን ለመኖር ቅዱስ ለመሆን እና በሁሉም ቦታና በሁሉም ዘመን ለመጓዝ የሚያስፈልገውን ያህል ያገኛል፣
አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ የቤተ ክርስትያን ሕይወት እንደቤተሰብ ሕይወት ነው፣ በቤተ ሰብ እያንዳንዳችን ለማደግ ወደ ብስለት ለመድረስ እና ለመኖር የሚያስችለን ሁሉ ይሰጠናል፣ ብቻህን ሆኖ ማደግ አይቻልም ብቻህን መጓዝ አይቻልም፤ ነገር ግን በቤተሰብ በኅብረት እንጓዛለን በማኅበረሰብም በኅብረት እናድጋለን፣ ቤተ ክርስትያንም እንደዚሁ ነው፣ በቤተ ክርስትያን ቃለ እግዚአብሔር እግዚአብሔር የሰጠን መልእክት መሆኑን በመተማመን እንሰማለን፤ በቤተ ክርስትያን ጌታን የእግዚአብሔር ብርሃን በሚያሳዩን ክፍት መስኰቶች በሆኑ ምሥጢራት ጌታን እናገኛለን፣ እነዚህ ምሥጢራት የእግዚአብሔር ሕይወት ምንጭ እናጣጥማለን፤ በቤተ ክርስትያን ከእግዚአብሔር በሚመጣው ፍቅር ተባብሮ መኖርን እንማራለን፣ ዛሬ እያንዳንዳችን በቤተ ክርስትያን እንዴት እኖራለሁ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፣ ወደ ቤተ ክርስትያን እሄዳለሁ ልክ ወደ ኳስ ሜዳ ጨወታ ለማየት እሄዳለሁ ዓይነት ከሆነስ? ወይንም ወደ ሲነማ ቤት እንደመሄድ ከሆነስ? እንደሲህ አይደለም ወደ ቤተ ክርስትያን መሄድ ሌላ ትርጉም አለው፣ እንዴት ሆኜ ወደ ቤተ ክርስትያን እሄዳለሁ? እንደ ክርስትያን እንዳድግ ወደ ብስለት ደረጃ እንድደርስ ቤተ ክርስትያን የምትሰጠኝን ጸጋዎች እንዴት እቀበላኋለሁ? ቤተ ክርስትያን በምሄድበት ጊዜ ከሌሎች ጋር ከማኅበረሰቡ እሳተፋለሁ ወይስ በችግሮቼ በገዛ ራሴ ተዘግቼ እቀራለሁ? ይህንን ነጥብ ለማጠቃለል ቤተ ክርስትያን ካቶሊካዊት ናት ምክንያቱም የሁሉም ቤት ናትና፤ ሁላቸው የቤተ ክርስትያን ልጆች ናቸው፤ ሁላቸውም በዚህ ቤት ይኖራሉ፣
2ኛው ትርጉም ደግሞ ዓለም አቀፋውነት ነው፤ ቤተ ክርስትያን ዓለም አቀፍ ስለሆነች ካቶሊካዊት ናት፣ በዓለማችን በሁሉም ክፍሎች ተዘርግታ ለእያንዳንዱ ሰውና የሴት ልጅ ወንዴልን ታበስራለች፣ ቤተ ክርስትያን የምሁራን ቡድን ስለሌሎች የማታስብ አይደለችም፣ በቤተ ክርስትያን የተዘጋ ነገር የለም፣ ለሁሉም ሰዎች ለመላው የሰው ዘር የተላከች ናት፣ አንዲትዋ ቤተ ክርስትያን በትናንሽ አካሎችዋም ትገኛለች፣ ማንኛው ክርስትያን በቍምስናየ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን አለች ምክንያቱም እርሷም የዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስትያን አባል ናት፤ የክርስቶስ ስጦታዎች የሆኑ እምነት ምሥጢራት እና አገልግሎት ሙላት አላት፣ ከጳጳስዋና ከር.ሊ.ጳጳሳት ጋር በመተባበርም አለምንም መለያየት ለሁሉም ክፍት ናት፣ ቤተ ክርስትያን በደወል ሓውልት ጥላ ሥር የምትገኝ ብቻ ሳትሆን ተመሳሳይ እምነት ለሚመስክሩ ከቅዱስ ቍርባን ለሚመገቡ እና በተመሳሳይ እረኞች ለሚገለገሉ ሁሉ እጆችዋን ዘርግታ ትቀበላለች፣ በመላው ዓለም ካሉ ትናንሽና ትላልቅ ካቶሊካውያን ማኅበሮች አካል ሆኖ መሰማት እንዴት ደስ ያሰኛል፣ እንዲሁም ሁላችን ትናንሽና ትላልቅ ማኅበረ ክርስትያኖች ለስብከተ ወንጌል የተላክን መሆናችን ማወቅ እንዲሁም ሁላችን ወንጌል ለመስበክ በሮቻችን እንዳለብን መረዳት እንዴት መልካም ነገር ነው፣ አሁን ወደገዛ ራሳችን በመመለስ፤ ጌታ በማግኘት እና የዚህች ቤተ ክርስትያን አባል መሆን የሚሰጠኝን ደስታ ለሌሎች ለማካፈል ምን አደርጋለሁ፧ ወንጌልን መስበክና እምነትን መመስከር የጥቂቶች ሥራ ብቻ አይደለም ሁላችንን እኔን አንተን ይመለከታል፣
3ኛና የመጨረሻ ትርጓሜ ደግሞ ቤተ ክርስትያን ካቶሊካዊት የምንበት ምክንያት የውህደት የአንደት ቤት በመሆንዋና አንድነት በብዙነት የሚረጋገጥበትና እንደሃብት የሚሆኑባት ስለሆነች ነው፣ የሙዚቃ ውህደትና ቅንብርን ያሰብን እንደሆነ በደንብ የተወሃሃደ ሙዚቃ በተለያዩ የሙዚቃ መሣርያዎች የቆመ ሲሆን እያንዳንዱ ቃና የብቻው የሆነ ጸባይ ሲኖረው የኅብረት በሆነ በአንድ ነገር ተስማምተው ጣዕመ ዜማ ይሰጣሉ፣ ለዚህም የሚመራ አንድ ዳይረክተር አለ፤ ይህ መሪ የሙዚቃ ቅንብሩ እንዲዋሃድና አንድ እንዲሆን ያደርጋል ነገር ግን ማንም ድምጽ አይደመሰስም እያንዳንዱ ድምጽ ከሌላው ልዩነትን ጠብቆ እጅግ ደስ በሚያሰኝና ክብር በሚሰጥ አገባብ እውን ይሆናል፣
ይህ ምስል ወይም ምሳሌ ቤተ ክርስትያንን እንደ ታላቅ ኦርከስትራና በውስጥ ብዙ ልዩነቶች እንዳሉ የሚገልጥ ጥሩ ምሳሌ ነው፣ ሁላችን እኩል አይደለንም እኩልም መሆን የለብንም፣ አንዱ ከሌላው እንለያያለን፤ እያንዳንዱ የገዛ ራሱ ይዘት አለው ይህም የቤተ ክርስትያን ቍንጅናን ያሳያል፣ እያንዳንዱ ሌሎችን እንዲያበለጽግ ያ እግዚአብሔር የሰጠውን የራሱን የሆነ ነገር ይዞ ይመጣል፣ ስለዚህ ቤተ ክርስትያንን ከሚያቋቁሙ ነገሮች ይህ ልዩነት አለ ሆኖም ግን ይህ ልዩነት ወደ ግጭት የሚያመራ አይደለም፣ ይህ ልዩነት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደ ውህደት ያመራል የዚሁ ውህደት እውነተኛ መምህሮም ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፣ የኦርከስትራ አስተማሪ ወይንም ዳይረክተር እንዳልነው ማለት ነው፣ እስቲ አሁንም ወደ ገዛ ራሳችን በመመለስ፤ በማኅበሮቻችን ይህንን ውህደት አብረን እንኖረዋለን ወይንስ እርስ በእርሳችን እንጣላለን? በቍምስናየ በመንፈሳዊ ማኅበሬ በቤተ ክርስትያን ቦታየ የት ነው? ወሬና ሓሜት አሉ ወይ? ወሬና ሓሜት ካሉ ውህደትና አንድነት የለም፤ ፉክክር ነው ያለው፣ ይህችም ቤተ ክርስትያን አይደለችም፣ ቤተ ክርስትያን የሁሉ ውህደትና አንድነት የሚገኝባት ናትና፣ ከአሁን ወዲህ አንዱ የሌላ አንጻር ወሬ እንዳይወራ ሓሜት እንዳይሰማ ጥላቻ ፈጽሞ ይወገድ፣ ሌላውን እንቀበላለንን? ፍትሓዊ የሆነ ልዩነት እንዲኖር እንፈቅዳለንን ማለትም ከእኛ ለየት ያለ ሰው እንዲኖር ለየት ያለ አስተሳስብ እንዲኖር እንቀበላለንን? አንድ በሆነ እምነት ልዩ ልዩ አሳቦች እንዲኖሩ እንፈቅዳለንን ወይንም ሁሉም አንድ መለዮ እንዲሆን እንፈልጋለን? እንደመለዮ ሁሉን በአንድ አስተሳሰብ በአንድ ነገር እንዲቆም ማድረግ ሕይወትን ይገድላል፣ የቤተ ክርስትያን ሕይወት በልዩነቶች የቆመ ነው፣ እላይ የተጠቀሰውን ሁሉን እንደመለዮ አንድ ማድረግ ከፈለግን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን እንገድላለን፣ ቤተ ክርስትያን ካቶሊካዊትና ዓለም አቀፋዊት ስለሆነች የዚሁ አንድነትና ልዩነት እንዲሁም የዚሁ ውህደት ፈጣሪ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ሁሌ ካቶሊካውያን እንድንሆን ያስችለን ዘንድ እንለምነው፣ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፣ የጥንታዊትዋ አለክሳንድርያ ሥር ዓተ አምልኮ የሚከተሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ጳጳሳትን በልዩ ስሜት ሰላምታየን አቀርባለሁ፣ በተለይ ደግሞ በላምፐዱሳ አሰቃቂ አደጋ ሕይወታቸው ላጡ የአገሮቻቸው ልጆች በሚያሳርጉት ጸሎትና በሚሰማቸው ሓዘን ቅርበቴን እገልጣለሁ፣







All the contents on this site are copyrighted ©.