2013-09-27 15:55:20

ዝክረ 50ኛው ዓመት፦ “Pacem in Terris-ሰላም በምድር”


RealAudioMP3 “Pacem in Terris-ሰላም በምድር” የተሰኘው የር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሐንስ 23ኛ የደረሱት ዓዋዲ መልእክት ዝክረ 50ኛው ዓመት ምክንያት በአገረ ቫቲካን እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 2 ቀን እስከ ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ዓውደ ጥናት ሊካሄድ መወሰኑ ትላትና በቅድስት መንበር የዜናና ኅትመት ሕንፃ በሚገኘው የጉባኤ አዳራሽ የፍትህና ሰላም ጉዳይ የሚከታተለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ፐተር ቱርክሶን ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለመረዳት ተችለዋል።
ብፁዕነታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዝክረ 50ኛው ዓመት ተራ ዝክር ሳይሆን ሰላም በምድር የተሰኘው ዓዋዲ መልእክት ወቅታዊነቱ የሚሰመርበት መሆኑ በመግለጥ የዚህ ዓውደ ጥናት ተጋባእያን ስልጣናዊ መሪ ቃል ለመቀበል እ.ኤ.አ. ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ጋር እንደሚገናኙ ገልጠው፣ ዝክረ 50ኛው ዓመት ሰላም በምድር ዓዋዲ መልእክት ምክንያት በማድረግ የሚካሄደው ዓወደ ጥናት፦ “ዓለም አቀፍ የተባበሩት መንግሥታት መዋቅር ኅዳሴ ያለው አንገብጋቢነት ይኽም ለመላ ዓለም የጋራ ጥቅም ለማረጋገጥ የዚሁ ዓለም አቀፍ ድርጅት አባል አገሮች ካለ ምንም ልዩነት ድምጻቸው የሚደመጥበት ድርጅት መሆን አለበት የሚል መሠረታዊ እቅድ ላይ ያነጣጠረ ኅዳሴ ይረጋገጥ ዘንድ ጥሪ የሚቅርብበት ነው” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለማችን የሚታየው የማኅበረ ክርስቲያን ስደት ይኽም በቅርቡ በኬንያና በፓኪስታን ከተጣለው ጸረ ክርስቲያን የሽበራ ጥቃት ጋር በማያያዝ ልክ የሌላው ሃይማኖት ማርከስ ወንጀል ተብሎ በአንዳንድ አገሮች በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ተመልክቶ እንደሚገኝ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማኅበረ ክርስቲያን እንዲሁም የንኡሳን የኅብረተሰብ ክፍል ሃይማኖት ተከታዮች የሕይወት ጸጥታና ደህንነት ለማረጋግጥ የሚያግዝ ሕግ መደንገጉ ያለው አስፈላጊነት ሲያመለክቱ፦ “ጸረ ማኅበረ ክርስቲያን የሚጠነሰሰው ጥቃትና የሚፈጸመው ቅትለት የመገናኛ ብዙኃን ትኩስ ዜና በማለት አንዴ ካቀረቡት በኋላ ስለ ጉዳይ መለስ ተብሎ በተለያየ መድረክ ውይይትና አስተያየት ሊሰጥበት እየተገባው፣ ወዲያውኑ ተረስቶ የሚቀር ጉዳይ ሆኖ ይታያል፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ በተአምኖተ እምነት ላይ እንደተመለከተው ‘አንዲት ቤተ ክርስቲያን’ የሚለው ሃረገ እምነት ጠቅሰው ይኸንን የምንናዘዘው ተአምኖተ እምነት ከሆን በየትም ሥፍራና አገር የሚኖር ማኅበረ ክርስቲያን ሲሰደድ የእኛ መሰደድ ሆኖ ሊሰማን ይገባል” ያሉትን ሥልጣናዊ ትምህርት ጠቅሰው፦ “የአንድ ክርስቲያን ስደት የሁሉም ክርስቲያን ስደት ነው” ብለዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የማኅበረ ክርስቲያን ወቅታዊው ሁኔታ ይኽም በሶሪያና የአረብ ዓገሮች የጸደይ አብዮት ተብሎ የተገለጠው ታሪካዊ ሁነት በታየባቸው አገሮች ጭምር፦ “የተቀጣጠለው የአረብ አገሮች ጸደይ አብዮት ጸረ አምባገነን መንግሥታት ብቻ ሳይሆን ሰፋ ባለ መልኩ ለየት ያለ አንድ የምስልና ሃይማኖት አመለካከትና ትርጓሜ ለማረጋግጥ ያቀደ መሆኑ ካለው አቅታዊው ሁኔታ ለመገንዘብ ይቻላል” ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ጋዜጠኞች ካቀረቡላቸው ጥያቄ በመንደርደርም፦ የኢራን አዲሱ ርእሰ ብሔር ሮሃኒ ስለ ኑክሊየር ሃይል ምንጭና እንዲሁም ከእስራኤል ጋር ግኑኝነት በሚሉት ሁለት አንገብጋቢ ጉዳዮች በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ገና ከወዲሁ የማይታመን ነው ብሎ አሉታዊ ቅድመ ፍርድ ከመስጠት ተቆጥቦ የሰጡት ሃሳብ በተግባር የሚሸኝ ሁነት ይፈጠር ዘንድ ጥረት ማድረግና ያሉት ሃሳብ ተግባር የሚከተል እንደሆነ ለማየት መጠበቁ በሳልነት ነው” ሲሉ ዋና ጸሐፊያቸው ብፁዕ አቡነ ማሪዮ ቶዞ በመቀጠልም፦ “በዚህ በኑክሊየር ኃይል ምንጭ ወቅት የኑክሊያር ጦር መሣሪያ በመጠቀም ቅንና ተገቢ ጦርነት ብሎ ለመናገር በእውነቱ ያዳግታል፣ ስለዚህ ችግሩ በጦር መሣሪያ መደለብ ወይንም ትጥቅ መፍታት ሳይሆን ሰላም በትክክልና በቅንነት በፍትህ እንዴት ለማረጋገጥ ይቻላል የሚለው ነው። በዚህ በአሁኑ ወቅት የኤኮኖሚ መቃወስ በስፋት እየታየበት ባለው ዓለም አንዳንድ አገሮች በዚሁ ጉዳይ ላይ በሚገባ ክማተኮር ይልቅ ባህይርያዊ ግብረ ገብ ሕግና ሥርዓት እየዘነጉ በሥነ ምግባርና በሥነ ሕይወት ሥነ ምግባር በተመለከተ ሕጎችና መመሪያዎች ሲደነግጉ ነው የሚታየው። ይኽ ደግሞ ሰላም በምድር የተሰኘው ዓዋዲ መልእክት የሕግ ሉአላዊነት ማለት የሰው ልጅ መብትና ግዴታ የሚያሟላ መሆን እንደሚገባው በማስገነዘብ ይገልጠዋል” ስለዚህ ይኸ የዓዋዲው መልእክት ያለው ወቅታዊነት የሚጤንበት ዓውደ ጥናት መሆኑ ባብራሩበት ሃሳብ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መጠናቀቁ የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ ፓውሎ ኦንዳርዛ አስታወቁ።








All the contents on this site are copyrighted ©.