2013-07-22 18:23:30

ጸሎትና አገልግሎት ለእምነት መሠረታውያን ናቸው፣


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍርናቸስኮስ ትናንትና እኩለ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በብዙ ከሚቆጠሩ ምእመናንና ነጋድያን የመል አከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት የዕለቱን ቃለ ወንጌል በመመርኰስ ጸሎትና መልካም ተግባር ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥ ለጓደኛ ተጨባጭ አገልግሎት መስጠት የሚደጋገፉ እንጂ የሚቃረኑ አይደለም ለእምነታችንም መሠረት ናቸው” ሲሉ እምነት በተግባር እንደሚገለጥና እምነትና ተግባር ሁለቱም አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጠዋል፣ በመጨረሻም ዛሬ ዕለት ለዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ለመሳተፍ ወደ ሪዮ ዲ ጃነሮ ለሚያደርጉት ጉዞ በጸሎት እንድንሸኛቸው ተማጥነዋል፣
በቅዱስነታቸው አስተምህሮ ዋናው ነጥብ የነበረው ጌታ ኢየሱስን ተቀብለው ያስተናገዱ ማርያና ማርታ ያሳዩዋቸው ሁለት ተግባሮች ናቸው፣ ማርታ በአገልግሎት ስትጠመድ ማርያም በጌታ እግር ተቀምጣ ታዳምጠው ነበር የሚለውን ነው፣ ማርታ ሥራ ስለበዛባት ለኢየሱስ ማርያን እንድትረዳት ያደርግ ዘንድ በማጉረምረም መልክ ጠየቀችው፤ ኢየሱስ ቀን ለስለስ ባለ አነጋገር አንድ ነገር ብቻ እንደሚያስፈልግና እርሱንም ማርያ እንደመረጠችው የሚነጥቃትም እንደሌለ ይገልጥላታል፣
“ከሁሉ አስቀድመን መረዳት ያለብን እነኚህ ሁለት ተግባሮች ተቃራኒ እንዳልሆኑ ነው፤ ማርያ እንዳደረገችው ጌታን ማዳመጥና በጌታ ቃል ማስተንተንና ማርታ ታደርገው የነበረ አገልግሎት ማለትም ተጨባጭ በሆነ መንገድ ለሰዎች የምናደርገው ምግባረ ሠናይ ማለትም የምናደርገው አገልግሎት የሚቃረኑ ሳይሆኑ የሚሟሉ ለክርስትያናዊ ሕይወታችን ደግሞ ሁለቱም መሠረታውያን ናቸው፣ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ነገር ግን ጥልቅ በሆነ አንድነትና ውህደት አብረው የሚጓዙና በሁለቱም ተመርተን መኖር ያለብን መሆናቸው መዘንጋት የለብንም ብለዋል፣
ቅዱስነታቸው አያይዘው ለመሆኑ ማርታ መልካም ሥራ ስትሠራ ለስለስ ባለመንገድም ይሁን ከጌታ ኢየሱስ ለምን ተገሳጽ አገኘች ብለው ጥያቄ አቅርበዋል፣
“ምክንያቱም ስትሰራው የነበረችውን ሥራ ብቻ መሠረታዊ ነው ብላ በማመንዋ ነው፣ በምታደርገው ሥራ ጠልቃ ስለእርሱ ብቻ በማሰብዋና በመጨነቅዋ ነው የገሰጻት፣ በአንድ ክርስትያን ሕይወት ውስጥ የአገልግሎትና ምግባረ ሠናይ ሥራዎች ከዋናው ምንጫቸው የሆነ ቃለ እግዚአብሔር የማዳመጥና ማርያ በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ ታደርገው እንደነበረ ስለ እርሱ ማስተንተንንም መዘንጋት የለብንም፣
“የተከበራችሁ ወንድሞችና እኅቶች በክርስትያናዊ ሕይወታችንም ሳይቀር ጸሎትና ምግባረ ሠናይ ጠለቅ ባለ መንገድ የተዋሃሃዱ መሆን አለባቸው፣ ለድኃ ለታመመ እርዳታ ለሚያስፈልገው እና በችግር ለሚገኝ ወንድማችን የመርዳት ተጨባጭ እርምጃ የሌለበት ጸሎት መካንና ጐደሎ ጸሎት ነው፣ ሆኖም ግን በቤተ ክርስትያን አገልግሎት ለምግባረ ሠናይ ብቻ ብዙ ትኵረትና ጌዚ በመስጠት የኢየሱስ ማእከልነትን የዘነጋን እንደሆነና ከእርሱ ጋር ለመገናኘትና ለመወያየት በቂ ጊዜ የማንሰጥ ከሆነ በምንረዳው የተቸገረ ወንድማችን ገዛ ራሳችንን እንጂ እግዚአብሔርን እንዳላገልገልን ማወቅ ያስፈልጋል፣ ስለዚህም ነው ቅዱሱ አቡነ ቡሩክ ኦራ ኤት ላቦራ ጸሎትና ሥራ በማለት ለመነኮሳን ወርቃማ ሕግ የተወላቸው፣
“ከጌታ ጋር ባለን የጓደኝነት ግኑኝነት ከሚደረገው ኃይለኛ አስተንትኖ የእግዚአብሔር ፍቅር ምሕርትንና አሳቢነትን ወደ ሌሎች ለማዳረስ የሚገፋፋን ችሎታ ይወለዳል፣ ከዚህም ጋር ለተቸገረ ወንድማችን የምንሰጠው አገልግሎት፣ በምሕረት ሥራዎች የምናበረክተው ምግባረ ሠናይ ወደ እግዚአብሔር ያደርሱናል ምክንያቱም በተቸገረው ወንድማችንና እኅታችን ጌታን እናያለን፣ በማለት የሁለቱም ግኑኝነት ከገለጡ በኋላ ለመል አከ እግዚአብሔር ጸሎት እንዲህ ሲሉ ተማጥነዋል፣ “የማዳመጥና የአግለልግሎት እናት የሆነቸው እመቤታችን ድንግል ማርያም የወንድሞቻችን ችግሮችን አስተውለን ለመቻልና በተግባር እንድረዳቸው ዘንድ የልጅዋ ቃላትን በልባችን እንድናኖርና እንድናስተንትነው እንዲሁም በታማኝነት ለመጸለይ ትርዳን” ካሉ በኋላ ጸሎተ መል አከ እግዚአብሔር አሳርገዋል፣
ከጸሎቱ በኋላ በአደባባዩ በታላቅ ቃላት የተጻፈ ሰፊ ጨርቅ ላይ መልካም ጉዞ የሚለውን እየተመለከቱ ወደ ርዮ ዲ ጃነሮ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉዞ በጸሎት እንዲሸኝዋቸው እንዲህ ሲሉ ተማጥነዋል፣
“በሪዩ ዲ ጃነሮ ከመላው ዓለም የተሰበሰቡ ብዙ ወጣቶች አሉ፣ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ሳይሆን የወጣቶች ሳምንት ይመስለኛል፣ አዎ የወጣቶች ሳምንት! የሳምንቱ ዋና ወጣቶቹ ናቸውና! ወደ ርዩ የሚመጡ ወጣቶች ሁሉ የኢየሱስ ድምጽን መስማት ይፈልጋሉ! ኢየሱስን ማዳመጥ! ጌታ በሕይወቴ ምን ማድረግ አለብኝ! መንገዴ የትኛው ይሆን! ብለው ሊጠይቁት ነው፣ ዛሬ በዚህ አደባባይ ወጣቶች ያሉ እንደሆነ አላውቅም! ወጣቶች አላችሁ ወይ! አዎ አያለሁ! ስለዚህ እናንተም እዚህ የምትገኙ ወጣቶች ለጌታ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቡለት! ጌታ ኢየሱስ በሕይወቴ ምን ማድረግ አለብኝ? ለኔ የሚሆን መንገድ የትኛው ነው? ብላችሁ ጠይቁት፣ እነኚህን እናንተና እዚያ ብራዚል ያሉ ወጣቶች የሚያቀርብዋቸው ጥያቄዎችን በብራዚል ብዙ ለምትፈቀርና ለምትከበር እመቤታችን ድንግል ማርያም እናማጥናቸው፣ በዚሁ አዲስ የመንፈሳዊ ንግደት ጉዞ እመቤታችን ድንግል ማርያም ትርዳን፣ ለሁላችሁም መልካም እሁድ እመኝላችኋለሁ፣ መልካም ምሳ በሰላም ያገኛኘን ሲሉ ተሰናብተዋል፣
ቅዱስነታቸው የመል አከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ አቅርበው የመል አከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳርገው ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ዘወትር እንደሚያደርጉት በዘመናችን የመገኛኛ ብዙኃን ትዊተር በተለያዩ ምክንያቶች በዓለም አቀፉ የወጣቶች ቀን ሊሳተፉ የማይችሉ ወጣቶች በጸሎት በመካከላችን እንዳሉ ይሰማቸው ሲሉ ጽፈዋል፣ ይዘቱም እንደሚከተለው ነው፣ “በዓለም አቀፉ የወጣቶች ቀን ወደ ሪዩ ዲ ጃነሮ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለመሳተፍ ላልቻሉ ወጣቶች በጸሎት መንፈስ በመካከላችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ኅብረታችንን እንገልጻለን ይላል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቅዳሜ ዕለት በጻፉት አጭር መል እክት “የተወደዳችሁ ወጣቶች ከእናንተ በብዛት ወደ ርዮ እየተጓዛችሁ መሆኑን አውቃለሁ፣ በምታደርጉት ጉዞ ሁሉ እግዚአብሔር ይሸኛችሁ” ብለው ጽፈው ነበር፣ ይህ የዘመናችን መገናኛ ብዙኃን ከ7.5 ሚልዮን ተከታዮች እንዳለው ከዜናው ጋር ተያይዞ የወጣ መግለጫ አክሎ ገልጠዋል፣







All the contents on this site are copyrighted ©.