2013-05-27 17:55:14

የማፍያ ቡድን አባላት ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ! ሕጻናትና ሴት ልጆች በባርነት ይዘው ሊኖሩ አይችሉም፣


ይህንን ያሉት ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካሳረጉ በኋላ ሥርዓተ ብፅዕናቸው ከትናንትና ወዲያ በፓለርሞ የታወጀው አባ ፒኖ ፑኙሊሲን አስታውሰው በተነጋገሩበት ወቅት ነበር፣ ብፁዕ አባ ፑኙሊሲ በመስከረም 15 ቀን 1993 በፓለርሞ በማፍያ እጅ የተገደሉ ናቸው፣
በማፍያ የሚታወቀው የወንጀለኞች ቡድን በጣልያን አገር በተልይ ደግሞ በደቡባዊ ክፍል ድኃውን የሕብረተሰብ ክፍል እንደመሳርያ በመጠቀም እንዲሁም ሃብታሞችን ገንዘብ እንዲከፍሉ በማድረግ ብዙ ሃብት ያካበተና በዓመጽ የሚኖር ነው፤ ብፁዕ አባ ፑሊሲ ከድሆች ጋር በማወገንና የእሳቸው ጠበቃ በመሆን ስለተቃወሟቸው ነው የገደልዋቸው፣
ያኔ ስመ ጥር ር.ሊ.ጳ ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በቦታው ተገኝተው ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ ንስሓ ግቡ! አንድ ቀን በእውነተኛው ዳኛ የሆነ እግዚአብሔር ፊት ትቆማላችሁና፤ ብለው ነበር፣
ቅዱስነታቸውም ያኛውን ኃይለ ቃል እንደመድገም ዓይነት ነው ትናንትና ማፍያና ተባባሪዎቻቸው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የጠሩት፣
“በብዙ ሰዎች ሴቶች ሕጻናትም ሳይቀር ላይ የሚወርደውን ስቃይ ያሳስበኛል፤ በተለይ ደግሞ በማፍያ የተጠቁ ወገኖች እንደ ባርያ ይዘዋቸው የሚጨቁንዋቸውና በተለያዩ የብዝበዛ ሥራዎች እስከ ሴት አዳሪነት የሚያስገድድዋቸውን አስባለሁ፣ እግዚአብሔር ይህንን በደል የሚፈጽሙ ሰዎች ልብ እንዲነካና እንዲለውጣቸው እንጸልይ፣ እነርሱ ይህንን ማእረግ አይችሉምና፣ እስከ መቼ ነው ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው ለሆን ባርያዎቻቸው የሚያደርጉን፣ ጌታን መለመን አለብን! እነኚህ የማፍያ አባላት የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ እንጸልይ፣ ሲሉ ከጠማጠኑ በኋላ ስለ ብፁዕ አባ ፑሊሲ እንዲህ ብለዋል፣
“አባ ፑሊሲ አብነታዊ ካህን በመሆን በተለይ በወጣቶች ሐዋርያዊ እረኛነት ብዙ ያበረከቱ ነበር፣ ወጣቶችን በወንጌል እያስተማረ ከክፉ የማፍያ ኑሮ ያወጣቸው ነበር፤ ማፍያዎቹ ደግሞ ይህንን መልካም ሥራ ለማደናቀፍ ገደሉት፣ እንደእውነቱ ከሆነ ግን አባ ፑሊሲ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳው ክርስቶስ ጋር በመሆን አሸንፈዋል፣
ቅዱስነታቸው ከመል አከ እግዚአብሔር ጸሎት በፊት በዕለቱ እንደ ላቲኑ ሥር ዓተ አምልኮ ተዘክሮ የዋለውን የቅድስት ሥላሴ በዓል በማስታወስ ሥላሴዎች በተጨባጭ በመካከላችን የሚሮሩና ለተቀበላቸው ሰው በልቡ ማደሪያ እንደሚሰሩ እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፣
“የእኛ እግዚአብሔር የተበታተነ ሓሳብ አይደለም ተጨባጭ ነው ስምም አለው እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ ይህ ፍቅር ስሜታዊና ግዝያዊ ፍቅር አይደለም ነገር ግን የሕይወት ሁሉ ምንጭ የሆነ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተና ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ክርስቶስ ፍቅር የሰው ልጅንና ዓለምን የሚያሳድስ የመንፈስ ቅዱስ ፍቅር ነው፣ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን ማስተንተን ለእኛ መልካም ነው ምክንያቱም ልክ ኢየሱስ ስለእኛ እንደተሰዋውና በፍቅር ከእኛ ጋር እንደሚጓዘው ዓይነት ሌሎችን ለማፍቀር ያስችለናልና፣
“ቅድስት ሥላሴ የሰው ልጅ ሓሳብ ውጤት አይደለም፣ ገዛ ራሱን የገለጠን የእግዚአብሔር ገጽታ ነው፣ ይህም ባንድ ከፍ ያለ ማስተማርያ ቦታ ተቀምጦ ሳይሆን ከሰው ልጆች ጋር እየተጓዘ ያደረገልን ግልጸት ነው፣ እግዚአብሔር አብ በእስራኤላውያን ታሪክ ከሰው ልጆች ጋር ተጓዘ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ሁሌ ከእኛ ጋር ተጉዘዋል የማናውቀውን ሁሉን ነገር የሚያስተምረንና በውስጣችን ሆኖ የሚመራን መልካም ሐሳብ እና ግልጸት በልቦቻችን የሚያኖርልን መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክልን ተስፋ ሰጥቶናል፣
“የተስፋ እናት የሆነች ድንግል ማርያምም በጉዞ አችንና በጐዳናችን ትገኛለች፤ እርሷ የተስፋ እናት ናት፣ የምታጽናና እናትም ናት፣ የመጽናናት እናት ሆናም በጉዞ አችን ትሸኛናለች፣ አሁን ደግሞ በጉዞ አችን ሁሉ እንድትሸኘን ሁላችን አብረን እንለምናት፣ ካሉ በኋላ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከምእመናኑ ጋር አብረው አሳርገዋል፣
ይህ በእንዲህ ሳለ ባሁኑ ወቅት ልማዳዊ እየሆነ ያለው በዘመናችን መገናኛ ብዙኃ በትዊተር ደግሞ “ሁሌ የግል ጥቅማችን በማስቀደም ለእግዚአብሔር እምቢ በምንልበት ጊዜ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያለውን የፍቅር ታሪክ እናደፍርሳለን” ሲሉ ከሶስት ሚልዮን በላይ ለሚሆኑ አትፖንቲፈክስ የሚለው ፖስታቸው ደንበኞች አጭር መልእክት አስተላልፈዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.