2013-05-24 15:00:27

የኢየሱስ ጨው የሌለን እንደሆነ ጣዕመቢስ እንሆናለን! የቤተ መዘክር ክርስትያን ሆነን እንቀራለን፣


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና በቅድስት ማርታ የእንግዳ መቀበያ በሚገኘው ቤተ ጸሎት ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ ላይ በስብከታቸው “ክርስትያኖች የእምነት የተስፋና የፍቅር ጨውን ወደ ሁሉ ማዳረስ አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል፣ ከቅዱስነታቸው ጋር አብረው የቀደሱ ብፁ ዓን ካርዲናሎች አንጀሎ ሶዳኖ ለዮናርዶ ሳንድሪና የፓዝ ሊቀ ጳጳስ ኤድሙንዶ አባስቶፍሎር ሞንተሮ ሲሆኑ የምሥራቅ አብያተ ክርስትያን ማኅበር ሠራተኞች ካህናትና ምእመናንም ተሳትፈዋል፣
ቅዱስነታቸው በስብከታቸው በክርስትያን ሕይወት ጨው ምንድር ነው? ኢየሱስ የሰጠን ጨው የትኛው ነው? ብለው በጥያቄና አስተንትኖ ጀምረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠን ጨው የእምነት የተስፋና የፍቅር ጨው ነው፣ ሆኖም ግን ይህ ጌታ ኢየሱስ ለድኅነታችን እንደሞተና ከሙታን እንደተነሣ እርግጠኝነት የሚሰጠን ጨው ጣዕሙን እንዳያጠፋ ኃይሉን እንዳያጠፋ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፣ ይህ ጨው እንደ በጨው መያዣ የተቀመጠ ጨው አምቀን ያስቀምጥነው እንደሆነ ምንም ፋይዳ የለውም፣ ሲሉ ልንጥቀምበት እንዳለብን አሳስበዋል፣
“ጨው ነገሮች ጣዕም እንዲኖራቸው ስንጠቀምበት ትርጉም አለው፣ እንዲሁም ለረዥም ጊዜ የተቀመጠ ጨውም በእርጥበት ምክንያት ጣዕሙና ኃይሉን ያጠፋል፣ ከጌታ የተቀበልነው ጨው እንድንሰጠው እንድንጠቀመው ነው የተሰጠን፣ አለበለዝያ ጣዕሙን ያጠፋል ምንም ጥቅምም የለውም፣ ጌታን ጣዕመቢስ ክርስትያኖች እንዳንሆን እንለምነው፣ ሆኖም ግን ጨው ሌላ ልዩ ባህርይም አለው፤ በምግብ ስንጠቀምበት በትክክለኛ መጠን የጨመርነው እንደሆነ ጨዋማነቱ አይሰማም፣ ያ የምንመገበው ምግብ ጣዕም ነው የሚሰማን፤ በሌላ አገላለጥ ጨው ምግብን ጣዕም እንዲኖረው ይረዳል፣ ለጣዕም ብቻ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ ሳይበላሽ እንዲቀመጥም ይረዳል፣ የክርስትና ልዩ ስጦታም ይህ ነው፣ ስለዚህ እኛ እምነታችንን በዚህ ጨው ስንሰብክ ስብከቱን የሚቀበሉት በዚሁ ልዩ ስጦታ ይጣፍጣሉ ልክ ስለምግብ እንዳልነው፣ እያንዳንዱ ባለው ልዩ ሁኔታ ይህንን የክርስትያን ጨው ይቀበላል እጅግ ጣፋጭም ይሆናል፣
“የክርስትና ልዩ መሆን ሁሉም አንድ መለዮ እንደመልበስ አይደለም! እያንዳንዱ እንዳለው ሆኑ ማንነቱና ሰብአዊነቱን እንዲሁም ባህሉን በመጠበቅ በዚሁ ጨው ይጣፍጣል፣ ኅብረ ብዙሕነት ሃብት ነውና፤ ሆኖም ግን ጣዕም ይሰጠዋል፣ ይህ የክርስትና ልዩ ስጦታ መልካም ነገር ነው ምክንያቱም እኛ ሁሉን ነገር በአንድ መልክ ልናጣፍጥ ስንፈልግ እርሱ ግን ሁሉን እንዳሉት ያጣፍጣል፣ አለበለዚያ ልክ አንዲት ሴት በምግብ ላይ ብዙ ጨው የጨመረችና መግቡ ጣዕሙን አጥፍቶ ጨው ጨው እንደሚለው ይሆናል፣ የክርስትና ልዩ ስጦታ ግን እያንዳንዱ ጌታ ከሰጠው ስጦታዎች እንዳለ ሆኖ ሳለ በዚሁ ይጣፍጣል፣
ይህንን ጨው ግን ይዘነው መቀመጥ የለብንም እንድንሰጠው ነው የተሰጠን፣ ይህም ከገዛ ራሳችን ወጣ ማለት አለብን ማለት ይህንን ለሌሎች መስጠት ያለብን ጨው መልእክትና ሃብት ይዘን መውጣት ያስፈልጋል፣ ይህንን በሁለት ደረጃ ማድረግ አለብን መጀመርያ ጨውን መስጠትና ለሌሎች አገልግሎት ማዋል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከጨው ወዲያ በማሻገር ይህንን ጨው ወደ ሰጠን ወደ ፈጣሪ መሻገር ያስፈልጋል፣ ይህንን ሁለተኛ ደረጃ በጸሎትና በስግደት ማድረግ አለብን፣
“እንዲህ ስናደርግ ጨው ጣዕሙን አያጠፋም በሕይወታችንም ይኖራል፣ ጌታን በስግደት ሳመልክ ከኔ ባሻገር ወደ ሰማያዊ ነገሮች በመምጠቅ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ፣ ወንጌልን ለመስበክ በምወጣበትም ጊዜ መል እክቱን ለሌሎች ለማዳረስ ከገዛ ራስየ እወጣለሁ፣ ሆኖም ግን እነኚህን ሁለት ነገሮች ያላደረግን እንደሆነ ደግሞ በጠርሙዝ እንደተቀመጠ ጨው ሆነን ጣዕመቢስ በመሆን የቤተ መዘክር ክርስትያኖች ሆነን እንቀራለን፣ ምናልባት ይህ ነው ጨዋችን ብለን ማሳየት እንችላለን፤ በጥምቀት የተቀበልኩት ይህም በሜሮን የተቀበልኩት ይህም በትምህርተ ክርስቶስ የተቀበልኩት ወዘተ ሆኖም ግን አልጫ የሆነ ጨው ለምንም የማይጠቅም ጣዕመቢስ ነው የዚህ ዓይነት ክርስትያን የቤተ መዘክር ክርስትያን ነው፣ ሲሉ ስብከታቸውን ደምድመዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.