2013-05-22 16:03:18

የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ


RealAudioMP3 20ኛ ዓመቱን ያጠናቀቀው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ ምክንያት በማድረግ የቫቲካን ረዲዮ በተከታታይ በሥነ አቢያተ ክርስቲያን ጉባኤዎችና የቲዮሎጊያ ሊቅ የኢየሱሳውያን ማኅበር አባል በአባ ዳርዩዝ ኮውላዝዪክ አማካኝነት የሚያቀርበው ሳምንታዊ አስተምህሮ በመቀጠል፣ ትላንትና አባ ኮዋልዝዪክ በኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ኅማማት በተለይ ደግሞ ሞቱ ማእከል በማድረግ ባቀረቡት 27ኛ ክፍለ አስተምህሮ፦ “በዘመነ ጲላጦስ ስለ እኛ ተሰቃየ፣ ተሰቀለ ሞተ ተቀበረ” ስንል በተአምኖተ እምነት ዘንድ ያለውን ቃል እንደግማለን፣ ይህ ቃል እንቅፋት ነው። ለምን እግዚአብሔር በዓለም ታሪክ ውስጥ ገባ? ከሃሌ ኵሉ የሆነው ኃያሉ እግዚአብሔር እንዴት ገዛ እራሱን በመስቀል ይገልጣል? የሚለውን ጥያቄ በማቅረብ፣ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የትምህረተ ክርስቶስ መዝገብ ቁጥር 599፦ “በእግዚአብሔር የድኅነት ዕቅድ፣ የክርስቶስ ቤዛነት፦ የኢየሱስ በግፍ ሞት የአጋጣሚ ሁኔታ ውጤት ሳይሆን የእግዚአብሔር ዕቅድ ምስጢር ነው….” ስለዚህ ይህ ማለት ደግሞ የዚህ ወንጌላዊ ሁነት ቀንደኞች ተወናያን የመለኮታዊ ተግባር መተላለፊያ ወይንም ተካፋይነት የለሽ በተገዥ ባህርይ የሚገለጡ አይደሉም፣ እግዚአብሔር ያስባል ሆኖም ግን የሰው ልጅ ነጻነትን አይጥስም ብለዋል።
እግዚአብሔር አሳቢ በመሆኑም የእርሱ ሥጋ የሚለብሰው ፍቅሩ በአልቀበል ባይነት አመጽ እንደሚሰቃይ ቀድሞ ያውቃል፣ ሆኖም ግን ይኽ ትስብእት ከዓለም ታሪክ እንዲገለል አላደረገም፣ በመስቀል ከኃጢአተኛው ሰው ልጅ ጋር ቅርበቱንና ትብብሩን ገልጠዋል። ምንም’ኳ የእርሱ ጠላት የመሆን ጠባይ ቢኖረንም እርሱ እኛን ከማፍቀር አይቦዝንም። የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የትምህረተ ክርስቶስ መዝገብ የቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች የጻፈው መልእክት ምዕ. 5,8፦ “ነገር ግን እኛ ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ፣ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ሞቶአል፣ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ምን ያህል ታላቅ መሆኑ ያስረዳል።” ኢየሱስ ክፉዎችን ለመቅጣት ከመስቀል ገዛ እራሱን አላገለለም አላወረደም፣ እንዳውም ስለ እነርሱ፦ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” (ሉቃ. 23,34) ሲል ይጸልያል። ይኽ ደግሞ ዮሓንስ ወንጌል በምዕ. 13, 1 “እስከ መጨረሻ” የሚያፈቅር ገደብ የሌለው ፍቅር መሆኑ ይገልጥልናል ካሉ በኋላ፦ “በስቁል ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ፍጹም ኃያልነትን እንመለከታለን። ሆኖም ይኽ ከሃሌ ኵልነት የፍቅርና የምኅረት ኃይል ነው” ብለዋል።
የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ክርስቶስ መዝገብ በቁጥር 613 እንደሚያመለክተውም የኢየሱስ ፍቅር፦ …ሰውን ለሱታፌ ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ ወደ ቀድሞ ክብሩ የሚመልስ የምሕረት ደም ነው” በማለት ይገልጥልና። የፍቅር መሥዋዕት ነው። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው እና ቅዱስ በመሆኑም ምክንያት ኃጢአትን አይቀበልም፣ ኃጢአተኛውን ለማዳን ኃጢአት በገዛ እራሱ ተቀብሎ ያጠፋል፣ ይኸንን በመፈጸም ለሰው ልጅ ምህረትን እርቅን ይሠራል የዘለዓለማዊ ሕይወት ትንሣኤን ያጸናል በማለት ያቀረቡት አስተምህሮ አጠናቀዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.