2013-05-22 16:41:27

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ፤


ውድ ወንድሞችና እኅቶች! እንደምን አደራችሁ!
ጸሎተ ሃይማኖት ስንደግም በመንፈስ ቅዱስ አምናለሁ ብለን እምነታችን ከገለጥን በኋላ ወዲያውኑ “በአንድ ቅድስት እና ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን አምናለሁ” እንላለን፣ በእነዚሁ ሁለት አዕማደ ሃይማኖት መካከል ጥልቅ መተሳሰር አለ፣ ለቤተ ክርስትያን ሕይወት የሚሰጣትና በጉዞዋ የሚመራት መንፈስ ቅዱስ ነው፣ ካለመንፈስ ቅዱስና የማያቋርጠው እርዳታው ቤተ ክርስትያን ለመኖር እና ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ ወደ መላም ዓለም ሄዳ ለማስተማርና ሁሉንም የዓለም ሰዎች የእርሱ ተከታዮች እንድታደርግ የሰጣት ተልእኮን (ማቴ 28፤18) እውን ማድረግ አትችልም ነበር፤ ስብከተ ወንጌል የመላዋ ቤተ ክርስትያን ተልእኮ ነው፤ የአንዳንድ ብቻ እንዳይመስላችሁ ነገር ግን የእኔ ያንተ የሁላችን ተልእኮ ነው፣ ሐዋርያ ጳውሎስ “ወንጌል ካልሰብኩ ወዮልኝ” (1ቆሮ 9፣16) በማለት ያውጃል፣ እያንዳንዳችን ሰባኬ ወንጌል መሆን አለብን! በተለይ ደግሞ በኑሮ አችን መስበክ አለብን፣ ር.ሊ.ጳ ጳውሎስ 6ኛ ኢቫንጀሊ ኑንስያንዲ በሚለው ሐዋርያዊ ም ዕዳናቸው ቍ.14 “ስብከተ ወንጌል የቤተክርስትያን ጸጋና ጥሪ እንዲሁም የጠለቀ ማንነትዋ ነው፤ ቤተ ክርስትያን ወንጌል ለመስበክ ብቻ ነው የምትኖረው” ብለዋል፣
በሕይወታችንና በቤተ ክርስትያን ሕይወት የስብከተ ወንጌል አንቀሳቃሽ ማን ነው? ር.ሊ.ጳ ጳውሎስ ስድስተኛ ጥርት ባለ መንገድ “እርሱ ነው! መንፈስ ቅዱስ! በቤተ ክርስትያን መጀመርያ ላይ እንዳደረገው አሁንም በእያንዳንዱ ስብከተ ወንጌል ሁሉ በእርሱ እንዲሞላና ወደ እርሱ እንዲᎀጣ እየሰራ ነው፤ ብቻችን ልናገኛቸው የማንችል ቃላትን በልቦቻችን እያኖረ እንዲሁም የተቀባዩን ነፍስ መልካሙን ዜና እና የሚሰበከውን የእግዚአብሔር መንግሥት ለመቀበል እንዲችል ያደርገዋል” (ኢቫንጀሊ ኑንስያንዲ ቍ. 75)፣ ስለዚህ ወንጌልን ለመስበክ እንደገና አንዴ ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ልባችን መክፈት አስፈላጊ ነው፣ ይህንን የምናደርገው ደግሞ ምን ለማድረግ እንደሚጠይቀንና የት እንደሚመራን ሳንፈራ ነው፣ በእርሱ እንተማመን! እርሱ እምነታችን ለመኖርና ለመመስከር ያስችለናል፤ የምናገኛቸው ሰዎች ልብም ሊያበራ ነው፣ የጴንጠቆስጤ ፍጻሜ ይህንን ያረጋገጥልናል፣ ሐዋርያት ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጋር በጽርሓ ጽዮን ተሰብስበው ሳሉ “ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።” (የሐ ሥራ 2፡2-4)፣ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ሲወርድ በፍርሓት ተዘግተውበት ከነበሩበት ቤት እንዲወጡ ከገዛ ራሳቸውም እንዲወጡ በማድረግ የእግዚአብሄር ታላላቅ ሥራዎች ስባኪዎችና መስካሪዎች ያደርጋቸዋል፣ ይህ የሐዋርያት መለወጥ ደግሞ በጽርሐ ጽዮን አከባቢ የነበሩና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች “ከሰማይ በታች ካሉ ሁሉ አገሮች” የመጡ ሰዎች ላይም ተሸጋግረዋል፣ ምክንያቱም ሁላቸው በየቋንቋዎቻቸው ይሰምዋቸው ነበርና፣
እዚህ ላይ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የወንጌልን ስብከት ሲመራና ሲያራምድ እናያለን አንድነት ውህደትም ይታያል፣ በባቢሎን መጽሓፍ ቅዱስ እንደሚተርከው የሰዎች መበታተንና የቋንቋዎች መዘባረቅ ጀመር፤ ይህም የሆነው የሰው ልጆች በትዕቢት ተገፍተው አለእግዚአብሔር በጉልበታቸው ብቻ “ሰማይ የሚነካ ግንብ ያላት ከተማ” ሊያንጹ በማቀዳቸው ነበር (ዘፍ 11፤4)፣ በጴንጠቆስጠ ግን እነኚህ መከፋፈሎች አክትመዋል፣ ከእግዚአብሔር ጋር መወዳደር የለም፡ አንዱ ከሌላው የሚዘጋበት ሁኔታም የለም፣ ሆኖም ግን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክፍት ሆነ፤ ቃሉን ለመስበክ ሁሉም ወጣ፤ መንፈስ ቅዱስ በልቦቻችን የሚያኖረው አዲስ ቋንቋ የፍቅር ቋንቋ የሆነው ሁላቸው ሊረዱት የሚችሉትና በሁሉም የዓለም ኑሮዎችና ባህሎች ተቀባይነት ያለውና ሊገለጥ የሚቻል ቋንቋ ተሰጠን፣ የውህደትና የወንጌል ቋንቋ የሆነው የመንፈስ ቅዱስ ቋንቋ ግድየለሽነትና በገዛ ራስን መዝጋትን እንዲሁም መለያየትና መቃወምን ለመሻገር ጥሪ ያቀርብልናል፣ ሁላችን ለገዛ ራሳችን “የእምነት ምስክርነቴ የአንድነትና የውህደት እንዲሆን መንፈስ ቅዱስ እንዲመራኝ እፈቅዳለሁኝ? በምኖራቸው አከባቢዎች የዕርቅና የፍቅር ቋንቋ የሆነው ቃለ ወንጌልን እሰብካለሁን? አንዳንዴ መከፋፈል ለመረዳዳት አለመቻል፤ውድድር ቅናትና ለእኔ ብቻ ባይነት ገኖ ሲታይ ያ በባቢሎን የሆነው ዛሬ የሚደገም ሆኖ ይሰማናል፤ እኔስ በሕይወቴ ምን አበርክታለሁ? በአከባቢየ አንድነትን አጠነክራለሁ ውይንስ በሕሜታና በቅናት እከፋፍላለሁ? ይህንን እናስብ፣ ወንጌልን መስበክ ማለት አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ዕርቁ ምሕረቱ ሰላሙ አንድነቱና ፍቅሩን በሕይወት መኖርና መመስከር ነው፣ ኢየሱስ የሚለንን እናስታውስ “ከእነዚህ ፍሬዎቻችሁ የእኔ ደቀመዛሙርት መሆናችሁን ሊያውቁ ናቸው፣ እርስ በእርሳችሁ የተዋደዳድችሁ እንደሆነ” (ዮሐ 13፤34-35)፣
ሁለተኛ ነጥብ ደግሞ በጴንጠቆስጤ ዕለት ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ ጥርት ባለ መንገድ ተናገራቸው ኢየሱስ ስለደኅንነታችን እንደሞተና እግዚአብሔር አብም ከሙታን እንዳነሣው የሚገልጠውን መልካም ዜናን አበሰራቸው፣ ይህ አንዱ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ይህ ነው የኢየሱስ ወንጌልን በብርታትና በጥራት አለምንም ፍርሃት ድምጽን ከፍ አድርጎ በማንኛው ጊዜና በማንኛው ቦታ መስበክ ነው፣ ይህ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ወይንም በጰንጠቆእስጤ እሳት የተደረገው ፍጻሜ ዛሬም በቤተ ክርትያናችንና በእያንዳንዳችን እየተፈጸመ ነው፤ ሁሌ አዳዲስ የስብከተ ወንጌል ኃይሎች የደኅንነት መልእክት የሚሰበኩባባቸው የተለያዩ መንገዶች እና አዳዲስ ብርታቶች እየፈለቁ ናቸው፣ ለዚህ ሥራ ልባችን አንዝጋ! ወንጌልን በትሕትናና በብርታት እንኑረው! እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚገልጠውን ሕዳሴው ተስፋውንና ደስታውን እንመስክር! ር.ሊ.ጳ ጳውሎስ ስድስተኛ በኢቫንጀሊ ኑንስያንዲ በሚለው ሐዋርያዊ ምዕዳናቸው ቍ 80 ላይ እንዳሉት “የስብከተ ወንጌል ጣፋጭና አጽናኝ ደስታ” ይሰማን፣ ምክንያቱም ኢየሱስን ማብሰርና ወንጌሉን መስበክ ደስታ ይሰጠናልና፤ በዚህ አንጻር በገዛ ራሳችን ተዘግተን የቀረን እንደሆነ ጭንቀትና ኃዘን እንዲሰማን በማድረግ ዝቅ ያደርገናል፣ ወንጌልን መስበክ ግን ከፍ ከፍ ያደርገናል፣
ሶስተኛውን ነጥብ ለመጥቀስ ያህል፤ ይህም አስፈላጊ ነው፤ ለሓዲስ ስብከት የምትዘጋጅ ቤተ ክርስትያን ሁሌ ከጸሎት መነሳት አለባት፤ ይህ ማለትም ሓዋርያት በጽርሓ ጽዮን እንዳደረጉት የመንፈስ ቅዱስ እሳትን መለመን ያስፈልጋል፣ ከእግዚአብሄር ያለን የመተማመንና የጦፈ ግኑንነት ብቻ ነው በገዛ ራሳችን ከመዘጋት ወጥተን በብርታት ወንጌልን ለማስበክ የሚያስችለን፣ ካለ ጸሎት የሚደረግ ስራ ሁሉ ባዶ ነው ስብከታችን አያንጽም ምክንያቱም በመንፈስ ቅዱስ አልተንቀሳቀስምና፣
ውዶቼ! ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16 ባለፈው የጳጳሳት ሲኖዶስ እንዳሉት ቤተ ክርስትያን ባለነው ዘመን “ከሁሉ በላይ የሚረዳን ትክክለኛውን መንገድ የሚመራን የመንፈስ ቅዱስ ንፋስ እያጣጣመች ናት፤ በዚህም በአዲስ ኃይል ጉዞ አችን እንጀምራለን ጌታንም እናመሰግናለን”፣ በየዕለቱ ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ያለንን ታማኝነት እናሳድስ! ይህ ታማኝነት እርሱ በእኛ ውስጥ እንዳለና እየሰራ መሆኑን የሚያረጋግጥልን ታማኝነት ነው፣ እርሱ ሐዋርያዊ ኃይልና ቅናት ሰላምና ደስታ ይሰጠናል፣ ይህንን መተማመን እንሳድሰው፣ በእርሱ እንመራ! በዓለማችን የእግዚአብሔር አንድነትና ሱታፌ መሣርያ በመሆን በብርታት ወንጌልን የሚመሰክሩ የጸሎት ሰዎች እንሁን!








All the contents on this site are copyrighted ©.