2013-05-21 17:49:19

በዓለ ጰራቅሊጦስ


በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ ትናንትና እኁድ በዓለ ሐምሳ ማለትም በዓለ ጰራቅሊጦስ በታላቅ ክብር ተዘክረዋል፣ በመንበረ ጴጥሮስም ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የመሩት ዋዜማ ማኅሌትና ቅዳሴ በታላቅ መንፈሳውነት ተካሄደ፣ ዓመተ እምነትን ምክንያት በማድረግ ደግሞ ከመላው ኢጣልያና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰበሰቡ የተለያዩ ክርስትያናዊ እንቅስቃሴዎች ቡድኖች በተለይ ደግሞ ካቶሊካዊ መታደስ በመንፈስ ቅዱስ የሚለው ካሪዝማቲክ ቡድን ከቅዳሜ ጀምሮ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይና አካባቢው ባሉ ጐዳናዎች ተሰብስበው በተለያዩ ጸሎት መዝሙሮችና አስተንትንዎች እንዲሁም በሥር ዓተ ዋዜማው ቅዱስነታቸው ከእነዚሁ እንቅስቃሴዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስና አባታዊ ምክር ሰጥተዋል፣ ትናንትናም በብዙ ካርዲናሎች ጳጳሳትና ካህናት መሥዋዕተ ቅዳሴ አሳርገዋል፣ በቅዳሴው ባሰሙት ስብከት “ለእግዚአብሔር ክፍት እንድንሆን ፍርሃትን ማሸነፍና ሰብአዊ ዕቅዶችንና የደኅንነት ዋስትናዎችን መተው ያስፈልጋል፣ መከፋፈል ለሚያስከትሉ ልዩነትና ቡድናዊ አስተሳሰብ እምቢ ማለት ያስፈልጋል” ሲሉ ሁሉም ለአንድነት እንዲሰለፍ ጠርተዋል፣ ቅዱስነታቸው በስብከታቸው የተጠቀምዋቸው ሶስት ቍልፍ ቃሎች ሕዳሴ አንድነትና ተልእኮ የሚሉ ነበሩ፣ ሶስቱም ቃላት ደሞ የመንፈስ ሥራን ይገልጣሉ፣ ይህም ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ክርስቶስ ስጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስትያናችን ሕይወትና በሕይወታችን እንዲሰራ እንድንፈቅድለት ይሁን ብለዋል፣
“የጸጋ ፍጻሜ ሆኖ የኢየሩሳሌም ጽርሓ ጽዮንን እስከ አጽናፈ ዓለም እንዲስፋፋ የሞላው የመንፈስ ቅዱስ እሳት ነው፣ በጽርሓ ጽዮን ሓዋርያት ልባቸውና አእምሮአቸው ከሰማይ በድንገት በመጣው ተጨባጭና ትክክለኛ በሆነው የእሳት ምላስ ተነክተው በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው እዛ ለነበሩት በተለያዩ ቋንቋዎች የእግዚአብሔር ታላላቅ ሥራዎችን ማወጅ በጀመሩት ጊዜ ለሁሉም አስደንቀዋል፣ እኛስ ለዚህ ዓይነት ሕዳሴ ዝግጁ ነንን፧
“ሕዳሴ ሁሌ ፍርሃት ፍርሃት ያሰኛል፤ ምክንያቱም ሁሉንን በቍጥጥራችን ሥር ስናኖር ብቻ ዋስትና ስለሚሰማን ነው፤ ሆኖም ግን ብቻችን ለመሥራት ለማቀድና ሕይወታችንን እኛ ባቀድናቸው መርሖች ዋስትናዎችና ደስ በሚሉን ነገሮች ለመምራት እንፈልጋለንና፣ ይህ አግባብ ከእግዚአብሔር ጋር ለምናደርገው ግኑኝነትም ልንጠቀመው እንሻለን፤ እግዚአብሔር ለኔ እስከመቸኝ እና በዕቅዴ እስከ ተስማማ እከተለዋለሁ፤ ባጠቃላይ በእርሱ መተማመን ይከበደናል፤ እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራን እና በሕይወታችንና በምርጫዎቻችን እርሱ እንዲያበራን ሁሉንም በእጁ መተው ይከብደናል፣
“እግዚአብሔር አዳዲስ መንገዶች ውስጥ እንዳይመራን እንፈራለን፤ ከተወሰነው የኑሮ አችን ዘዴ እንዳያወጣን እንሰጋለን፣ ግላዊ ጥቅማችንን ያስቀደመው ዝግ የሆነው አስተያያታችንን ለእርሱ መክፈት ያስፈራናል፣ ሆኖም ግን በእውነት የሚያሳድገንን ሕይወታችንን እውን የሚያደርገው የእግዚአብሔር ሕዳሴ ነው፣ ይህም ማለት እውነተኛ ደስታንና ሰላምን የሚሰጠን ሕዳሴው ነው፤ ምክንያቱም እግዚብሔር ያፈቅረናል ዘወትርም መልካማችን ይሻል፣
“ሕዳሴው ለሕዳሴ ተብሎ አይደለም የሚመጣው ማለትም በኑሮአችን ሁሌ እንደሚያጋጥመው ልማዳዊ ሕይወት በሚሰለቸን ግዜ አዲስ ነገር እንደምንፈልገው ነገር አይደለም፣
“እግዚአብሔር ለሚያቀርብልን ያልታሰቡ አስደናቂ ነገሮችን ለመቀበል ዝግጁ ነንን?ወይስ በፍርሃት ተገዝተን ለመንፈስ ቅዱስ ሕዳሴ ራሳችንን እንዘጋለን? የእግዚአብሔር ሕዳሴ የሚያቀርበልንን መንገዶች ለመጓዝ ብርታት አለን ወይ? ወይስ በገዛ ራሳቸው ዝግ ሆነው አንቀበልም በሚሉ ዕቅዶቻችንን ተገን አድርገን እንከላከላለን? እንዚህን ጥያቄዎች ደጋግመን ቀኑን ሙሉ ያስተንተንን እንደሆነ መንፈሳዊ ጤና ሊሰጡን ይችላሉ፣ ሲሉ መንፈስ ቅዱስ ለሚሰጠን ሕዳሴ መፍራት እንደሌለብን አሳስበዋል፣
በሌላ በኩል ለሥርዓት ስንል የሚሰማን ፍርሃትና ጥርጣሬን እንዴት ማስወገድ ይቻላል ለሚል ጥያቄ ለመመለስ በሚመስል ዓይነት ቅዱስነታቸው ያቀረቡት ሓሳብ ምናልባት መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ስጦታዎች በመስጠት በቤተ ክርስትያን ውስጥ የሚያደፈርስ ሆኖ የሚሰማን ከሆነ ልዩነቱ ሃብት መሆኑን ማወቅና መቀበል እንደሚያስፈልግ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የአንድነት መንፈስ ነውና፣ ይህ ማለትም አንድ ዓይነት መለያ ወይም ደንብ ሳይሆን ውህደት ነው፣ እንዲህ ማድረግ የሚችለው ደግሞ እርሱ ብቻ ነው፣ ሲሉ አንድነት በብዙኅነት ወይም ኅብረ ብዙነት መሆኑን ገልጠዋል፣ ሆኖም ግን ይህ ለመለያየትና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በማለት ጽንፈኝነትን እንዳያስከትል እንዲህ ሲሉ አሳስበዋል፣
“እዚህም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ አለ፤ ልዩነቱን የምፈጥረው እና ከሆንና በልዩነቶቻችን ተዘግተን የምንቀር ከሆነ ቡድኖች በመፍጠር መከፋፈልን ልናስከትል እንችላለን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አንድነትን በሰብአዊ ዕቅዶቻችንና በምንፈጥራቸው መለዮ ሐሳብ ልናደርገው የሞከረን እንደሆነም እንሳሳታለን፣ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እና ተል እኮ ባላቸው እረኞች ተመርቶ በአንድነት የሚደረግ ጉዞ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምልክት ነው፣
“የዚህ ዓይነት ቤተ ክርስትያን ክርስቶስን የምትሰጠኝና ወደ ክርስቶስ የምትመራኝ ቤተ ክርስትያን ናት፤ ይህንን በመጻረር በውድድር የሚደረጉ ጉዞዎች አደገኞች ናቸው፣ ስለዚህ ከቤተ ክርስትያን አንቀጸ ሃይማኖትና ሱታፌ ቅዱሳን ውጭ የሚደረግ ጀብደኝነት የለም፣
“ስለዚህ እንዲህ ብለን ገዛ ራሳችንን እንጠይቅ፤ ማንኛው ማግለልልና ብቸኛነትን በማሻገር ለመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ክፍት ነኝን፧ በቤተ ክርስትያን ውስጥና ከቤተ ክርስትያን ጋር በመኖርስ በመንፈስ እመራለሁን? ብለን ኅሊናችን እንመርምር ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የስብከተ ወንጌል ተልእኮ አንቀሳቃሽ ነውና፣
“መንፈስ ቅዱስ በሕያው የእግዚአብሔር ምሥጢር እንድንገባ ያደርገናል፣ እንዲሁም በገዛ ራስዋ ዝግ ከሆነችና አምባገነን ቤተ ክርስትያንም ያድነናል፣ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በኢየሩሳሌም በጽርሓ ጽዮን የተፈጸመው ጴንጠቆስጤ መጀመርያ ነው፣ ይህ ሁሌ እውን የሚሆን መጀመርያ ነው፣ ሲሉ ስለመንፈስ ቅዱስ ሥራ በሰፊው ከገለጡ በኋላ የሚከተልውን የመጨረሻ ጥያቄ አቅርበዋል፣
“እንደማኅበር መጠን በገዛ ራሳችንና በቡዳናችን ብቻ ተዘግተን የመቅረት ዝንባሌ ያለን እንደሆነ ወይንም መንፈስ ቅዱስ ለተል እኮው ክፍት እንድንሆን ፈቃደኞች እንደሆንን ገዛ ራሳችን እንጠይቅ፣ ዛሬ እነኚህን ሶስት ቃላት እናስታውስ ሕዳሴ ሱታፌና ተልእኮ፣ በማለት እያንዳንዱ ግለሰብና ማኅበረ ክርስትያን በመንፈስ ለመታደስና ለመመራት ክፍት እንዲሆን ከቤተ ክርስትያን ጋር በውህደትና በሱታፌ እንዲኖሩና ለስብከተ ወንጌል ተል እኮ እንዲነሱ አሳስበዋል፣

ቅዱስነታቸው ቅዳሴ ከፈጸሙ በኋላ የንግሥተ ሰማያት ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት ከ300 ሺ በላይ ለሚሆኑ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይና በአከባቢው በሚገኙ ጐዳናዎች ለተሰበሰቡት “አዲስ ጴንጠቆስጠ የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይን በክፍት ሰማይ አዲስ ጽርሓ ጽዮን አደረገው፣ ትናንትና በዋዜማና ማኅሌተ ሌሊት የጀምርነው ዛሬ በምሥጢረ ሥጋሁ ወደሙ የፈጸምነው ይህ በዓል የእምነት በዓልም ሆኖልናል፣ እውነትም እንደገና የምትወለድ ቤተ ክርስትያንን አይተናል” ሲሉ ቅዱስነታቸው በበዓሉ የተሰማቸውን እርካታ ገልጠዋል፣
“እኛም በተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የአንድነት መልካምነትን አጣጥመናል፣ አንድ ነገር ብቻ መሆንን፣ ይህም ሁሌ የቤተ ክርስትያንን አንድነት እንዳዲስ ነገር የሚፈጥረው መንፈስ ቅድስ ሥራ ነው፤ ሲሉ ደስታቸውን ገልጠዋል፣
አያይዘውም ከቅዳሜ ማታ ጀምረው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተሰብስበው በመጸለይ ለተገኙት የተለያዩ ክርስትያናዊ እንቅስቃሴዎች ማኅበሮችና የቤተ ክርስትያን ቡድኖች እንዲህ ሲሉ አመስግነዋል፣
“ለቤተ ክርስትያን ታላቅ ስጦታና ሃብት ናችሁ! ሁላችሁን አመሰግናለሁ! በተለይ ደግሞ ከሮማና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመጣችሁ ሁሉ! ሁሌ የወንጌል ኃይል ይዛችሁ ተጓዙ! አትፍሩ! ሁሌ የቤተ ክርስትያን ደስታ የሱታፌዋ ፍቅር ይኑራችሁ! ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ጌታ ሁሌ ከእናንተ ጋር ይሁን እመቤታችን ድንግል ማርያም ትጠብቃችሁ ሲሉ ከመረቅዋቸው በኋላ የንግሥተ ሰማያት ጸሎት አሳርገዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.