2013-05-20 15:47:19

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ.፦ አሉባልተኝነት ቤተ ክርስቲያንን ያወድማል፣ የተዛባ የሃሰት መረጃ ስም ማጥፋትና ሀሜት ኃጢአት ነው


RealAudioMP3 እ.ኤ.አ. ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ እንደተለመደው በአገረ ቫቲካን ቅድስት ማርታ ሕንፃ በሚገኘው ቤተ ጸሎት በጳጳሳዊ የላተራነንሰ መንበረ ጥበብ ዋና አስተዳዳሪ ብፁዕ አቡነ ኤንሪኮ ዳል ኮቮሎ የተመሩት የዚሁ መንበረ ጥበብ ተማሪዎች ቡድን የንኡሳን ማኅበረ ክርስቲያን ጉዞ የተሰየመው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ መሥራቾች ኮኮ አርጒየሎና ካርመን ሄርናንደስ የተመሩት አንድ የዚሁ እንቅስቃሴ አባላትና የአርነትና ሱታፌ ካቶሊካዊ እንቅስቃሴ አባላት ሮበርቶ ፎንቶላንና ኤሚሊያ ጉዋሪኒየሪ የተመሩት የዚሁ ማኅበር አባላት የተሳተፉበት ከሮማ ሰበካ ካህን አባ ዳኔኤለ ግረክ ጋር በመሆን በመሩት መሥዋዕተ ቅዳሴ ባሰሙት ስብከት፦ “ክርስቲያን በሌላ ሰው ሕይወት ጣልቃ ከመግባት ፈተና መቆጠብ አለበት” የሚል ቃለ ምዕዳን ማእከል በማድረግ የዕለቱ ምንባበ ወንጌል ተንተርሰው፦ “ስንት አሉባልተኝነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ እኛ ክርስቲያኖች ምንኛ በዚህ ፈተና የተጠቃን ነን። አሉ ባሉባልተኝነት የሌላውን ቆርበት መላጥ፣ እርስ በእርስ መጎዳዳት ማለት ነው። የሌላውን ስም ስናጠፋ ክብሩን እናንቋሽሻለን። ሌላው እንዲያድግ ከማድረግ ይልቅ ጎድሎና ተዋርዶ እንዲገኝ እንቀሳቀሳለን። ሌላውን ዝቅ በማድረግ እኔነትን ከፍ ለማድረግ። ሆኖም ይኽ መንገድ የሚበጅ አይደለም። አሉባልተኝነት ለምን እንደሆነ አይገባኝም ደስ ያሰኘናል። መልካም ተመስሎ ይታየናል። ልክ እንደ ጣፋጭ ማር እንድ ሁለት እያልክ በመደጋገም የሚወሰድ ሆኖ በመጨረሻ ግን የሆድ ቁርጠት ነው የሚሆነው። ማር ሲበዛ እንደሚባለው ነውና። አሉባልተኝነት በመጀመሪያ ይጣፍጣል በመጨረሻ ግን ያወድማል፣ መንፈስን ያወድማል፣ ቤተ ክርስቲያንን ያወድማል፣ አሉባልተኝነት የቃኤል መንፈስ የሚኖር ነው። ወንድምህን መግደል፣ በምላስ ወንድምህን መግደል።” ማለት መሆኑ የገለጡት ቅዱስ አባታችን ቀጥለውም፦ የተዛባ የሃሰት መረጃ ወይንም ዜና እናቀርባለን፣ ወይንም አንድ ዜና ስናቀርብ ሙሉ ለሙሉ በሙላት ሳይሆን ገሚሱን ይኽም ለእኛ የሚበጅ ባለ መሆኑ ለኛ እንደሚበጀን እውነትን በከፊል እናቀርባለን፣ …ማጥላላት፣ አንድ ሰው ሲሳሳት ደስ ተሰኝቶ እንዲዋረድ ለማድረግ ስለ እርሱ መናገር፣ ታዋቂነቱን ዝቅ ለማድረግ፣… ስም ማጥፋት ሌላውን ለማጥላላት እውነት ያልሆነውም መንዛት፣ ኃጢአት ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ኃጢአቶች መፈጸም ማለት የኢየሱስን በልጆቹና በወንድሞቹ ላይ በደል በመፈጸም እርሱን መቃወም ወይንም መውገር ማለት ነው” ብለዋል።
አሉባልታ የማይበጅ መሆኑ ቅዱስ አባታችን ሲገልጡ፦ “ቤተ ክርስቲያንን ያወድማል፣ ኢየሱስ ተከተለኝ ሲል፣ መዳን ከሌሎች ጋር በመፎካከር ወይንም ከሌላው ጋር በመነጻጸር ወይንም በአሉባልተኝነት የሚከወን እንደሆነ አድርገን እንገምታለን። ድህነት ኢየሱስን በመከተል ነው” ካሉ በኋላ፦ ‘በሌሎች ሕይወት ጣልቃ ከመግባት እንቆጠብ ዘንድ ይኸንን ጸጋ ጌታ ይሰጠን ዘንድ እንለምነው። በአግባብ የተካኑ መጥፎ ልማድ ያላቸው ክርስቲያኖች እንዳንሆን ጌታን እንለምነው። ኢየሱስን እንከተል ዘንድ በእርሱ መንገድ እንጓዝ ዘንድ ይኽንን ጸጋ እርሱን እንለምነው። እርሱን መከተል ብቻ ይበቃናል” ሲሉ ያሰሙትን ስብከት አጠቃለዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.