2013-05-18 09:14:59

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ.፦ ቤተ ክርስቲያን የምትሻውና የሚያገለግላት ከጋለ ሓቀኛ ስሜት የመነጨ ሐዋርያዊነት እንጂ የእልፍኝ ክርስቲያኖች አይደለም


RealAudioMP3 እ.ኤ.አ. ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ጧት በአገረ ቫቲካን ባለው የእንግዳ መቀበያ ቅድስት ማርታ ሕንፃ በሚገኘው ቤተ ጽሎት ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ጳጳሳዊ የፍትህና ሰላም ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ፐተር ቱርክሶና ዋና ጸሓፊያቸው ብፁዕ አቡነ ማሪዮ ቶሶ ጋር በመሆን የዚሁ ጳጳሳዊ ምክር ቤትና የቫቲካን ረዲዮ ሠራተኞች የተሳተፉበት መሥዋዕተ ቅዳሴ መርተው፦ ቤተ ክርስቲያን የምትሻው የኢየሱስ ብሥራት ወደ ፊት እንዲል የሚያደርገው ከጋለ ሓቀኛ ስሜት የመነጨ ሐዋርያዊነት እንጂ የእልፍኝ ክርስቲያኖችን አይደለም የሚል ሓሳብ ማእከል ያደረገ ስብከት ማሰማታቸው የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ አለሳንድሮ ጂሶቲ አስታወቁ።
“ቅዱስ ጳውሎስ ለሌሎች መሰናክል ሆኖ ነው የተገኘው። በስብከቱ በሙያው በምግባሩ እንቅፋት ሆኖ ነው የተገኘው። የኢየሱስ ክርስቶስ ብሥራት ለግል እርባናና ክብር ለመዋቅሮች ጠቀሜታ ታልሞ የሚቀርብ ሲሆን ጳውሎስ ለዚህ ዓይነቱ ብስራትና ሕይወተ ክርስትና እንቅፋት ነው። ጌታ ከእኛ የሚፈልገው እኛ ወደፊት እንድንል ነው። በተመቻቸና በተረጋጋ ሊፈርስ በሚችለው ሁነት ሕይወታችን ከልለን ለመኖር እንራወጣለን። ጳውሎስ ጌታን ያበስር በመሆኑ እንቅፋት ሆኖ ነው የተገኘው። ሆኖም ግን ምንም ሳይበግረው ቀናተኛው ክርስትያናዊ ምግባረ ሐዋርያዊነት የነበረው በመሆኑ ወደ ፊት ይል ነበር። ከጋለ ሓቀኛ ስሜት የመነጨ ሐዋርያዊነት ይኖር ነበር። ጳውሎስ አስመሳይ አልነበረም። እውነትንና የኢየሱስ ክርስቶስ በማስቀደም ወደ ፊት የሚል በመሆኑ ለሁሉም እንቅፋት ነበር” ካሉ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ነበልባል ሰው እንደነበርና ይኽም ምግባሩን የሚመለከት ብቻ ሳይሆን ሁለመናው ነበልባል ነው። ጌታም በዚህ የጳውሎስ ነበልባልነት ውስጥ በዚህ የጦርነት መስክ ውስጥ በመግባት ወደ ፊት እንዲል እንዳደረገው ሲያብራሩ፦ ይቆይልኝ ማለት እንወዳለን ለገዛ እራሳችን ለቁምስናችን ለሰበካችን ብቻ ጌታ ያስብ ዘንድ እንወዳለን። በእውነቱ እድለኞች ነን። ሐዋርያዊ ቀናተኛነት ለግል ጥቅም ወይንም ሥልጣን ለመጨበጥ ታልሞ ሳይሆን ከልብ የመነጨ እውነተኛ ስሜት መሆን አለበት። ይኸንን ነው ጌታ ከእኛ የሚፈልገው። ይኽ ዓይነቱ እውነተኛው የጋለ ስሜት ከየት ይገኝ ይሆን? ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቅ ካለን ኅሊናዊ ግንዛቤ የሚመነጭ ነው። ጳውሎስ ኢየሱስን አግኝቶታል፣ ከኢየሱስ ጋር ተገናኝተዋል። ይኽ የጳውሎስ ጌታን ማወቅ በርግጥ አስፈላጊ ቢሆንም በቅድሚያ ሁለተኛ ደረጃ የሆነው ለቀዳሜው እርሱም ከግላዊና ከልባዊ ግኑኝነት ለሚረጋገጠው ማወቅ የሚደግፍ ሥነ ምርምራዊ ወይንም ሥነ ጥናታዊ እውቅት አይደለም። ስለዚህ በቅድሚያ ልባዊና ግላዊ ግኑኝነት አስፈላጊ ነው” እንዳሉ ጂሶቲ ገለጡ።
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊት እንዲል የሚገፋፋው ኢየሱስ ክርስቶስን ማወጅ የሚል ዓላማ ነው። ይኽ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ለችግር ለአደጋ አጋልጦታል፣ ስለ ኢየሱስ ሲል ለመከራ ሁሉ መጋለጡና፣ የጋለ ሐዋርያዊ ስሜት ከፍቅር የሚመነጭ መሆኑና፣ ይኽ ደግሞ ገዛ እራስ መሳትን ሊያሰማ ይችላል ነገር ግን መንፈሳዊነት የተሞላ ሕይወት የሚያመለክት ሲሆን፣ ስለዚህ ለዚህ ዓይነቱ የጋለ ሐዋርያዊ ስሜት መንፈስ ቅዱስ ያበረታን ዘንድ እርሱን መጠየቅ እንደሚገባን ሲገልጡ፦ የእልፍኝ ክርስቲያኖች እንዳሉ የታወቀ ነው። እነሱም በሚገባ የታነጹ አደብ የተሞሉ ሁሉም መልካም የሆነላቸው ‘የሚያከብሩና የሚከበሩ’ እንጂ በቤተ ክርስቲያን ተልእኮ በመሳተፍ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መሆንን የማያውቁ ናቸው። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በዚህ የጋለ ሐዋርያው ስሜት የሞላን ዘንድ እንለምነው። እንደ ጳውሎስ ለብ ባለና በተረጋጋ መንፍስ ደልቶዋቸው በቤተ ክርስቲያን ለሚኖሩት እንቅፋት የመሆን ጸጋ ይስጠን። ወደ የከተሞቻችን ውጫዊ ክፍሎች ወደ ተረሱት የከተሞቻችን ክልሎች እንድንሄድ ቤተ ክርስቲያን ይኽ ዓይነቱ መንፈስ እጅግ ያስፈልጋታል፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማያውቁት ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን እዚህ በክተሞቻችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወጅ እጅግ አንገብጋቢ ነውና። ስለዚህ ቅዱስ መንፈስ የጋለ ሐዋርያዊነት ክርስቲያናዊ መንፈስ በእኛ ያኑር። እንደ ጳውሎስ እንቅፋት ሆነን የተገኘን እንደሆነ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁነው። ጌታ ለጳውሎስ እንዳለው ወደ ፊት እንበል። በርቱ” በማለት ያሰሙት ስብከት እንዳጠቃለሉ ጂሶቲ ገለጡ።








All the contents on this site are copyrighted ©.