2013-05-16 19:59:05

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ውድ ወንድሞችና እኅቶች፤ እንደምን አደራችሁ!
ዛሬ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስትያንንና እያንዳንዳችን ወደ እውነት ስለሚመራን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ለመናገር እወዳለሁ፣ ኢየሱስ ራሱ ስለመንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ሲናገር “እርሱ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” (ዮሐ 16፡13) ምክንያቱም “እርሱ ራሱ የሓቅ መንፈስ ስለሆነ” (ዮሐ 14፤17፣ 15፤26፣16፤13) ብለዋል፣
ያለንበት ዘመን እውነት የሆነ ሁሉ የሚጠረጠርበት ዘመን ነው፣ ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ስለ ወላዋይነት ወይንም ረላቲቭዝም ብዙ ጊዜ ተናግረዋል፣ ይህም ወሳኝ እውነት ቍርጥ እውነት የለም፤ እውነት በአብላጫ የምናስበውና የምንፈልገው ነው፣ የሚል አስተሳሰብ ነው፣ ለመሆኑ በእውነት እውነት የሚባል ነገር አለ ወይ? እውነት ማለት ምን ማለት ነው? ልናውቃት እንችላለንን? ልናገኛችስ እንችላለንን? እዚህ ጲላጦስ ጴንጤናዊ በፍርድ ጊዜ ኢየሱስ ስለ ጥልቅ እውነትና ስለተልእኮው ሲነግረው ያቀረበው ጥያቄ ትዝ ይለኛል፤ “እውነትስ ምን ማለት ነው” (ዮሐ 18፤37.38)፣ ጲላጦስ እውነት ከእርሱ በፊት ተደቅኖ እንዳለ ለማወቅ አልቻለም፤ የእግዚአብሔር አብ ገጽታ የሆነው ኢየሱስ የእውነት ገጽታ መሆኑን ለማየት አልቻለም፤ ያም ሆነ ይህ እውነት ራሱ ኢየሱስ ነው፣ ይህም ግዜው በተደረሰ ጊዜ “ሥጋ ለብሰዋል” (ዮሐ 1፤1.14) እኛ እንድናውቀውም በመካከላችን ኖረ፣ እውነት እንደ አንድ ነገር አይታይም፤ እውነት መገናኘት ነው፣ አለኝ ብሎ የሚጨበጥ ነገር አይደለም ከአንድ አካል ጋር መገናኘት ነው፣
ሆኖም ግን አንድያ የእግዚአብሔር አብ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የእውነት ቃል መሆኑን ማን ያሳውቀናል? ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር። ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ” (1ቆሮ 12፤3) ብሎ ያስተምረናል፣ ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ክርስቶስ ሥጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው እውነትን እንደምናውቅ የሚያደርገን፣ ኢየሱስ ጰራቅሊጦስ ብሎ ይገልጸልዋል ይህ ማለትም ለእርድታ የሚደርስ ረዳት በዚሁ የእውቀት ጉዞ አችን በጐናችን በመሆን የሚረዳን ነው፣ ኢየሱስ በመጨርሻው እራት ለሓዋርያት እንዳረጋገጠው መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ያስተምረናል የእርሱ ቃላትን ሁሉ እንድናስታውስ ያደርገናል (ዮሐ 14፤26)
እንታድያ! በዚሁ ሕይወታችንና የቤተ ክርስትያን ሕይወትን ወደ እውነት የመምራት ጉዳይ ላይ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የትኛው ነው? ብለን የጠየቅን እንደሆነ በመጀመርያ ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ሁሉ በእያንዳንዳችን ልብ እያኖረ እንድናስታውስ ያደርገናል፣ ምክንያቱም እነዚህ በብሉይ ኪዳን ነቢያት እንደ የእግዚአብሔር ሕግ የተገለጡት የኢየሱስ ቃላት በልባችን ታትመው በምናደርጋቸው ምርጫዎችና በየዕለቱ በምናካሄደው ኑሮ መሪ ሓሳብ በመሆን የኑሮ አመራር ይሰጡናል፣ በዚህም በትንቢተ ሕዝቅ ኤል የተነገረው ተፈጸመ፣ “ንጹሕ ውኃ እርጫችኋለሁ፤ እናንተም ንጹሕ ትሆናላችሁ፤ ከኵሰታችሁ ሁሉና ከጣዖታቶቻችሁ ሁሉ አነጻችኋለሁ፣ አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፣ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፣ የሥጋ ልብንም እሰጣችዋለሁ፣ መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ ሥር ዓቴን እንድትከተሉና ሕጌን በጥንቃቄ እንድትጠብቁ አደርጋለሁ” (ሕዝ 36፡25-27) እንደእውነቱ ከሆነ ተግባሮቻችን ከውስጣችን ነው ምንጭ የሚያገኙት፣ ልባችን ነው ወደ እግዚአብሔር ሊመለስ ያለበት በዚህም ለመንፈስ ቅዱስ የከፈትነው እንደሆነ እርሱ ይለውጠዋል፣
መንፈስ ቅዱስም ኢየሱስ እንዳለው ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል (ዮሐ 16፤13) ኢየሱስ እንድናገኝን ሙሉ እውነትን ለማወቅ ብቻ አይደለም የሚመራን ነገር ግን በእውነት ውስጥ ያጠልቀናል በዚህም ነገሮችን እግዚአብሔር እንደሚያውቃቸው አድርገን እንድናውቅ በማስቻል ከእርሱ ጋር አንድነት እንዲኖረን ያደርገናል፣ ይህንን በምንም ተአምር በኃይላችን ልናደርገው አንችልም፣ እግዚአብሔር ኅልናችን ካላበራልን በስተቀር ክርስትናችን አፍ አዊ ብቻ ይሆናል፣ የቤተ ክርስትያናችን ባህል መንፈስ ቅዱስ የእምነት ስሜት በልባችን ውስጥ እያስተጋባ ይሰራል ይላል፣ ይህ የእምነት ስሜት ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እንደሚያስተምረው “የእግዚአብሔር ሕዝብን በቤተ ክርስትያን ሥልጣናዊ ትምህርት መሪነት የተላለፈውን እምነት እንዲቀበል በቅኑ ፍርድ እንዲያጠናው እና በሙላት በሕይወቱ ኑሮ በተግባር እንዲኖረው ያደርገዋል” (ብርሃነ አሕዛብ 12)፣ እስቲ ወደ ገዛ ራሳችን መለስ ብለን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፤ ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ክፍት ነኝን? እንዲያበራልኝ መንፈስ ቅዱስን እለምናለሁን፧ በእግዚአብሔር ነገሮች ላይ እንዳተኩር እንዲያበራልኝ እጸልያለሁን? ይህ ጸሎት ዘወትር ማድረግ ያለብን ጸሎት ነው፣ ማለትም መንፈስ ቅዱስ ልቤ ለእግዚአብሔር ቃል ክፍት እንዲያደርግልኝ! ልቤ ለመልካም ነገር ክፍት እንዲሆን! ልቤ ለእግዚአብሔር መልካምነት ክፍት እንዲሆን፣ ዘወትር መጸለይ አለብን፣ እስቲ ልጠይቃችሁ ስንቶቻችሁ ናችሁ በየዕለቱ ለመንፈስ ቅዱስ የምትጸልዩ፣ ጥቂቶች ይሆናሉ! ሆኖም ግን ይህንን የኢየሱስ ፍላጐት መፈጸም አለብን መንፈስ ቅዱስ ልቦቻችን ለኢየሱስ እንዲከፍተልን ሁሌ እንድንጸልይ ይሁን፣
“ሁሉን ነገሮች እያተነተነች በልቧ ታኖር የነበረችውን” (ሉቃ 2፤19.51) እመቤታችን ድንግል ማርያምን እናስታውስ፣ የእግዚአብሔር ቃልንና የእምነት እውነትን ተቀብሎ በሕይወት መኖር በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ይዳብራል፣ ስለዚህ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም መማር አለብን፣ የታዛዥነትዋ እሺ ማለትንና የእግዚአብሔር ልጅን ለመቀበል በልበ ምሉነት መቀበልዋን እንደገና መኖር ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ይህ ሕይወትዋን ባጠቃላይ የለወጠ ፍጻሜ ነውና፣ በመንፈስ ቅዱስ አማክኝነት እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ በልባችን መኖርያ ያገኛሉ፤ እኛ በእግዚአብሔር እግዚአብሔር ደግሞ በእኛ ይኖራል፣ ነገር ግን እውነት ሕይወታችን በእግዚአብሔር ትመራለችን? ከእግዚአብሔር በማብለጥ ቅድምያ የምንሰጣቸው ነገሮችስ ስንት ናቸው?ውድ ወንድሞችና እኅቶች የሕይወታችን አንድያ ጌታ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር እውነት እንዲመራን የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ሕይወታችን እንዲያበራው ይሁን፣ በዚሁ የእምነት ዓመት ቅዱስ መጽሓፍን በማንበብና በማስተንተን ትምህርተ ክርስቶስን በማጥናትና የቤተ ክርስትያን ምሥጢራትን በማዘውተር፤ ክርስቶስንና የእምነት እውነቶችን ለማወቅ ተጨባጭ ጥረት ያደረግን እንደሆነ ራሳችን እንጠይቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እምነታችን ኑሮአችን እንዲያቃና ምን እያደረግን ነው ብለን እንጠይቅ፣ ክርስትያን መሆን ለአንድ ጊዜ ብቻ ወይም ለተወሰነ ግዜ በአንዳንድ አጋጣሚ ብቻ አይደለም ወይንም በአንድ ምርጫዎች ብቻ አይደለም፣ እንዲህ ብሎ ክርስትና የለም፣ ክርስትያን መሆን በሙላት በአጠቅላይ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠንና የሚያስተምር የክርስቶስ እውነት በየዕለቱ በአጠቃላይና ለዘወትር ክርስትያን መሆን እንዳለብን ያስተምረናል፣ በሐዋርያት ጐዳና እንድንጓዝ እንዲመራን ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ሁል ግዜ እንለምነው፣ ይህንን ቍርጥ ውሳኔ እናድርግ መንፈስ ቅዱስን በየዕለቱ እንዲያበራልን እንዲመራንና እንዲረዳን ለመጸለይ እንወስን፣ ታደርጉታላችሁን? እንዲህ በማድረግ ነው መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሱስ የሚያቀርበን፣ እግዚአብሔር ይስጥልን፣







All the contents on this site are copyrighted ©.