2013-05-10 16:55:23

ቤተ ክርስትያን ትሕትናና ብርታት ለብሳ ክፍትና ተራማጅ መሆን አለባት፣


ቤተ ክርስትያን ትሕትናና ብርታት ለብሳ ክፍትና ተራማጅ መሆን እንዳለበት ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና ባደረጉት ስብከት ገልጠዋል፣ ቅዱስነታቸው ለር.ሊ.ጵጵስና ከተመረጡ ሁለት ወር ሊሞላ ሶስት ቀኖች በቀሩት ወቅት እንደ አዲስ አግባብ የጀመሩት በቅድስት ማርታ እንግዳ መቀበያ ቤተ መቅደስ በየዕለቱ ከተለያዩ የቅድስት መንበር አስተዳዳሪውችና ሠራተኞች ጋር በሚያሳርጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ የሚያቀርብዋቸው አጫጭር ስብከቶች ታላቅ ትኵረት እየተሰጠው ነው፣
ቅዱስነታቸው በእነዚሁ ስብከቶቻቸው ቀስ በቀስ የሚያስተምሩት የጥንታዊትዋ የሓዋርያት ቤተ ክርስትያን ታሪክ በሓዋርያት ሥራ እንደተመለከተው ሲያቀርቡ የመንበረ ጴጥሮስ ተልእኮአቸውን እንዲሁ ሊጀምሩት ማቀዳቸውና የዘመናችን ቤተ ክርስትያን እንደ ጥንትዋ የሓዋርያት ቤተ ክርስትያን በትሕትናና በብርታት መንፈስ ቅዱስን እያዳመጠች መጓዝ እንዳለባት ለመግለጥ ነው፣
ቅዱስነታቸው የሚያራምዱት ዕቅድ ቤተ ክርስትያንዋ ከገዛ ራስዋ ወጥታ የተገለሉትንና ድኆችን ማገልገል እንዳለባት ነው፣ ቤተ ክርስትያን እንደ እንጀራ እናት ሳይሆን እውነተኛ እናት ሆና የሚለያዩ ግድግዳዎች ሳይሆን የሚያገናኙ ድልድዮች መገንባት አለባት፣ ቤተ ክርስትያን እንደ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ የእርዳታ ድርጅት ሳይሆን የፍቅር ማኅበረ ሰብ ሆና በሮችዋ ለሁሉም ክፍት ናቸው፣ እያንዳንዱ በጥምቀት የቤተ ክርስትያን አባል የሆነ ሁሉ ክርስቶስን ለመስበክና ቤተ ክርስትያንን ወደፊት ለማራመድ ታላቅ ኃላፊነት አለው፣ ክርስትያን መሆን ማለት በአንድ ሙያ ሰልጥኖ ባለሥልጣን ወይም ባለሙያ መሆን ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየተመሩ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ዜናን ለማብሰር የሚያስችል ስጦታ ነው፣ ለዚህም ነው ክርስትያን ሁሌ በጉዞ ላይ መሆን ያለበት ክርስትያን መቆም የለበትም መራመድ አለበት፣
“ቤተ ክርስትያን ብርታት ካጣች የፍርሃት መንፈስ በውስጥዋ ያድራል፣የፈሪ ክርስትያኖች ቤትም ትሆናለች፣ ብርታት የጐደለው ፈሪ መሆን ቤተ ክርስትያንን እጅግ ይጐዳታል፣ ምክንያቱም ፍርሓት ከቤትህ እንዳትወጣ ያደርገሃል፤ አቅጣጫህ ታጠፋለህ፤ ሌላው ይቅር መጸለይም አትችልም ወንጌሉን ለመስበክም ብርታት ይጐድልሃል፣ ይህንን ብርታት ለማግኘት ከፈለግን የእግዚአብሔርን ቃል በትሑት ልብ መቀበል መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን እንዲሰራ ክፍት ሆነን እርሱን መቀበልና ለእርሱ መታዘዝ ያስፈልጋል፣ እንዲህ የምታደርግ ቤተ ክርስትያን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እሺ በማለት በእርሱ ፍቅር ጸንታ ትኖራለች፣
“የቤተ ክርስትያን ሰዎች የሆንን እኛ በአንድ የፍቅር ታሪክ መካከል እንገኛለን፣ እያንዳንዳችን በዚሁ የፍቅር ሰንሰለት እንደ ቀለቤት ነን፣ ይህንን ያልተረዳን እንደሆነ ስለቤተ ክርስትያን ምንም አንረዳም ማለት ነው፣
ሲሉ የክርስትና ኃላፊነትን ገልጠው ነበር፣
ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስትያን ማንነትዋን አውቋ እንድትጓዝና እንድትሰራ ሲጠይቁ ያሉ አደገዎችንም ይጠቅሳሉ፣ የኢየሱስ መንገድ የፖሎቲካ ወይንም የርእዮተ ዓለም መንገድ ወይንም የኅብረተሰብ መምርያ ሞራል ስላልሆነ አንደኛው አደጋ ከዓለማዊነት እንደሚመጣ እንዲህ ሲሉ ገልጠው ነበር፣
“ቤተ ክርስትያን የዓለማዊነት መንፈስ የለበሰች እንደሆነ በውስጥዋም የዚህ ዓለም መንፈስ የገባ እንደሆነ የጌታ ሰላም ያልሆነው የዚህ ዓለም ሰላም ካገኘች ደካማ ቤተ ክርስትያን ናት ወዲያውኑም ትሸነፋለች የጌታ ወንጌል መል እክትን ለማድረስ አትችልም፣ ዓለማዊት ከሆነች የመስቀል መል እክት የሆነውን የክርስቶስ መል እክትን ለማራመድ አትችልም፣ ወደኋላ ትመለሳለች እንጂ ወደፊት አትራመድም፤ በማለት ሁነኛ እርምጃ መውሰድ እንዳለብንና የኢየሱስ መንፈስ ለብሰን መንቀሳቀስ እንዳለብን አስተምረዋል፣
ቅዱስነታቸው ሓምሳ ዓመት ወደ ኋላ መለስ ብለውም መንፈስ ቅዱስ በሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ ያበራልንን ነገር እግምት ውስጥ በማስገባት “መንፈስ ቅዱስ በጉባኤው አማካኝነት ያለንን ነገር ሁሉ ፈጽመናል ወይ ሲሉ ይጠቃሉና፤
“አይመስለኝም፤ ይህንን ሓምሳኛውን ዓመት እናክብር የማያስቸግረን ኃውልት እንሥራ፣ ከዚህ የባሰ ደግሞ ወድኋላ ሊጐቱን የሚፈልጉ ድምጾች አሉ፣ ይህ የሚያመለክተን ደንቆሮዎች መሆናችንን ነው፣ መንፈስ ቅዱስን እንዳይሰራ እንደማገድና እንደማስተኛት ነው፣ ጌታ እንደሚለውም ልበ ደንዳናዎችና ደንቆሮዎች መሆን ነው፣ እንደእውነቱ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ የሚያስቸግረን ይመስለኛል ምክንያቱም ያንቀሳቅሰናል እንድንጓዝ ይገፋፋናል ቤተ ክርስትያን ወደፊት እንድትራመድ ይገፋታል፣ እውነት ነው ቤተ ክርስትያን ሁሌ በመስቀልና ትንሣኤ በስደትና በጌታ መጽናናት መካከል ነው የምትጓዘው፤ ሆኖም ግን መንገዱ ይህ ነው በዚህ መንገድ የሚጓዝም አይሳሳትም፣ ቤተ ክርስትያን የፍቅር ታሪክ እንጂ የቢሮክራሲ መዋቅር አይደልችም፣ እናት ናት፣
“በዚህ ቅዳሴ ብዙ እናቶች አላችሁ፣ አንድ ሰው መጥቶ አንቺ የቤት አስተዳዳሪ እንጂ እናት አይደልሽም ቢል አይደለም እናት ነኝ ነው የምንለው፣ ቤተክርስትያንም እንደዛ እናት ናት. እኛም፣ በዚሁ እናታዊ የፍቅር ታሪክ እንጓዛለን ይህንን ወደፊት የሚያራምድ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው፤ እኛ ሁላችን አንድ ቤተ ሰብ ነን እናታችንም ቤተ ክርስትያን ናት ሲሉ እውነተኛው የቤተ ክርስትያን ባህርይ ገልጠዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.