2013-05-03 14:42:21

የቅዱስነታቸው ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ወደ አገረ ቫቲካን መመለስ


RealAudioMP3 እ.ኤ.አ. ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ በገዛ ፈቃዳቸው የቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ ሥልጣናቸው በእድሜ መግፋት በሚል ውሳኔ የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይነት የሚጠይቀው ጉልበት መጓደል ምክንያት ለቀው እ.ኤ.አ. የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ሮማ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው የካስተል ጋንዶልፎ ሐዋርያዊ ሕንፃ ተዛውረው ከሁለት ወር ቆይታ በኋላ ወደ ሃገረ ቫቲካን ተመልሰው ሐዋርያዊ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ሲለቁ እንደወሰኑትም በሃገረ ቫቲካን በሚገኘው በእመ ቤተ ክርስቲያን የመናንያን ገዳም መግባታቸው የቅድስት መንበር የዜናና ኅትመት ክፍል ተጠሪ አባ ፈደሪኮ ሎምባርዲ ትላትና በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
ቅሱነታቸው ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ እ.ኤ.አ. ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በሮማ ሰዓት አቆጣጠር ከቀትር በኋላ ልክ 4 ሰዓት ተኩል ከካስተል ጋንዶልፎ ሐዋርያዊ ሕንፃ ከሚገኘው የሄሊኮፕተር ማረፊያ ተነስተው ሃገረ ቫቲካን በሚገኘው የሄሊኮፕተር ማረፊያ ደርሰው ወደ እመ ቤተ ክርስቲያን ገዳም መዛወራቸውና እዛው በገዳሙ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ አቀባበል እንዳደረጉላቸውም አባ ሎምባርዲ ገልጠው፦ በገዳሙ የቅዱስነታቸው ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ የግል ዋና ጸሓፊ የቤተ ጳጳስ ኅየንተ ብፁዕ አቡነ ገዮርግ ጋኤንስዋይን እንዲሁም የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ ሆነው በማገልገል ላይ በነበሩበት ወቅት የሸኙዋቸው Comunione e liberazione-ሱታፌና አርነት በተሰየመው ካቶሊካዊ እንቅስቃሴ ሥር የተመሠረተው የደናግል ማኅበር አባላት አራት ደናግል ቅርብ ሆነው እንዲያገለግሉዋቸው እዛው በገዳሙ እንደሚኖሩ አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም አባ ሎምባርዲ እ.ኤ.አ. መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ወደ ካስተል ጋንዶልፎ በመሄድ ከቅዱስነታቸው ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ጋር ተገናኝተው እንደነበርና እንዲሁም ሚያዝያ 16 ቀን የቅዱስነታቸው ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ የተወለዱበት ቀን ምክንያት ስልክ በመደወል መልካም ምኞት መግለጣቸውና በዚያን ዕለት ጧት ያሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ ልኂቅ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ እግዚአብሔር በፍቅሩ ከጎናቸው ሆኖ እንዲጠብቃቸው ስለ አሳቸው ጸሎት ማዕከል ያደረገ እንደነበርና እ.ኤ.አ. ግንቦት 1 ቀን የቅዱስ ዮሴፍ ዓመታዊ በዓል ምክንያት የልኂቅ ር.ሊ.ጳ. የቅዱስ ስም ዕለት ምክንያትም ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ስልክ በመደወል መልካም የቅዱስ ስም ቀን መልእክት እንዳቀረቡላቸው አባ ሎምባርዲ ገልጠው የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አጠቃለዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.