2013-04-17 19:37:56

የዐቢይ ፆም ሰባተኛ ሰንበት


«ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ አማን አማን እብለከ ዘኢተወልደ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይክል በዊዓ መንግሰተ እግዚአብሔር» (ጌታ ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፣እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም፡፡ ዮሐ 3፡5)፡፡ RealAudioMP3
አሁን የምንገኝበት የዐቢይ ፆም ሰባተኛው ሰንበት «ኒቆዲሞስ» ይሰኛል፤ ምክንያቱም ይህ ፈሪሳዊና የሕግ መምህር በሌሊት ወደ ክርሰቶስ በመሄድ ሰው ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚገባበትን መንገድ ተምሮበታልና፡፡ (ዮሐ 3›1-20) ኒቆዲሞስ በህግ መምህርነቱ ከፍ ያለ ስፍራ ቢኖረውም በክርስቶስ ፊት ዕውቀቱ ጎዶሎና ትክክለኛ የመዳኛ መንገድም የትኛው እንደሆነ ባለማወቁ ወደ ክርስቶስ ሄደ፡፡ ጨለማው እንዲበራለት በጨለማ ላይ ሥልጣን ወዳለው ክርስቶስ ሄደ፡፡ ክርስቶስም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለመግባት «ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ» እንደሚገባው አስተማረው፡፡የዚህ ወንጌል ማእከላዊ መልዕክት ወደዘለዓለም ሕይወት ለመግባት «ዳግም ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ» አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑ ነው፡፡ ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባው ነገር ቢኖር፣ እኛ ተጠምቀናል በምስጢረ ሜሮንም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች ተቀብለናል፤ ነገር ግን አኗኗራችን በውሃ እና በመንፈስ ቅዱስ እንደተወለደ ሰው ነውን? ይህን ጥያቄ የማነሳው በወንጌሉ ውስጥ «ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስ የተወለደ ግን መንፈስ ነው» (ዮሐ 3፡6) የሚል ስለማነብ ነው፡፡ እንግዲህ በውሃና በመንፈስ ቅዱስ ተወልዶ ወደ ምድር ብቻ መመልከት አያስፈልግም፤በአንጻሩ ሐዋርያው እንዳለው «አዲስ ፍጥረት» መሆን መጀመር ነው (ገላ 5፡17)፡፡ ያኔ የእግዚአብሔር ልጅነትን መብት ያገኛል (ዮሐ 1፡12)፤ ከአሕዛብ የተለየ፣የንጉሥ ካህን፣ከተመረጠውም ሕዝብ ወገን መሆኑን ያሳያል (1ጴጥ 2፡9)፣የዘለዓለም ሕይወት ተካፋይም ይሆናል፡፡
እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ነን ካልን እሱን አባታችንን እንምሰል፡፡ በሰብዓዊ አመለካከት ሲታይ በአብዛኛው መልኩ ወደ ወላጆቹ ቀረብ የማይል ልጅ ይጠረጠራል ባካባቢው ሰዎች፤የኛም አኗኗራችን ከእግዚአብሔር መንገድ ጋር የሚጻረር ከሆነ የእርሱ ልጆች መሆናችን ያጠራጥራል፡፡ በእርግጥ የምናምን ከሆነ ያመንነውን አምላካችንን መስለን በትእዛዙ እንመላለስ፤ ለዚህም የእርሱ መለኮታዊ ጸጋ ትርዳን፡፡
ሰላም ወሠናይ
አባ ዳዊት ወርቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን








All the contents on this site are copyrighted ©.