2013-04-17 18:34:34

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ፣


ውድ ወንድሞችና እኅቶች! መልካም ቀን ይሁንላችሁ፤ በጸሎተ ሃይማኖት ጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደወጣና በእግዚአብሔር አብ ቀኝ እጅ RealAudioMP3 እንደተቀመጠ የሚገልጥ አንቀጽ እናገኛለን፣ የጌታ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት በዕርገቱ ከዚህ ዓለም ወደ ሰማያዊ አባቱ በመሄዱና በቀኝ እጁ ከፍ በማለቱ ያከትማል፣ የዚህ ፍጻሜ ትርጉም ምን ይሆን? ለሕይወታችን የሚያስከትላቸው ነገሮችስ የትኞቹ ናቸው? በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የተቀመጠውን ኢየሱስ ማስተንትን ምን ማለት ነው? እነኚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ወንጌላዊው ሉቃስ እንመልከት፣
ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ከሚያደርገው የመጨረሻውን ንግደት በማጤን እንጀምር፤ ይህንን በተመለከተ ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ይላል፤ “የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥” (ሉቃ 9፤51) ወደ ቅድስትዋ ከተማ ሲወጣ ከዚህ ዓለም ኑሮ የሚወጣበት መኖርያውን ማለት ሰማይን ይመለከታል ሆኖም ግን ወደ አባቱ የክብር ሕይወት የሚወስደው መንገድ በመስቀል የሚያልፍ መሆኑን ያውቅ ነበር፤ ይህም ስለሰው ፍቅር ማድረግ ያለበት ለመለኮታዊ ዕቅድ መታዘዝ ነው፤ አዲስ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ በቍ 661 ላይ “በመስቀል ላይ መውጣት የኢየሱስ ወደ ሰማይ መውጣትን አስቀድሞ ይነግራል” ይላል፣ በእግዚብሔር ክብር ውስጥ ለመግባት መጀመርያ በየዕለቱ ለፍላጎቱ ታማኝነት እንዲሚያስፈልግ ይህ ታማኝነት መስዋዕትነትን የዕቅዶቻችን መለወጥን ሊጠይቅ ይችላል፣ የኢየሱስ ዕርገት በተጨባጭ በደብረ ዘይት እውን ሆነ፣ በሕማማቱ ጊዜ በዚህ ኮረብታ ከአባቱ ጋር በጠለቀ ግኑኝነት አንድ ለመሆን በጸሎት ተጠምዶበት የነበረ ቦታም ነው፣ እዚህ ላይ የሚያሳየን ያ ጸሎት በእግዚአብሔር ዕቅድ ታማኝ ሆኖ ለመኖር ጸጋ እንደሚሰጥ ያሳየናል፣
ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ መጨረሻ ላይ የዕርገቱ ሁኔታን ጠቅለል ባለ መንገድ ያቀርብልናል፣ ኢየሱስ ሐዋርያቱን እስከ ቢታንያ በመውሰድ ወደ ውጭ ይወስዳቸዋል፣ እጆቹን አንስቶ ይባርካቸዋል፣ እየባረካቸውም ከእሳቸው ተለየ ወደ ሰማይም ወጣ፤ እሳቸውም በእርሱ ፊት ተደፍተው ሰገዱ ከዛም በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱና እዛም ጌታን እያመስገኑ ሁሌ በቤተመቅደስ እንደተቀመጡ ይተርካል፣ (ሉቃ 24፤50-53) እዚህ ላይ በሁለት ነጥቦች ማትኰር እወዳለሁ፣ ኢየሱስ በዕርገቱ ጊዜ የክህነት ሥራውን ማለት ቡራኬ የመስጠት ሥራውን ሲያደርግ ሐዋርያቱም እምነታቸውን ተደፍተው በመስገድ ያረጋግጣሉ፤ ይህ አንዱ አስፈላጊ ነጥብ ሲሆን በዓለም ውስጥ ኢየሱስ አንድያ ዘለዓለማዊ ካህን ሆኖ በሕማማቱ በሞቱ በመቀበሩና ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ተሻግሮ ሁሌ ስለ እኛ ለማማለድ ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሔር አብ በመውጣቱ አደረገው (ዕብ 9፤24) ቅዱስ ዮሐንስ በአንደኛ መል እክቱ እንደሚያመለክተው እርሱ አማላጃችን ነው፣ ይህ አማላጅ ወይንም ጠበቃ የሚለው ቃል እንዴት ደስ ይላል፤ አንድ ሰው ክስ ተመስርቶበት ወደ ዳኛ ሲቀርብ ለመጀመርያ ጊዜ የሚያደርገው ጠበቃ መሻት ነው፣ እኛ ሁሌ የሚከላከልልን ጠበቃ አለን፤ ከዲያብሎስ ጥቃት ይከላከልልናል፤ ከገዛ ራሳችንና ከኃጢአቶቻችን ሳይቀርም ይከላከልልናል፣ ውድ ወንድሞችና እኅቶች ከእርሱ ምሕረትንና ቡራኬን መጠየቅ እንጂ መፍራት የሌለብን ጠበቃ አለን፣ እርሱ ሁሌ ይምረናል፣ ጠበቃችን ስለሆነም ሁሌ ይከላከልልናል፣ ይህንን እንዳንረሳ አደራ፣ የኢየሱስ ወደ ሰማይ ዕርገት ይህንን አጽናኝ እውነት ለጉዞአችን ያረጋግጥልናል፣ በእውነተኛ ሰውና እውነተኛ አምላክ በሆነው ክርስቶስ ሰብአዊነታችን ወደ እግዚአብሔር ቀርበዋል፣ እርሱ መንገዱን ከፈተልን፤ ወደ አንድ ተራራ ሲወጡ የዋስትና መጠጊያአችን ነው፤ ወይንም ወደ እርሱ በመሳም ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰን መገናኛ ገመድ ነው፣ ሕይወታችን ለእርሱ የተውንና በእርሱ እንድንመራ የፈቀድን እንደሆነ በሚታመኑ እጆች መኖራችን በአዳኙ እጆች በጠበቃችን እጆች መኖራችን እርግጥ ነው፣
ሁለተኛ ነጥብ ደግሞ፤ ቅዱስ ሉቃስ እንደሚተርከው ሐዋርያቱ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረጉን ካዩ በኋላ በታላቅ ደስት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱ ያመለክታል፣ ይህ ከባህርያዊ ነገር ወጣ ያለ ይመስላል፣ በዘልማድ ከቤተሰቦቻችን ስንለይ በተለይ ደግሞ ከምንወዳቸው እንደገና ላለመገናኘት እንደ በሞት ስንለያይ እጅግ እናዝናለን ምክንያቱም እንደገና ልናያቸው አንችልም ድምጻቸውን ዳግም ለመስማት ወይንም ፍቅራቸውን ለማጣጣምና በመሃከላችን መኖራቸውን እንደገና ልናገኘው አንችልምና፣ በዚሁ አንጻር ግን ወንጌላዊው ሓዋርያት በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል ይላል፤ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ይህ የሚያመልከተው ነገር ካለ ከባህርያዊ አመለካከት አንጻር በእምነት ዓይን የተመለከትን እንደሆነ ኢየሱስ ሁሌ ከእርሳቸው ጋር መሆኑንና ፈጽሞ እንደማይለያቸው በአባቱ ክብር እንደሚደግፋቸው እንደሚመራቸውና ለእርሳቸው እንደሚያማልድ በእምነት ስላረጋገጡ ነው፣
ቅዱስ ሉቃስ የሐዋርያት ሥራ መጽሓፍም ጸሓፊ በመሆኑ የጌታ ዕርገትን በሐዋርያት ሥራ የመጀመርያ ም ዕራፍም ጠቅሶታል፣ ይህንን ያደረገበት ምክንያትም የኢየሱስ ምድራዊ ሕይወትን ከቤተ ክርስትያን ሕይወት ጋር ትሥስር እንዳላቸው ለማሳየት ነው፣ እዚህ ላይ ቅዱስ ሉቃስ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ትዕይንት የደበቀውንና ወደ ሰማይ ሲመነጥቅ የከለለውን ደመናም ይጠቅሳል፣ ሐዋርያቱም ወደ እግዚአብሔር አብ የሚያርገውን ክርስቶስ እያስተነተኑ መሆናቸውንም ይገልጣል (የሐዋ ሥራ 1፤9-10) ታሪክ ልብ ብለን የተመለከትን እንደሆነ ሐዋርያት በዚህ ሁኔታ ሳሉ ሁለት ነጭ ልብስ የለበሱ ሰዎች መጥተው ሐዋርያቱን እዛ ላይ ሰማይን እየተመለክቱ ደርቀው እንዳይቀሩ ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳዩት ሁኔታና አግባብ ዳግም እንደሚመለስ ለሁሉም ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ይነግርዋቸዋል (የሐዋ ሥራ 1፤10-11)፣ የጌታ ኢየሱስ ቃለ ወንጌልን በዕለታዊ ሕይወት ለመስበክና ለመመስከር ከእርሱ ኃይል ለማግኘት በእርሱ ጌትነት አስተንትኖ መንሳት እንዳለባቸው ያመልክታል፣ የቅዱስ በነዲክቶስ ማለትም አቡነ ብሩክ አስትንትኖና ሥራ ወይንም ጸሎትና ሥራ የሚለው መሪ ሓሳብም ከዚህ ይመንጫል ማለትም ሁለቱም ለክርስትያናዊ ሕይወታችን አስፈላጊዎች መሆናቸውን ለማመልከት ነው፣
ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ ዕርገት የጌታ በዚህ አለመኖር አያመለክትም ነገር ግን እርሱ በአዲስ መንገድ በመሃከላችን እንደሚኖር ቀድሞ እንደነበረው በአንድ የተለየ ክልል ብቻ ተወስኖ አለመኖሩን ሲያመለክት ይህ አዲስ ክስተት ጌታ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ግርማዊነት ቦታና ጊዜ በማይወስነው በአዲስ መንገድ ሁሌ በእያዳንዳችን ጐን እንደሚኖር ያመለክታል፣ በሕይወት ዘመናችንና በኑሮ አችን ብቻችን አይደለንም፣ ይህ አማላጅና ጠበቃ ሁሌ እጐናችን ሆኖ ይረዳናል ይከላከልልናልም፣ ፈጽሞ ብቻችን ልንሆን አንችልም፤ የተሰቀለውና ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ጌታ ይመራናል፤ እንዲሁም ምንም ድምጽ ሳያሰሙና ሳይታዩ በቤተ ሰብ እና በሥራ ኑሮአቸው እንዲሁም በችግሮቻቸው በደስታቸውና በተስፋቸው በየዕለቱ እምነታቸውን በሙላትና ብታማኝነት በጌታ ፍቅራዊ ግርማዊነት በመተማመን እንዲሁም ከሞት በተነሳውና ወደሰማይ ባረገው ጠበቃችን የሆነው ጌታ በመተማመን ከእኛ ጋራ የሚኖር ወንድሞችና እኅቶች እንዳሉን መዘንጋት የለብንም፤ አይዞ! ብቻችን አይደለንም፣ ሲሉ ትምህርታቸውን ደምድመዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.