2013-04-13 13:56:18

ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ.፦ “እግዚአብሔርን ማዳመጥና ኢየሱስን መከተል ነጻ ያወጣናል ደስተኞችም ያደርገናል”


RealAudioMP3 እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ እንደተለመደው በቅድስት ማርታ ሕንፃ በሚገኘው ቤተ ጸሎት አንዳንድ ሎ ሶርቫቶረ ሮማኖ የተሰየመው የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ሠራተኞችና ጋዜጠኞች በተገኙበት ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ በዕለቱ ምንባብ ተንተርሰው፦ “ዓለም ፈጽሞ ሊሰጠንና ሊዋሰን የማይቻለውን ነጻነትና ደስታ እግዚአብሔርን ከማዳመጥ ብቻ ነው የምንታደለው፣ እግዚአብሔርን መታዘዝ ማለት እርሱን ማዳመጥ ማለት ሲሆን፣ ይኽም እግዚአብሔር ለሚያመላክትልን መንገድ ለመቀበል ክፍት ልብ ሊኖረ ይገባል። ነጻ የሚያወጣንና ደስተኞች የሚያደርገን እግዚአብሔርን መታዘዝ ማለትም ቃሉን ማዳመጥ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ ለፈሪሳውያንና ለጸሕፍቶች እኔ የምታዘዘው ኢየሱስን እንጂ እናንተ ከኢየሱስና ከእግዚአብሔር ላልሆነው እፈጽመው ዘንድ ለምትሰጡኝ ትእዛዝ አይደለም። ብዙውን ጊዜ ዓለም የሚለንና ኢየሱስ በሚለው ቃል ተወጥረን በማስመሰልና በአድር ባይነት መንፈስ ስንመራ ይታያል፣ ኢየሱስን ስናዳምጥ በእኛ ላይ ምን ይከሰታል? ስደት መከራ ሊደቀንብን ይችላል፣ ኢየሱስ የሚያመለክተውን መንገድ መከተል ብዙ ውጣ ውረድ ሊያስከትልብን ይችላል፣ ሆኖም ግን ነጻነታችን እና ደስታችን እርሱ ባመለከተው መንገድ መጓዝ ነው” እንዳሉ የቅዳሴው ሥነ ሥርዓት የተከታተሉት የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ አመደዮ ሎሞናኮ ገለጡ።
“በዛሬው ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታቀርብልን ምእዳን በኢየሱስ መንገድ ተራመዱ እርሱ የሚያመለክተውን መንገድ ተከተሉ የሚል ነው። ስለዚህ ይኸንን ለመፈጸም ዓለም የሚያቀርብልን ነጻ የማያወጣውን ኃጢአት ተመሳስሎ መኖር ላይ የጸናው ያድር ባይነት መንገድ መቃወምና እምቢ ማለት ተገቢ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ነው። በኢየሱስ የተመለከተልን መንገድ ለመክተልና እግዚአብሔርን ለመታዘዝ እንድንችል መንፈስ ቅዱስ ደጋፊያችን ነው። በኢየሱሳዊው መንገድ እንድንጓዝ ኃይሉ ከመንፈስ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር አብ ኢየሱስን እንድናዳምጥና በኢየሱስ መንገድ እንጓዝም ዘንድ የሚያበቃን ይኸንን መንፈስ አለ ምንም ውስንነት ይሰጠናል። የጽናት ጸጋ ያስፈልገናል። ስለዚህ ጌታ ሆይ ኃጢአተኛ ነኝ፣ አንተኑ መታዘዝ እየተመኘሁ አንዳንዴ የዓለምን መንገድ ስከተል እገኛለሁ፣ በአንተ መንገድ መመላለስን እሻለሁ” ካሉ በኋላ፦ “ኢየሱስ በሚያመለክትልን መንገድ እንጓዝ ዘንድ ጸጋውን እንለምን፣ ይኸንን መንገድ ሳንከተል ስንቀር ምኅረት እንጠይቅ፣ ጌታ ይቅር ይልልናል፣ ምክንያቱም እርሱ ፍጹም የዋህና ደግ ነውና” በማለት ያቀረቡትን ሥልጣናዊ አስተንትኖ እንዳጠናቀቁ የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ ሎሞናኮ ካጠናቀሩት ዘገባ ለመረዳት ተችለዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.